1ከዚያም ዳዊት በራማ ካለው ከነዋት ሸሽቶ መጣና ዮናታንን፥”ምን አድርጌአለሁ? ጥፋቴስ ምንድነው? በአባትህ ፊት ኃጢአቴ ምን ቢሆን ነው ሕይወቴን ለማጥፋት የሚፈልገው? “ አለው።
2ዮናታንም ዳዊትን፥”ይህ ከአንተ ይራቅ፥ አትሞትም። ነገሩ ትልቅም ይሁን ትንሽ ሳይነግረኝ አባቴ ምንም አያደርግም። አባቴ ይህንን ነገር ለምን ይደብቀኛል? ነገሩ እንዲህ አይደለም።
3ዳዊት ግን እንደገና ማለና፥ “በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን አባትህ ያውቃል። እርሱም፥ 'ይህንን ዮናታን አይወቅ፥ ካልሆነ ያዝናል' ይላል። በሕያው እግዚአብሔር ስም፥ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ በእኔና በሞት መካከል የቀረው አንድ እርምጃ ነው" አለው።
4ዮናታን ዳዊትን፥ "የምትጠይቀኝን ሁሉ አደርግልሃለሁ" አለው።
5ዳዊትም ዮናታንን፥ "ነገ አዲስ ጨረቃ የምትታይበት ቀን ነው፥ ከንጉሡ ጋር ለመብላት መቀመጥ ይኖርብኛል። እስከ ሦስተኛው ቀን ምሽት ድረስ በመስኩ ውስጥ ሄጄ እንድደበቅ ፍቀድልኝ" አለው።
6አባትህ እኔን በማጣቱ ከጠየቀህ፥ "ዳዊት፥ መላው ቤተ ሰቡ ዓመታዊ መሥዋዕት ስለሚያቀርቡ ወደ ቤተ ልሔም ይሄድ ዘንድ እንድፈቅድለት አጥብቆ ለመነኝ' በለው።
7እርሱም፥ 'መልካም ነው' ካለህ ነገሩ ለአገልጋይህ ሰላም ሆኗል ማለት ነው። ነገር ግን እርሱ እጅግ ከተቆጣ ክፉ ሊያደርግብኝ እንደወሰነ በዚህ ታውቃለህ።
8እንግዲህ አገልጋይህን በርኅራኄ ተመልከተኝ። በእግዚአብሔር ፊት ከአገልጋይህ ጋር ቃል ኪዳን አድርገሃልና። ኃጢአት ቢገኝብኝ ግን አንተው ግደለኝ፤ ለምንስ ወደ አባትህ ትወስደኛለህ?" አለው።
9ዮናታንም፥ "ይህ ከአንተ ይራቅ! አባቴ ክፉ ሊያደርግብህ መወሰኑን ባውቅ አልነግርህም?"
10ዳዊትም ዮናታንን፥ "አባትህ አንደ አጋጣሚ በቁጣ ቢመልስልህ ማን ይነግረኛል?" አለው።
11ዮናታንም ዳዊትን፥ "ና፥ ወደ መስኩ እንሂድ" አለው። ሁለቱም ወደ መስኩ ሄዱ።
12ዮናታንም ዳዊትን እንዲህ አለው፥ "የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁን። ነገ ወይም በሦስተኛው ቀን እንደዚህ ባለው ሰዓት አባቴን በምጠይቀው ጊዜ፥ ስለ ዳዊት በጎ አሳብ ካለው ልኬብህ አላሳውቅህም?
13አባቴ በአንተ ላይ ክፉ ማድረጉ የሚያስደስተው ከሆነ በሰላም እንድትሄድ ባላሳውቅህና ባላሰናብትህ እግዚአብሔር በዮናታን ላይ ይህንን እና ከዚህም የከፋውን ያድርግበት። ከአባቴ ጋር እንደነበረ እግዚአብሔር ከአንተም ጋር ይሁን።
14አንተስ በሕይወት በምኖርበት ዘመን እንዳልሞት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታማኝነት አታሳየኝም?
15እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች፥ እያንዳንዳቸውን ከምድር ላይ በሚያጠፋበት ጊዜ የቃል ኪዳን ታማኝነትህን ከቤቴ አታጥፋ"።
16ሰለዚህ ዮናታን ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገና”እግዚአብሔር ከዳዊት ጠላቶች እጅ ይጠይቀው“ አለ።
17ዮናታን ነፍሱን እንደሚወዳት ዳዊትን ይወደው ስለነበረ፥ ለእርሱ ከነበረው ፍቅር የተነሣ ዳዊት እንደገና እንዲምልለት አደረገ።
18ከዚያም ዮናታን እንዲህ አለው፥”ነገ አዲስ ጨረቃ የምትታይበት የወር መጀመሪያ ቀን ነው። ወንበርህ ባዶ ስለሚሆን ላትኖር ነው።
19ለሦስት ቀናት ከቆየህ በኋላ፥ ፈጥነህ ውረድና በዚህ ጉዳይ ካሁን በፊት ወደተደበቅህበት ስፍራ መጥተህ በኤዜል ድንጋይ አጠገብ ቆይ።
20በዒላማ ላይ የምወረውር መስዬ ሦስት ፍላጻዎችን ወደዚያ አቅራቢያ እወረውራለሁ።
21ከእኔ ጋር ያለውን ታዳጊ ወጣት እልከውና፥ 'ሂድ ፍላጻዎቹን ፈልግ' እለዋለሁ። ታዳጊውን ልጅ፥ 'ተመልከት፥ ፍላጻዎቹ አጠገብህ ናቸው፤ ውሰዳቸው' ካልኩት ሕያው እግዚአብሔርን! ለአንተ ደኅንነት እንጂ ጉዳት አይሆንብህምና ትመጣለህ።
22ነገር ግን ታዳጊውን ወጣት፥ 'ተመልከት፥ ፍላጻዎቹ ከአንተ በላይ ናቸው' ካልኩት እግዚአብሔር አሰናብቶሃልና መንገድህን ሂድ።
23እኔና አንተ ያደረግነውን ስምምነት በሚመለከት እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ለዘላለም ምስክር ነው።"
24ስለዚህ ዳዊት በመስኩ ውስጥ ተደበቀ። አዲስ ጨረቃ በሆነ ጊዜ ንጉሡ ምግብ ለመብላት ተቀመጠ።
25ንጉሡ እንደተለመደው በግድግዳው አጠገብ በነበረው በመቀመጫው ላይ ተቀመጠ። ዮናታን ተነሣ፥ አበኔርም በሳኦል አጠገብ ተቀምጦ ነበር። የዳዊት ቦታ ግን ባዶ ነበር።
26በዚያን ቀን ሳኦል ገና ምንም አልተናገረም፥ ምክንያቱም፥ "አንድ ነገር ደርሶበት ይሆናል፥ ወይም በሕጉ መሰረት አልነጻም ይሆናል፤ በርግጥ ባይነጻ ነው" ብሎ ሳላሰበ ነው።
27ነገር ግን አዲስ ጨረቃ በታየችበት ማግስት፥ በሁለተኛው ቀን የዳዊት ስፍራ ባዶ ነበር። ሳኦል ልጁን ዮናታንን፥ "የእሴይ ልጅ ዳዊት ትላንትም ይሁን ዛሬ ወደ ማዕድ ያልመጣው ለምንድነው?" አለው።
28ዮናታንም ለሳኦል እንዲህ በማለት መለሰለት፥ "ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም ለመሄድ እንድፈቅድለት አጥብቆ ለመነኝ።
29እርሱም፥ 'እባክህን እንድሄድ ፍቀድልኝ። በዚያ ከተማ ቤተሰባችን የሚያቀርበው መሥዋዕት አለ፥ እኔም በዚያ እንድገኝ ወንድሜ አዞኛል። አሁንም በፊትህ ሞገስን ካገኘሁ፥ ወንድሞቼን አያቸው ዘንድ እንድሄድ እባክህን ፍቀድልኝ' አለኝ። ወደ ንጉሡ ማዕድ ያልመጣው በዚህ ምክንያት ነው።"
30ከዚያም የሳኦል ቁጣ በዮናታን ላይ ነደደ፥ እርሱም እንዲህ አለው፥ "አንተ የጠማማና አመጸኛ ሴት ልጅ! ለራስህ ኃፍረትና ለእናትህ የዕርቃንነት ኃፍረት የእሴይን ልጅ እንደ መረጥክ የማላውቅ መሰለህ?
31የእሴይ ልጅ በምድር ላይ እስካለ ድረስ አንተም ሆንክ መንግሥትህ አትጸኑም። አሁንም በእርግጥ መሞት የሚገባው ነውና ልከህ አስመጣልኝ።“
32ዮናታንም አባቱን ሳኦልን፥”የሚገደለው በምን ምክንያት ነው? ያደረገውስ ምንድነው? “ ሲል መለሰለት።
33በዚያን ጊዜ ሳኦል ሊገድለው ጦሩን ወረወረበት። ስለዚህ አባቱ ዳዊትን ለመግደል መወሰኑን ዮናታን ተረዳ።
34ዮናታን እጅግ ተቆጥቶ ከማዕድ ተነሣ፥ አባቱ ስላዋረደው ስለ ዳዊት አዝኖ ነበርና በወሩ በሁለተኛው ቀን ምንም ምግብ አልበላም።
35በማግስቱ ዮናታን ከዳዊት ጋር ወደተቀጣጠሩበት መስክ ሄደ፥ አንድ ታዳጊ ወጣትም አብሮት ነበር።
36እርሱም ታዳጊውን ወጣት፥”ሩጥ፥ የምወረውራቸውን ፍላጻዎች ሰብስብ“ አለው። ታዳጊው ወጣት በሚሮጥበት ጊዜ ፍላጻውን ከበላዩ ላይ ወረወረው።
37ታዳጊው ወጣት ዮናታን የወረወረው ፍላጻ ወደ ወደቀበት ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ ዮናታን ታዳጊውን ተጣርቶ፥ "ፍላጻው ከአንተ በላይ ነው" አለው።
38ዮናታንም ታዳጊውን፥ "ቶሎ በል፥ ፍጠን፥ አትዘግይ!" አለው። ስለዚህ የዮናታኑ ታዳጊ ወጣት ፍላጻዎቹን ሰብስቦ ወደ ጌታው መጣ።
39ታዳጊው ወጣት ግን አንዳች የሚያውቀው አልነበረም። ጉዳዩን የሚያውቁት ዮናታንና ዳዊት ብቻ ነበሩ።
40ዮናታን የጦር መሣሪያዎቹን ለታዳጊው ወጣት ሰጥቶ፥ "ሂድ፥ ወደ ከተማ ውሰዳቸው" አለው።
41ታዳጊው ወጣት እንደ ሄደ፥ ዳዊት ከጉብታው ኋላ ተነሣ፥ ወደ ምድርም ተጎንብሶ ሦስት ጊዜ ሰገደ። እርስ በእርሳቸው ተሳሳሙ፥ ተላቀሱም፥ ዳዊትም አብዝቶ አለቀሰ።
42ዮናታንም ዳዊትን፥”'እግዚአብሔር፥ በእኔና በአንተ፥ በዘሬና በዘርህ መካከል ለዘላለም ይሁን' ተባብለን በእግዚአብሔር ስም ተማምለናልና በሰላም ሂድ” አለው። ከዚያም ዳዊት ተነሥቶ ሄደ፥ ዮናታንም ወደ ከተማ ተመለሰ።