1ሳኦል ልጁን ዮናታንን እና አገልጋዮቹን በሙሉ ዳዊትን እንዲገድሉት ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድደው ነበር።
2ስለዚህ ዮናታን ዳዊትን፥ "አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ይፈልጋል። በመሆኑም ለራስህ ጥንቃቄ አድርግ፥ በነገውም ቀን በምስጢራዊ ቦታ ተደበቅ።
3አንተ ባለህበት አካባቢ ሄጄ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፥ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ። አንዳች ነገር ካገኘሁኝም እነግርሃለሁ“ አለው።
4ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት መልካምን ነገር ተናገረ፥ እንዲህም አለው፥”ንጉሡ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ። እርሱ ክፉ አላደረገብህም፥ እርሱ የሠራው ሥራ ለአንተ መልካም ሆኖልሃልና።
5ነፍሱን በእጁ ላይ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ። እግዚአብሔርም ለእስራኤል በሙሉ ታላቅ ድልን ሰጠ። አንተም አይተህ ደስ ብሎህ ነበር። ያለምንም ምክንያት ዳዊትን በመግደልህ በንጹህ ደም ላይ ለምን ኃጢአት ትሠራለህ?“
6ሳኦልም ዮናታንን ሰማው። ሳኦልም፥”ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም“ ብሎ ማለ።
7ከዚያም ዮናታን ዳዊትን ጠራው፥ ዮናታንም ይህንን ነገር ሁሉ ነገረው። ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፥ እርሱም እንደቀድሞው በፊቱ ነበረ።
8እንደገናም ጦርነት ሆነ። ዳዊት ወጥቶ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ በታላቅ አገዳደልም ድል አደረጋቸው። እነርሱም ከፊቱ ሸሹ።
9ሳኦል በእጁ ጦሩን እንደያዘ በቤቱ ተቀምጦ እያለ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሳኦል ላይ መጣበት፥ ዳዊትም በገና ይደረድር ነበር።
10ሳኦል በጦሩ ዳዊትን ከግድግዳው ጋር ለማጣበቅ ሞከረ፥ ዳዊት ግን ከሳኦል ፊት ዘወር አለ፥ ስለዚህ የሳኦል ጦር በግድግዳው ላይ ተሰካ። በዚያ ምሽት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ።
11ሳኦልም በማግስቱ ይገድለው ዘንድ ከብበው እንዲጠብቁት ወደ ዳዊት ቤት መልዕክተኞች ላከ። የዳዊት ሚስት ሜልኮልም፥”በዚህ ሌሊት ሕይወትህን ካላዳንክ ነገ መገደልህ ነው“ አለችው።
12ስለዚህ ሜልኮል ዳዊትን በመስኮት እንዲወርድ አደረገችው። እርሱም ሄደ፥ ሸሽቶም አመለጠ።
13ሜልኮልም የቤተሰቡን የጣዖት ምስል ወስዳ በአልጋው ውስጥ አጋደመችው። በራስጌው ከፍየል ጸጉር የተሠራ ትራስ አስቀመጠች፥ በልብስም ሸፈነችው።
14ሳኦል ዳዊትን የሚወስዱ መልዕክተኞች በላከ ጊዜ እርሷ፥ "አሞታል" አለቻቸው።
15ከዚያም ሳኦል ዳዊትን እንዲያዩት መልዕክተኞች ላከ፥ እርሱም፥ "እንድገድለው ከነዐልጋው አምጡልኝ" አላቸው።
16መልዕክተኞቹ ወደ ቤት በገቡ ጊዜ፥ በዐልጋው ውስጥ የቤተሰቡ የጣዖት ምስል፥ በራስጌውም ከፍየል ጸጉር የተሠራው ትራስ ነበር።
17ሳኦል ሜልኮልን፥ "ጠላቴ እንዲሄድና እንዲያመልጥ በማድረግ ለምን አታለልሽኝ?" አላት። ሜልኮልም ለሳኦል፥ "'ልሂድ፥ አለበለዚያ እገድልሻለሁ' ስላለኝ ነው" ብላ መለሰችለት።
18ዳዊትም ሸሽቶ አመለጠ፥ ሳሙኤል ወዳለበት ወደ ራማም ሄደ፥ ሳኦል ያደረገበትንም ሁሉ ነገረው። ከዚያም እርሱና ሳሙኤል ሄዱ፥ በነዋትም ተቀመጡ።
19ለሳኦልም፥ "ዕወቀው፥ ዳዊት በራማ ነዋት ነው" ተብሎ ተነገረው።
20ሳኦልም ዳዊትን እንዲይዙት መልዕክተኞችን ላከ። እነርሱም ትንቢት የሚናገሩ የነቢያትን ጉባዔ፥ ሳሙኤልንም መሪያቸው ሆኖ ባዩ ጊዜ በሳኦል መልዕክተኞች ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ መጣባቸው፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ።
21ይህ ሁኔታ ለሳኦል በተነገረው ጊዜ፥ ሌሎች መልዕክተኞችን ላከ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። ስለዚህ ሳኦል እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ ሌሎች መልዕክተኞችን ላከ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ።
22ከዚያም እርሱ ደግሞ ወደ አርማቴም ሄደ፥ በሤኩ ወዳለው ጥልቅ የውሃ ጉድጓድም መጣ። እርሱም፥”ሳሙኤልና ዳዊት የት ነው ያሉት? “ ብሎ ጠየቀ። አንደኛው ሰው፥”በራማ ነዋት ናቸው“ ብሎ መለሰለት።
23ሳኦልም በራማ ወዳለው ነዋት ሄደ። የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱም ላይ መጣ፥ በራማም ወደሚገኘው ወደ ነዋት እስኪደርስ ድረስ በመንገድ ላይ ትንቢት ይናገር ነበር።
24እርሱም ደግሞ ልብሶቹን አወለቀ፥ በሳሙኤል ፊት እርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገረ፥ ያን ቀንና ሌሊቱን ሁሉ ራቁቱን ተጋደመ። እነርሱም፥”ሳኦል ከነቢያት አንዱ ሆነ እንዴ? “ ያሉት በዚህ ምክንያት ነው።