መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ሳሙኤል 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማ መሴፋ የሚኖር አንድ ሰው ነበር፤ ስሙ ሕልቃና ይባላል፥ እርሱም የኤፍሬማዊው የናሲብ ልጅ፥ የቶሑ ልጅ፥ የኤሊዮ ልጅ፥ የኢያርምኤል ልጅ ነበር።
2እርሱም ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ስማቸውም የአንደኛዋ ሐና፥ የሁለተኛዋም ፍናና ነበር። ፍናና ልጆች ነበሯት፣ ሐና ግን አንድም ልጅ አልነበራትም።
3ይህም ሰው በየዓመቱ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ለመስገድና መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ሴሎ ይሄድ ነበር። የእግዚአብሔር ካህናት የሆኑት ሁለቱ የኤሊ ወንዶች ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በዚያ ነበሩ።
4በየዓመቱ ሕልቃና የሚሠዋበት ጊዜ ሲደርስ፥ ለሚስቱ ፍናና፥ ለወንዶችና ሴቶች ልጆችዋ በሙሉ ሁልጊዜ ከመሥዋዕቱ ሥጋ ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር።
5ነገር ግን ሐናን ይወዳት ስለነበር ሁልጊዜም ድርሻዋን ሁለት ዕጥፍ አድርጎ ይሰጣት ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ማኅፀንዋን ዘግቶት ነበር።
6እግዚአብሔር ማኅፀንዋን ዘግቶት ስለነበር ጣውንቷ እርስዋን ለማስመረር ክፉኛ ታስቆጣት ነበር።
7ስለዚህ በየዓመቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከቤተሰብዋ ጋር በምትወጣበት ጊዜ ጣውንቷ ሁልጊዜ ታበሳጫት ነበር። በዚህ ምክንያት ታለቅስ ነበር፤ ምግብም አትበላም ነበር።
8ባሏ ሕልቃና ሁልጊዜ "ሐና ሆይ፥ ለምንድነው የምታለቅሽው? ምግብስ የማትበዪው ለምንድነው? ልብሽ የሚያዝነውስ ለምንድነው? ከዐሥር ወንዶች ልጆች ይልቅ ላንቺ እኔ አልሻልም?" ይላት ነበር።
9ከእነዚህ ወቅቶች በአንዱ፥ በሴሎ መብላታቸውንና መጠጣታቸውን ከጨረሱ በኋላ ሐና ተነሣች። ካህኑ ዔሊ በእግዚአብሔር ቤት መግቢያ በራፍ በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ነበር።
10እርሷም እጅግ አዝና ነበር፤ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች፥ አምርራም አለቀሰች።
11እንዲህ ስትልም ስዕለት ተሳለች፣ "የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ የአገልጋይህን ጉስቁልና ብትመለከትና ብታስበኝ፥ አገልጋይህን ባትረሳኝ፥ ነገር ግን ወንድ ልጅን ብትሰጠኝ፥ እኔም የሕይወት ዘመኑን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ መቼም ቢሆን ጸጉሩ አይላጭም"።
12በእግዚአሔር ፊት ጸሎቷን ቀጥላ እያለች ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር።
13ሐና በልቧ ትናገር ነበር። ከንፈሮችዋ ይንቀሳቀሱ ነበር፥ ድምፅዋ ግን አይሰማም ነበር። ስለዚህ ዔሊ ሰክራለች ብሎ አሰበ።
14ዔሊም "ስካርሽ የሚቆየው እስከ መቼ ነው? ወይንሽን ከአንቺ አርቂው" አላት።
15ሐናም፣ "ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፥ እኔ ልቤ በሐዘን የተጎዳብኝ ሴት ነኝ። ወይን ወይም የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም፥ ነገር ግን ነፍሴን በእግዚአብሔር ፊት እያፈሰስኩ ነው።
16አገልጋይህን እንደ ኃፍረተ ቢስ ሴት አትቁጠረኝ፤ ይህን ያህል ጊዜ የተናገርኩት እጅግ ከበዛው ሐዘኔና ጭንቀቴ የተነሣ ነው" በማለት መለሰችለት።
17ከዚያም ዔሊ፣ "በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ" ብሎ መለሰላት።
18እርሷም፣ "አገልጋይህ በዐይንህ ፊት ሞገስን ላግኝ" አለችው። ከዚያም መንገዷን ሄደች፥ በላችም፤ ከዚያም በኋላ ፊቷ ሐዘንተኛ አልሆነም።
19እነርሱም ማልደው ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፥ ከዚያም ወደ መኖሪያቸው ወደ አርማቴም ተመለሱ። ሕልቃና ከሚስቱ ከሐና ጋር ተኛ፥ እግዚአብሔርም አሰባት።
20ጊዜው ሲደርስም ሐና አረገዘችና ወንድ ልጅ ወለደች። "ከእግዚአብሔር ስለ እርሱ ለምኜ ነበር" ስትል ስሙን ሳሙኤል ብላ ጠራችው።
21ሕልቃናና ቤተ ሰቡ በሙሉ ለእግዚአብሔር ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብና ስዕለታቸውን ለመፈጸም ዳግመኛ ወደ ሴሎ ወጡ።
22ሐና ባሏን "ልጁ ጡት መጥባት እስኪያቆም እኔ አልሄድም፤ ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት እንዲታይና ለዘላለም በዚያ እንዲኖር አመጣዋለሁ" ብላው ስለነበረ አልሄደችም።
23ባሏም ሕልቃና፥ "መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ። ጡት መጥባቱን እስኪያቆም ቆዪ፥ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽና" አላት። ስለዚህ ልጇ ጡት መጥባቱን እስኪያቆም ድረስ በቤት በመቆየት ተንከባከበችው።
24ጡት መጥባቱን ባስቆመችው ጊዜ፥ እርሱን ከሦስት አመት ወይፈን፥ አንድ ኢፍ ዱቄትና አንድ ጠርሙስ ወይን ጋር በሴሎ ወደሚገኘው ወደ እግዚአብሔር ቤት ወሰደችው። ልጁ ገና ሕፃን ነበር።
25ወይፈኑን አረዱት፤ ልጁንም ወደ ዔሊ አመጡት።
26እርሷም፥ "ጌታዬ ሆይ፥ ሕያው እንደመሆንህ፥ እዚህ አጠገብህ ቆማ ወደ እግዚአብሔር የጸለየችው ሴት እኔ ነኝ።
27ስለዚህ ልጅ ጸለይኩኝ፥ እግዚአብሔርም የለመንኩትን ልመና ሰጥቶኛል።
28ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ በሕይወት በሚኖርበት ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል"። እነርሱም በዚያ ለእግዚአብሔር ሰገዱ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።