መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ሳሙኤል 18

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ለሳኦል መናገሩን በጨረሰ ጊዜ የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፥ ዮናታንም እንደ ራሱ ነፍስ አድርጎ ወደደው።
2በዚያ ቀን ሳኦል ዳዊትን ወደ ራሱ አገልግሎት ወሰደው፤ ወደ አባቱ ቤት እንዲመለስ አላሰናበተውም።
3ዮናታን ዳዊትን እንደ ራሱ ነፍስ አድርጎ ስለወደደው በመካከላቸው የወዳጅነት ቃል ኪዳን አደረጉ።
4ዮናታን የለበሰውን ካባ አውልቆ ከጦር ልብሱ ጋር፥ እንዲሁም ሰይፉን፥ ቀስቱንና መታጠቂያውን ለዳዊት ሰጠው።
5ዳዊት ሳኦል ወደሚልከው ቦታ ሁሉ ይሄድ ነበር፥ ይከናወንለትም ነበር። ሳኦልም በተዋጊዎቹ ላይ ሾመው። ይህም በሕዝቡ ዓይን ሁሉ ደግሞም በሳኦል አገልጋዮች ፊት ደስ የሚያሰኝ ሆነ።
6ፍልስጥኤማውያንን ድል አድርገው ወደ መኖሪያቸው በመመለስ ላይ እያሉ ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ንጉሥ ሳኦልን ለመገናኘት፥ ሴቶች በከበሮና በሙዚቃ መሳሪያዎች በደስታ እየዘመሩና እየጨፈሩ መጡ።
7ሴቶቹም ሲጫወቱ እየተቀባበሉ ይዘምሩ ነበር፤ እነርሱም፥ "ሳኦል ሺዎችን ገደል፥ ዳዊትም ዐሥር ሺዎችን ገደለ" እያሉ ዘመሩ።
8ሳኦል እጅግ ተቆጣ፥ ይህም መዝሙር አስከፋው። እርሱም፥ "ለዳዊት ዐሥር ሺዎች አሉ፥ ለእኔ ግን ሺዎችን ብቻ። ታዲያ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረው?" አለ።
9ሳኦል ከዚያን ቀን ጀምሮ ዳዊትን በጥርጣሬ ዐይን ተመለከተው።
10በቀጣዩ ቀን በሳኦል ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ መጣበት። እርሱም በቤት ውስጥ እንደ ዕብድ ይለፈልፍ ነበር። ስለዚህ ዳዊት በየቀኑ ያደርግ እንደነበረው በገናውን ይደረድር ነበር። ሳኦልም በእጁ ጦር ይዞ ነበር።
11ሳኦል፥ "ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ" ብሎ በማሰብ ጦሩን ወረወረበት። ነገር ግን ዳዊት ከሳኦል ፊት ሁለት ጊዜ እንዲህ ባለ መንገድ አመለጠ።
12እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንጂ ከእርሱ ጋር ስላልነበረ ሳኦል ዳዊትን ፈራው።
13ስለዚህ ሳኦል ከፊቱ አራቀው፥ ሻለቃም አድርጎ ሾመው። በዚህ ሁኔታ ዳዊት በሕዝቡ ፊት ይወጣና ይገባ ነበር።
14እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለነበረ ዳዊት የሚሠራው ሁሉ ይከናወንለት ነበር።
15እንደ ተከናወነለት ሳኦል ባየ ጊዜ እጅግ ፈራው።
16ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱት።
17ከዚያም ሳኦል ዳዊትን፥ "ትልቋ ልጄ ሜሮብ ይቹት። እርሷን እድርልሃለሁ። ብቻ ጎብዝልኝ፥ የእግዚአብሔርን ጦርነቶችም ተዋጋ" አለው። ሳኦል፥ "እጄ በእርሱ ላይ አይሁን፥ ነገር ግን የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ ይሁን" ብሎ አስቦአልና።
18ዳዊትም ሳኦልን፥ "የንጉሥ አማች ለመሆን እኔ ማነኝ? ሕይወቴ ወይም የአባቴ ቤተ ሰብ በእስራኤል ውስጥ ምንድነው?" አለው።
19ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤድሪኤል ተዳረች።
20ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደችው። ለሳኦል ነገሩት፥ ይህም እርሱን ደስ አሰኘው።
21ከዚያም ሳኦል፥ "ወጥመድ እንድትሆነውና የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ እንድትሆን እርሷን እድርለታለሁ" ብሎ አሰበ። ስለዚህ ሳኦል ዳዊትን ለሁለተኛ ጊዜ፥ "አማቼ ትሆናለህ" አለው።
22ሳኦል አገልጋዮቹን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፥ "ዳዊትን በምስጢር እንዲህ በሉት፥ 'አስተውል፥ ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፥ አገልጋዮቹም ሁሉ ይወዱሃል። እንግዲያው የንጉሡ አማች ሁን'"
23ስለዚህ የሳኦል አገልጋዮች ይህንን ቃል ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም፥ "እኔ ድሃና ብዙም የማልታወቅ ሰው ሆኜ እያለሁ የንጉሥ አማች እንድሆን ማሰባችሁ ጉዳዩ እንዴት ቀልሎ ታያችሁ?" አላቸው።
24የሳኦል አገልጋዮችም ዳዊት የተናገረውን ቃል ነገሩት።
25ሳኦልም፥ "ለዳዊት እንዲህ ትሉታላችሁ፥ 'የንጉሡን ጠላቶች ለመበቀል ከአንድ መቶ የፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ብቻ በቀር ንጉሡ ምንም ጥሎሽ አይፈልግም"። ዳዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲወድቅ ለማድረግ ሳኦል አሰበ።
26አገልጋዮቹ ይህንን ቃል ለዳዊት በነገሩት ጊዜ የንጉሡ አማች መሆን ዳዊትን ደስ አሰኘው።
27እነዚያ ቀናት ከማብቃታቸው በፊት፥ ዳዊት ከሰዎቹ ጋር ሄዶ ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደለ። ዳዊት የንጉሡ አማች ይሆን ዘንድ ሸለፈቶቹን አመጣ፥ ለንጉሡም ሙሉውን ቁጥር አስረከቡ። ስለዚህ ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ዳረለት።
28እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደነበረ ሳኦል አየ፥ ዐወቀም። የሳኦል ልጅ ሜልኮልም ወደደችው።
29ሳኦልም ዳዊትን የበለጠ ፈራው። ሳኦል የዳዊት ጠላቱ እንደሆነ ቀጠለ።
30ከዚያም የፍልስጥኤም ልዑላን ብዙ ጊዜ ያደርጉት እንደነበረው ለጦርነት መጡ፥ ዳዊት ከሳኦል አገልጋዮች ሁሉ በበለጠ ሁኔታ የተሳካለት ሆነ፥ በመሆኑም ስሙ እጅግ የተከበረ ሆነ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።