መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ሳሙኤል 17

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ፍልስጥኤማውያን ሠራዊታቸውን ለውጊያ አዘጋጁ። እነርሱም የይሁዳ በሆነችው በሰኮት ተሰበሰቡ። በሰኮትና በዓዜቃ መካከል በምትገኘው በኤፌስደሚምም ሰፈሩ።
2ሳኦልና የእስራኤል ሰዎችም ተሰብስበው በኤላ ሸለቆ ሰፈሩ፥ ፍልስጥኤማውያንን ለመግጠምም ስፍራቸውን ያዙ።
3ፍልስጥኤማውያን በአንደኛው ወገን ተራራ ላይ ቆሙ፥ በዚህኛው ወገን ባለው ተራራ ላይ እስራኤላውያኑ ቆሙ፥ በመካከላቸውም ሸለቆ ነበር።
4የጌት ሰው ጎልያድ የሚባል አንድ ጀግና ከፍልስጥኤማውያን የጦር ሰፈር ወጣ፥ ቁመቱም ስድስት ክንድ ከስንዝር ነበር።
5በራሱ ላይ ከነሐስ የተሠራ የራስ ቁር ደፍቶ፥ ጥሩርም ለብሶ ነበር። ጥሩሩም አምስት ሺህ የነሐስ ሰቅል ይመዝን ነበር።
6በእግሮቹ ላይ የነሐስ ገምባሌዎች አድርጎ ነበር፥ በትከሻዎቹም መሓል ቀለል ያለ የነሐስ ጦር ነበር።
7የጦሩ ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ ወፍራም ነበር። የጦሩ ጫፍ ስድስት መቶ የብረት ሰቅል ይመዝን ነበር። ጋሻ ጃግሬው በፊቱ ሄደ።
8እርሱም ተነሥቶ በእስራኤል ሠልፈኞች ላይ እንዲህ በማለት ጮኸ፥ “ለውጊያ የተሰለፋችሁት ለምንድነው? እኔ ፍልስጥኤማዊ፥ እናንተ የሳኦል አገልጋዮች አይደላችሁም? ለራሳችሁ አንድ ሰው ምረጡና ወደ እኔ ይውረድ።
9እርሱ ሊዋጋኝ ቢችልና ቢገድለኝ እኛ አገልጋዮቻችሁ እንሆናለን። ነገር ግን ባሸንፈውና ብገድለው እናንተ አገልጋዮቻችን በመሆን ታገለግሉናላችሁ።”
10ፍልስጥኤማዊው ደገመና፥ “ዛሬ የእስራኤልን ሰልፈኞች እገዳደራቸዋለሁ። እንድንዋጋ አንድ ሰው ስጡኝ" አለ።
11ፍልስጥኤማዊው የተናገረውን ሳኦልና እስራኤላውያን ሁሉ በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፥ ተስፋም ቆረጡ።
12ዳዊት በይሁዳ የሚኖረው የቤተ ልሔም ኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይ ስምንት ወንዶች ልጆች ነበሩት። በሳኦል ዘመን እሴይ በዕድሜው ያረጀና ከወንዶቹ ሁሉ በዕድሜ የገፋ ሰው ነበር።
13የእሴይ ሦስቱ ታላላቅ ልጆች ሳኦልን ተከትለው ወደ ጦርነቱ ሄደው ነበር። ወደ ጦርነት የሄዱት የሦስቱ ወንዶች ልጆች ስም፥ የመጀመሪያው ልጅ ኤልያብ፥ ተከታዩ አሚናዳብና ሦስተኛው ሣማ ይባሉ ነበር።
14ዳዊት የሁሉም ታናሽ ነበር። ትልልቆቹ ሦስቱ ሳኦልን ተከተሉት።
15ዳዊት በሳኦል ሠራዊትና በቤተ ልሔም የሚገኙትን የአባቱን በጎች በመጠበቅ ተግባር ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ናበር።
16ፍልስጥኤማዊው ኃያል ሰው ለአርባ ቀናት በየጠዋቱና በየምሽቱ ለጦርነት ዝግጁ መሆኑን ለማሳየት ይቀርብ ነበር።
17ከዚያም እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፥”ከዚህ ከተጠበሰው እሸት ዐሥር ኪሎና እነዚህን ዐሥር ዳቦዎች በጦር ሰፈሩ ውስጥ ላሉት ወንድሞችህ ፈጥነህ ውሰድላቸው።
18በተጨማሪም እነዚህን ዐሥር የአይብ ጥፍጥፎች ለሻለቃቸው ስጠው። ወንድሞችህ ያሉበትን ሁኔታ ተመልከትና ደኅና ስለመሆናቸው ማረጋገጫ አምጣልኝ።
19ወንድሞችህ ከሳኦልና ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋር ፍልስጥኤማውያንን እየተዋጉ በኤላ ሸለቆ ናቸው።“
20ዳዊት ማልዶ ተነሣና በጎቹን ለእረኛ ዐደራ ሰጠ። እርሱም እሴይ እንዳዘዘው የወንድሞቹን ስንቅ ይዞ ሄደ። ሠራዊቱ ወደ ውጊያው ግምባር እየፎከረ በመውጣት ላይ እያለ ዳዊት ወደ ጦር ሰፈሩ ደረሰ።
21እስራኤላውያንና ፍልስጥኤማውያን፥ ሠራዊት በሠራዊት ላይ ለውጊያ ተሰለፉ።
22ዳዊት የያዘውን ዕቃ ለስንቅ ጠባቂው ዐደራ ሰጥቶ ወደ ሠራዊቱ በመሮጥ ለወንድሞቹ ሰላምታ አቀረበ።
23ከእነርሱ ጋር እየተነጋገረ እያለ ጎልያድ ተብሎ የሚጠራው፥ ከጌት የመጣው ፍልስጥኤማዊ ከሰልፈኞች መካከል ወጥቶ የቀድሞውን የሚመስል ቃል ተናገረ። ዳዊትም ሰማቸው።
24የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ሰውዬውን ባዩት ጊዜ፥ ከእርሱ ሸሹ፥ እጅግም ፈርተውት ነበር።
25የእስራኤልም ሰዎች፥ "ይህን የሚወጣውን ሰው አያችሁት? እስራኤልን ለመገዳደር ነው የመጣው። እርሱን የሚገድለውን ሰው ንጉሡ እጅግ ያበለጽገዋል፥ ልጁን ይድርለታል፥ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ውስጥ ከግብር ነጻ ያደርጋቸዋል" ይባባሉ ነበር።
26ዳዊትም በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፥ "ይህንን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድልና ከእስራኤል ኀፍረትን ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ሊንቅ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ሆነና ነው?" አላቸው።
27ከዚያም ሰዎቹ ቀደም ሲል የተናገሩትን ደግመው፥ "ስለዚህ እርሱን ለሚገድለው የሚደረግለት ይህ ነው" አሉት።
28ዳዊት ከሰዎቹ ጋር ሲነጋገር የሁሉ ታላቅ የሆነው ወንድምየው ኤልያብ ሰማው። ኤልያብም በዳዊት ላይ ቁጣው ነድዶ፥ "ወደዚህ የወረድከው ለምንድነው? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ውስጥ ለማን ተውካቸው? እኔ ትዕቢትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁ፤ ወደዚህ የወረድከው ውጊያውን ለማየት ነውና" አለው።
29ዳዊትም፥ "አሁን እኔ ምን አደረኩ? እንዲያው መጠየቄ ብቻ አልነበረም?" አለው።
30ከእርሱ ወደ ሌላው ዞር ብሎ በተመሳሳይ መንገድ ተናገረ። ሰዎቹም የቀድሞውን የሚመስል መልስ ሰጡት።
31ዳዊት የተናገረው ቃል በተሰማ ጊዜ፥ ወታደሮች ቃሉን ለሳኦል ነገሩት፥ እርሱም ዳዊትን አስጠራው።
32ከዚያም ዳዊት ሳኦልን፥ "በዚያ ፍልስጥኤማዊ ምክንያት የማንም ልብ አይውደቅ፤ አገልጋይህ ሄዶ ከፍልስጥኤማዊው ጋር ይዋጋል" አለው።
33ሳኦልም ዳዊትን፥ "አንተ ከዚህ ፍልስጥኤማዊ ጋር ለመዋጋት መሄድ አትችልም፤ አንተ ገና ልጅ ነህ፥ እርሱ ደግሞ ከወጣትነቱ ጀምሮ ተዋጊ ነው" አለው።
34ዳዊት ግን ሳኦልን፥ "አገልጋይህ የአባቴን በጎች እጠብቅ ነበር። አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው ጠቦት በሚወስድበት ጊዜ
35በኋላው ተከትዬ እመታውና ከአፉ አስጠለው ነበር። ሊያጠቃኝ በተነሣብኝ ጊዜም ጉሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር።
36አገልጋይህ አንበሳና ድብ ገድያለሁ። የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ስለተገዳደረ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል" አለው።
37ዳዊትም፥ "እግዚአብሔር ከአንበሳና ከድብ መዳፍ አድኖኛል። ከዚህም ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል" አለው።
38ከዚያም ሳኦል ዳዊትን፥ "ሂድ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን" አለው። ሳኦል የራሱን የጦር መሣሪያ ለዳዊት አስታጠቀው። በራሱ ላይ የነሐስ ቁር ደፋለት፥ ጥሩርም አለበሰው።
39ዳዊትም ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጠቀው። ነገር ግን አልተለማመደውምና ለመራመድ አቃተው። ከዚያም ዳዊት ሳኦልን፥ "አልተለማመድኳቸውምና በእነዚህ መዋጋት አልችልም" አለው። ስለዚህ ዳዊት ከላዩ ላይ አወለቃቸው።
40በትሩን በእጁ ያዘ፥ ከጅረቱም አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች መርጦ በእረኛ ኮሮጆው ውስጥ ጨመራቸው። ፍልስጥኤማዊውን በሚቀርብበት ጊዜ ወንጭፉን ይዞ ነበር።
41ፍልስጥኤማዊውም በፊት ለፊቱ ከሚሄደው ጋሻ ጃግሬው ጋር መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ።
42ፍልስጥኤማዊው ዙሪያውን ሲመለከት ዳዊትን ባየው ጊዜ ቀይ፥ መልከ መልካም ገጽታ ያለው ትንሽ ልጅ ብቻ ስለነበረ ናቀው።
43ፍልስጥኤማዊው ዳዊትን፥ "በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝ?" አለው። ፍልስጥኤማዊውም በአማልክቶቹ ስም ዳዊትን ረገመው።
44ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ "ወደ እኔ ና፥ እኔም ሥጋህን ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ" አለው።
45ዳዊትም ለፍልስጥኤማዊው እንዲህ ሲል መለሰለት፥ "አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ። እኔ ግን አንተ ባቃለልከው፥ የእስራኤል ሠራዊት አምላክ በሆነው፥ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።
46ዛሬ እግዚአብሔር በአንተ ላይ ድልን ይሰጠኛል፥ እገድልሃለሁ፥ ራስህንም ከሰውነትህ ላይ አነሣዋለሁ። ዛሬ የፍልስጥኤምን ሠራዊት ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፥ ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል አምላክ እንዳለ እንዲያውቅና
47በዚህ የተሰበሰበው ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍ ወይም በጦር ድልን እንደማይሰጥ እንዲያውቁ ነው። ጦርነቱ የእግዚአብሔር ነውና እናንተንም በእጃችን ላይ አሳልፎ ይሰጣችኋል።"
48ፍልስጥኤማዊው ተነሥቶ ዳዊትን በቀረበው ጊዜ ዳዊት ሊገናኘው ወደ ጠላት ጦር በፍጥነት ሮጠ።
49ዳዊት እጁን ወደ ኮሮጆው አስገብቶ አንድ ድንጋይ ከዚያ ወሰደ፥ ወነጨፈውና የፍልስጥኤማዊውን ግንባር መታው። ድንጋዩም በፍልስጥኤማዊው ግንባር ውስጥ ጠልቆ ገባ፥ እርሱም በግንባሩ በምድር ላይ ተደፋ።
50ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው። ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለው። በዳዊት እጅ ሰይፍ አልነበረም።
51ከዚያም ዳዊት ሮጠና በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፥ ከእርሱም ሰይፉን ወሰደ፥ ከሰገባው አወጣና ገደለው፥ በእርሱም ራሱን ቆርጦ አነሣው። ፍልስጥኤማውያን ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ።
52ከዚያም የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች እልል እያሉ ተነሥተው ፍልስጥኤማውያንን እስከ ሸለቆውና እስከ ኤቅሮን መግቢያ ድረስ አሳደዷቸው። የፍልስጥኤማውያኑ ሬሳ ከሸዓራይም እስከ ጌትና ዔቅሮን ድረስ በየመንገዱ ወድቆ ነበር።
53የእስራኤል ሰዎች ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሱና የጦር ሰፈራቸውን በዘበዙ።
54ዳዊት የፍልስጥኤማዊውን ራስ ወስደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጣው፥ የጦር መሣሪያውን ግን በድንኳኑ ውስጥ አኖረው።
55ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ለመጋጠም ሲሄድ ሳኦል ባየው ጊዜ፥ የሰራዊቱን አዛዥ አበኔርን፥ "አንተ አበኔር፥ ይህ ወጣት የማን ልጅ ነው?" አለው። አበኔርም፥ "ንጉሥ ሆይ፥ በሕያውነትህ እምላለሁ፥ አላውቅም" አለው።
56ንጉሡም፥ "የማን ልጅ እንደሆነ ምናልባት ሊያውቁት የሚችሉትን ጠይቅ" አለው።
57ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ አበኔር ወሰደው፥ የፍልስጥኤማዊውን ራስ በእጁ እንደያዘ ወደ ሳኦል አመጣው።
58ሳኦልም፥ "አንተ ወጣት፥ የማን ልጅ ነህ?" አለው። ዳዊትም፥ "እኔ የቤተ ልሔማዊው የአገልጋይህ የእሴይ ልጅ ነኝ" ብሎ መለሰለት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።