1እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፥ “በእስራኤል ንጉሥ እንዳይሆን ለናቅኩት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? በወንዶች ልጆቹ መካከል ለራሴ ንጉሥ የሚሆነውን መርጫለሁና ወደ ቤተ ልሔማዊው ወደ እሴይ እልክሃለሁ። የዘይት መያዣ ቀንድህን በዘይት ሞልተህ ሂድ” አለው።
2ሳሙኤልም፥ “እንዴት መሄድ እችላለሁ? ሳኦል ከሰማ ይገድለኛል” አለ። እግዚአብሔርም፥ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፥ 'ለእግዚአብሔር ልሠዋ መጥቻለሁ' በል።
3እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፥ እኔም የምታደርገውን አሳይሃለሁ። የምነግርህንም እርሱን ትቀባልኛለህ” አለው።
4ሳሙኤልም እግዚአብሔር እንደተናገረው አደረገ፥ ወደ ቤተ ልሔምም ሄደ። የከተማይቱም ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡና፥ “በሰላም ነው የመጣኸው?” አሉት።
5እርሱም፥ “በሰላም ነው። ለእግዚአብሔር ልሠዋ መጥቻለሁ። ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሱና ከእኔ ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ”አላቸው። እሴይንና ወንዶች ልጆቹንም ቀደሳቸው፥ ወደ መሥዋዕቱም ጠራቸው።
6እነርሱ በመጡ ጊዜም፥ ወደ ኤልያብ ተመልክቶ እግዚአብሔር የሚቀባው በእርግጥ በፊቱ ቆሟል ብሎ በልቡ አሰበ።
7ነገር ግን እግዚአብሔር ሳሙኤልን፥ "እኔ ንቄዋለሁና ውጫዊ ገጽታውን ወይም የቁመቱን ዘለግታ አትመልከት። እግዚአብሔር ሰው እንደሚያይ አያይምና፤ ሰው ውጫዊ ገጽታን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል" አለው።
8ከዚያም እሴይ አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገው። ሳሙኤልም፥ "እግዚአብሔር ይኸኛውንም አልመረጠውም“ አለ።
9ከዚያም እሴይ ሳማን አሳለፈው። ሳሙኤልም፥ "እግዚአብሔር ይኸኛውንም አልመረጠውም“ አለ።
10እሴይ ሰባቱን ወንዶች ልጆቹን በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረጋቸው። ሳሙኤልም እሴይን፥”እግዚአብሔር ከእነዚህ አንዳቸውንም አልመረጠም“ አለው።
11ሳሙኤልም እሴይን፥”ወንዶቹ ልጆችህ እነዚህ ብቻ ናቸው? “ አለው። እርሱም፥”የሁሉ ታናሽ የሆነው ገና ቀርቷል፥ እርሱ ግን በጎች እየጠበቀ ነው" ብሎ መለሰ። ሳሙኤልም እሴይን፥ "ልከህ አስመጣው፤ እርሱ እዚህ እስኪመጣ ድረስ አንቀመጥምና" አለው።
12እሴይም ልኮ አስመጣው። በመጣ ጊዜም ልጁ ቀይ፥ ዐይኖቹ የተዋቡና መልከ መልካም ገጽታ ነበረው። እግዚአብሔርም፥ "ያ ሰው እርሱ ነውና ተነሣ፤ ቀባውም" አለው።
13ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ አንሥቶ በወንድሞቹ መካከል እርሱን ቀባው። ከዚያን ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ በኃይል መጣበት። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ።
14የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ተለየ፥ በምትኩም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ክፉ መንፈስ አሠቃየው።
15የሳኦል አገልጋዮችም፥ "ተመልከት፥ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ እያሠቃየህ ነው።
16ደህና አድርጎ በገና መደርደር የሚችል ሰው እንዲፈልጉ ጌታችን በፊቱ ያሉትን አገልጋዮቹን ይዘዝ። ከዚያም ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ እርሱ ይጫወትልሃል፥ አንተም ደኅና ትሆናለህ" አሉት።
17ሳኦልም አገልጋዮቹን፥ "በገና በደንብ መደርደር የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ" አላቸው።
18ከዚያም ከወጣቶቹ አንዱ እንዲህ ሲል መለሰ፥ "ደኅና አድርጎ በገና መደርደር የሚችለውን፥ ጽኑ፥ ኃያል፥ ተዋጊ፥ በንግግሩ ጠንቃቃና መልከ መልካም የሆነውን የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው።"
19ስለዚህ ሳኦል መልዕክተኞችን ወደ እሴይ ልኮ፥ "ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ" አለው።
20እሴይም እንጀራና ወይን ጠጅ የተሞላ አቁማዳ የተጫነበትን አህያ፥ ከፍየል ጠቦት ጋር አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው።
21ከዚያም ዳዊት ወደ ሳኦል መጣና አገልግሎቱን መስጠት ጀመረ። ሳኦል እጅግ ወደደው፥ ዳዊትም ጋሻ ጃግሬው ሆነ።
22ሳኦልም፥ "በዐይኔ ፊት ሞገስን አግኝቷልና ዳዊት በፊቴ እንዲቆም ፈቃድህ ይሁን“ ብሎ ወደ እሴይ ላከ።
23በሳኦል ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ዳዊት በገና አንሥቶ ይደረድርለት ነበር። ስለዚህ ሳኦል ይታደስና ደኅና ይሆን ነበር፥ ክፉውም መንፈስ ከእርሱ ይርቅ ነበር።