1ሳሙኤልም ሳኦልን እንዲህ አለው፥”እግዚአብሔር በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ እንድቀባህ ላከኝ። አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስማ።
2የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሚለው እንዲህ ነው፥ 'እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ አማሌቅ እየተቃወመ በመንገዱ ላይ ያደረገበትን አስታውሻለሁ።
3አሁንም ሂድና አማሌቅን ምታ፥ ያላቸውን ሁሉ ፈጽመህ ደምስስ። አትራራላቸው፥ ወንድና ሴቱን፥ ልጅና ሕፃኑን፥ በሬና በጉን፥ ግመልና አህያውን ግደል።"
4ሳኦል ሕዝቡን በጥላኢም ከተማ ሰብስቦ ቆጠራቸው፤ እነርሱም ሁለት መቶ ሺህ እግረኞችና ዐሥር ሺህ የይሁዳ ሰዎች ነበሩ።
5ከዚያም ሳኦል ወደ አማሌቅ ከተማ መጥቶ በሸለቆው ውስጥ አደፈጠ።
6ከዚያም ሳኦል ቄናውያንን፥ "ከግብፅ በመጡ ጊዜ ለእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ደግነትን አሳይታችኋልና ከእነርሱ ጋር እንዳላጠፋችሁ፥ ከአማሌቃውያን መካከል ተለይታችሁ ውጡና ሂዱ" አላቸው። ስለዚህ ቄናውያን ከአማሌቃውያን ተለይተው ሄዱ።
7ሳኦልም አማሌቃውያንን ከኤውላጥ ጀምሮ ከግብፅ በስተምሥራቅ እስካለችው እስከ ሱር ድረስ መታቸው።
8የአማሌቃውያኑን ንጉሥ አጋግን ከነሕይወቱ ያዘው፤ ሕዝቡን ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋቸው።
9ነገር ግን ሳኦልና ሕዝቡ አጋግን፥ እንዲሁም ምርጥ የሆኑትን በጎች፥ በሬዎች፥ የሰቡትን ጥጆችና የበግ ጠቦቶች በሕይወት ተዉአቸው። መልካም የሆነውን ሁሉ አላጠፉም። የተናቀውንና ዋጋ ቢስ የሆነውን ነገር ሁሉ ግን ፈጽመው ደመሰሱ።
10ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሳሙኤል መጣ፥
11"እኔን ከመከተል ስለተመለሰና ያዘዝኩትንም ስላልፈጸመ ሳኦልን በማንገሤ ተጸጽቻለሁ"። ሳሙኤልም ተቆጣ፤ ሌሊቱን በሙሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጮህ አደረ።
12ሳሙኤልም ሳኦልን በጠዋት ለመገናኘት ማልዶ ተነሣ። ለሳሙኤልም፥ "ሳኦል ወደ ቀርሜሎስ መጥቶ ለራሱ ሐውልት አቆመ፥ ከዚያም ተመልሶ ወደ ጌልገላ ወረደ" ብለው ነገሩት።
13ከዚያም ሳሙኤል ወደ ሳኦል መጣ፥ ሳኦልም፥ "አንተ በእግዚአብሔር የተባረክህ ነህ! የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ፈጽሜአለሁ" አለው።
14ሳሙኤልም፥ "ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ድምፅና የበሬዎች ግሣት ምንድነው?" አለው።
15ሳኦልም፥ "ከአማሌቃውያኑ ያመጧቸው ናቸው። ሕዝቡ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ለመሠዋት ምርጥ የሆኑትን በጎችና በሬዎች በሕይወት አስቀሯቸው። የቀሩትን ፈጽመን አጥፍተናል" ብሎ መለሰለት።
16ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልን፥ "አድምጠኝ፥ በዛሬው ሌሊት እግዚአብሔር የነገረኝን እነግርሃለሁ" አለው። ሳኦልም፥ "ተናገር!" አለው።
17ሳሙኤልም እንዲህ አለው፥ "በራስህ ግምት ታናሽ ብትሆንም በእስራኤል ነገዶች ላይ አለቃ ተደረግህ። እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ ቀባህ፤
18እግዚአብሔርም፥ 'ሂድና ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፥ እስኪጠፉም ድረስ ተዋጋቸው' ብሎ በመንገድህ ልኮህ ነበር።
19ታዲያ የእግዚአብሔርን ድምፅ ያልታዘዝከው ለምንድነው? ከዚያ ይልቅ ግን ከምርኮው በመውሰድ በእግዚአብሔር ፊት ክፋትን አደረግህ።"
20ሳኦልም ሳሙኤልን፥ "የእግዚአብሔርን ድምፅ በትክክል ታዝዣለሁ፥ እግዚአብሔር በላከኝም መንገድ ሄጃለሁ። የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን ማርኬዋለሁ፥ አማሌቃውያንንም በሙሉ ፈጽሜ ደምስሻለሁ።
21ሕዝቡ ግን ከምርኮው ላይ ጥቂት በጎችንና በሬዎችን፥ ሊጠፉም የነበሩ ምርጥ ነገሮችን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በጌልገላ ሊሠዉአቸው ወሰዱ" አለው።
22ሳሙኤልም፥ "የእግዚአብሔርን ድምፅ ከመታዘዝ የበለጠ በሚቃጠል መባና መሥዋዕት እግዚአብሔር ደስ ይሰኛል? ከመሥዋዕት መታዘዝ ይሻላል፥ ከአውራ በግ ስብም መስማት ይሻላል።
23እምቢተኝነት እንደ ምዋርተኝነት ኃጢአት ነው፥ እልኸኝነትም እንደ አመጸኝነትና እንደ ክፋት ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እርሱም ደግሞ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል“ አለው።
24ከዚያም ሳኦል ሳሙኤልን፥”ኃጢአትን ሠርቻለሁ፤ ሕዝቡን ስለፈራሁና ቃላቸውን ስለታዘዝኩ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝና የአንተን ቃል ተላልፌአለሁ።
25አሁንም እባክህን ኃጢአቴን ይቅር በለኝ፥ ለእግዚአብሔር እንድሰግድም ከእኔ ጋር ተመለስ“ አለው።
26ሳሙኤልም ሳኦልን፥”ከአንተ ጋር አልመለስም፤ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና አንተም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን እግዚአብሔር ንቆሃል" አለው።
27ሳሙኤል ለመሄድ ዘወር ባለ ጊዜ፥ ሳኦል የልብሱን ጫፍ ያዘ፥ እርሱም ተቀደደ።
28ሳሙኤልም፥ "እግዚአብሔር ዛሬ የእስራኤልን መንግሥት ከአንተ ቀደደው፥ ከአንተ ለሚሻለው ለጎረቤትህም አሳልፎ ሰጠው።
29ደግሞም የእስራኤል ኃይል አይዋሽም፥ አሳቡንም አይለውጥም፥ እርሱ አሳቡን መለወጥ ይችል ዘንድ ሰው አይደለምና“ አለው።
30ከዚያም ሳኦል፥”ኃጢአትን አድርጌአለሁ። አሁን ግን እባክህ በሕዝቤ ሽማግሌዎችና በእስራኤል ፊት አክብረኝ። ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንድሰግድ ከእኔ ጋር ተመለስ“ አለው።
31ስለዚህ ሳሙኤል ከሳኦል ኋላ ተመለሰ፥ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ።
32ከዚያም ሳሙኤል፥”የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ“ አለ። አጋግ በሠንሠለት አንደታሠረ ወደ እርሱ መጣና፥”ለካስ ሞት እንዲህ መራራ ነው“ አለ።
33ሳሙኤልም፥”ሰይፍህ እናቶችን ልጅ ዐልባ እንዳደረጋቸው አሁን እናትህ በሴቶች መካከል ልጅ ዐልባ ትሆናለች“ ብሎ መለሰለት። ከዚያም ሳሙኤል አጋግን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ ቆራረጠው።
34ሳሙኤል ወደ ራማ ሄደ፥ ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ሳኦል ጊብዓ ሄደ።
35ሳሙኤል እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ሳኦልን አላየውም፥ ለሳኦልም አለቀሰለት። እግዚአብሔርም ሳኦልን በእስራኤል ላይ በማንገሡ አዘነ።