1አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣቱን ጋሻ ጃግሬውን፥”ና፥ በፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ላይ በሌላ አቅጣጫ እንሂድባቸው“ አለው። ለአባቱ ግን አልነገረውም።
2ሳኦል መጌዶን በሚባል በጊብዓ ዳርቻ በሮማኑ ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር።
3እርሱም በሴሎ የእግዚአብሔር ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ የሆነው፥ ኤፉድ ይለብስ የነበረውን አኪያን ጨምሮ ስድስት መቶ ያህል ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ። ዮናታን መሄዱን ሕዝቡ አላወቀም ነበር።
4ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያኑ ጦር ሰፈር አቋርጦ ለመሄድ ባሰበባቸው በመተላለፊያዎቹ መካከል በግራና በቀኙ በኩል ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ። የአንደኛው ሾጣጣ ድንጋይ ስም ቦጼጽ ሲሆን የሁለተኛው ስም ሴኔ ነበር።
5አንደኛው ቀጥ ያለው ድንጋይ የቆመው በስተሰሜን በሚክማስ ፊት ለፊት ሲሆን ሌላኛው በጊብዓ ፊት ለፊት በስተደቡብ ነበር።
6ዮናታንም ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፥ "ና፥ ወደእነዚህ ወዳልተገረዙት ጦር ሰፈር እንሻገር። እግዚአብሔር በብዙ ወይም በጥቂት ሰዎች ከማዳን ሊከለክለው የሚችል ነገር የለምና፥ ምናልባት እግዚአብሔር ይሠራልን ይሆናል" አለው።
7ጋሻ ጃግሬውም፥ "በልብህ ያለውን ሁሉ አድርግ። ወደፊት ቀጥል፥ ተመልከት፥ የምታዝዘኝን ሁሉ ለመፈጸም ከአንተ ጋር ነኝ" ብሎ መለሰለት።
8ከዚያም ዮናታን እንዲህ አለው፥ "ወደ እነርሱ ተሻግረን እንታያቸዋለን።
9እነርሱም፥ 'ወደ እናንተ እስክንመጣ እዚያው ቆዩ' ካሉን በስፍራችን እንቆያለን፥ ወደ እነርሱም አንሻገርም።
10ነገር ግን፥ 'ወደ እኛ ውጡ' ብለው ቢመልሱልን እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናልና ወደ እነርሱ እንሻገራለን።”
11ስለዚህ ሁለቱም ራሳቸውን ለፍልስጥኤማውያን ጦር ገለጡ። ፍልስጥኤማውያኑም፥ “ተመልከቱ፥ ዕብራውያኑ ከተደበቁባቸው ጉድጓዶች ወጥተው እየመጡ ነው" ተባባሉ።
12ከዚያም የጦር ሰፈሩ ሰዎች ወደ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በመጣራት፥”ወደ እኛ ውጡ፥ አንድ ነገርም እናሳያችኋለን" አሏቸው። ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፥ “እግዚአብሔር በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጥቷቸዋልና ተከተለኝ" አለው።
13ዮናታን በእጁና በእግሩ ተንጠላጥሎ ወጣ፥ ጋሻ ጃግሬውም ከኋላው ተከተለው። ፍልስጥኤማውያኑ በዮናታን ተገደሉ፥ ጋሻ ጃግሬውም ከኋላው ተከትሎ ጥቂቶቹን ገደለ።
14ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በፈጸሙት በዚያ የመጀመሪያ ጥቃት አንድ ጥማድ በሬ ሊያርሰው በሚችለው የመሬት ስፋት ላይ ሃያ ያህል ሰዎችን ገደሉ።
15በጦር ሰፈሩ፥ በእርሻውና በሕዝቡ መካከል ሽብር ሆነ። የጦር ሰፈሩና ወራሪዎቹም እንኳን ተሸበሩ። ምድሪቱ ተንቀጠቀጠች፥ ታላቅ ሽብርም ሆነ።
16በብንያም ጊብዓ የነበሩ የሳኦል ጠባቂዎች፥ የፍልስጥኤም ወታደሮች ሲበተኑና ወዲያና ወዲህ ሲራወጡ ተመለከቱ።
17ከዚያም ሳኦል ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሰዎች፥”ቁጠሩና ከእኛ የጎደለ ማን እንደሆነ ዕወቁ“ አላቸው። በቆጠሩ ጊዜም ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው ታጡ።
18ሳኦልም አኪያን፥ "የእግዚአብሔርን ኤፉድ ወደዚህ አምጣው" አለው። በዚያ ቀን አኪያ ኤፉድ ለብሶ ከእስራኤል ወታደሮች ጋር ነበር።
19ሳኦል ከካህኑ ጋር በመነጋገር ላይ እያለ በፍልስጥኤማውያን የጦር ሰፈር የነበረው ሁከት መጨመሩን ቀጠለ። ሳኦልም ካህኑን፥ "እጅህን መልስ" አለው።
20ሳኦልና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ በሩጫ ወደ ጦርነቱ ሄዱ። የእያንዳንዱ ፍልስጥኤማዊ ሰይፍ በራሱ ዜጋ ላይ ነበር፥ ታላቅ ግራ መጋባት ውስጥ ነበሩ።
21ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጋር የነበሩና አብረዋቸው ወደ ጦር ሰፈሩ የገቡት ዕብራውያን እነርሱም እንኳን አሁን ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ከነበሩት እስራኤላውያን ጋር ተባበሩ።
22በኤፍሬም አቅራቢያ በኮረብታዎቹ ውስጥ የተደበቁ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ፍልስጥኤማውያን መሸሻቸውን በሰሙ ጊዜ እነርሱም እንኳን ለውጊያ በኋላቸው አሳደዷቸው።
23ስለዚህ እግዚአብሔር በዚያን ቀን እስራኤልን አዳነ፥ ውጊያውም ቤትአዌንን አልፎ ሄደ።
24ሳኦል፥”ጠላቶቼን እስከምበቀልበት እስከ ምሽት ድረስ የትኛውንም ዓይነት መብል የሚበላ ቢኖር የተረገመ ይሁን“ ብሎ ሕዝቡን አምሎ ስለነበረ በዚያን ቀን የእስራኤል ሰዎች ተጨነቁ። ስለዚህ ከሠራዊቱ አንዱም ምግብ አልቀመሰም።
25ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ወደ ጫካ ውስጥ ገባ፥ ማርም በምድሩ ላይ ነበር።
26ሕዝቡ ወደ ጫካ በገባ ጊዜ ማሩ ይፈስስ ነበር፥ ነገር ግን ሕዝቡ መሓላውን ስለፈራ በእጁ ጠቅሶ ወደ አፉ ያደረገ አንድም አልነበረም።
27ዮናታን ግን አባቱ ሕዝቡን በመሓላ ማሰሩን አልሰማም ነበር። በእጁ ላይ የነበረውን በትር ጫፉን በማሩ እንጀራ ውስጥ አጠቀሰው። እጁን አንሥቶ ወደ አፉ አደረገው፥ ዐይኖቹም በሩለት።
28ከዚያም ከሰዎቹ አንዱ፥”ሕዝቡ በረሃብ ቢደክምም እንኳን አባትህ፥ 'በዚህ ቀን ምግብ የሚበላ የተረገመ ይሁን' ብሎ ሕዝቡን ከመሓላ ጋር አጥብቆ አዝዞአል" ብሎ መለሰለት።
29ከዚያም ዮናታን፥ "አባቴ በምድሪቱ ላይ ችግር ፈጥሯል። ከዚህ ማር ጥቂት በመቅመሴ ዐይኖቼ እንዴት እንደበሩ ተመልከቱ።
30ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው ከበዘበዙት ላይ ዛሬ በነጻነት በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ በተሻለ ነበር? ምክንያቱም አሁን በፍልስጥኤማውያን መካከል የተገደሉት ያን ያህል ብዙ አይደሉም“ አለ።
31እነርሱም በዚያን ቀን ፍልስጥኤማውያንን ከሚክማስ ጀምሮ እስከ ኤሎን ድረስ መቱአቸው። ሕዝቡም እጅግ ደከሙ።
32ሕዝቡም ተስገብግበው ወደ ብዝበዛው ተጣደፉ፥ በጎችን፥ በሬዎችንና ጥጆችንም በመሬት ላይ አረዱ። ሕዝቡም ከነደሙ በሉ።
33ከዚያም ለሳኦል፥ "ተመልከት፥ ሕዝቡ ከነደሙ በመብላታቸው በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት በመሥራት ላይ ናቸው" አሉት። ሳኦልም፥ "ተላልፋችኋል፥ አሁንም ትልቅ ድንጋይ አንከባልላችሁ አምጡልኝ“ አለ።
34በመቀጠልም፥ "ወደ ሕዝቡ ሂዱና፥ 'እያንዳንዱ ሰው በሬውንና በጉን እዚህ አምጥቶ በማረድ ይብላ። ከነደሙ በመብላት በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአትን አታድርጉ' ብላችሁ ንገሯቸው" አለ። ስለዚህ በዚያ ምሽት እያንዳንዱ በሬውን እያመጣ በዚያ ዐረደው።
35ሳኦል ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፥ ይኸውም ለእግዚአብሔር የሠራው የመጀመሪያው መሠዊያ ነበር።
36ከዚያም ሳኦል፥ "ሌሊቱን ፍልስጥኤማውያንን እናሳድ፥ እስኪነጋም ድረስ ሀብታቸውን እንበዝብዝ፤ ከእነርሱም አንድ በሕይወት አናስቀር“ አለ። እነርሱም፥”መልካም መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግ“ ብለው መለሱለት። ካህኑ ግን፥”እዚሁ እግዚአብሔርን እንጠይቅ“ አለ።
37ሳኦልም እግዚአብሔርን እንዲህ ሲል ጠየቀ፥”ፍልስጥኤማውያንን ላሳድዳቸው? በእስራኤል እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህ? “። ነገር ግን በዚያን ቀን እግዚአብሔር አልመለሰለትም።
38ከዚያም ሳኦል፥”የሕዝቡ አለቆች የሆናችሁ ሁሉ ወደዚህ ቅረቡ፤ ዛሬ ይህ ኃጢአት እንዴት እንደመጣብን መርምሩና ዕወቁ።
39እስራኤልን ያዳነ ሕያው እግዚአብሔርን! ልጄ ዮናታን ቢሆን እንኳን በእርግጥ እርሱ ይሞታል" አለ። ነገር ግን ከሕዝቡ ሁሉ አንዱም እንኳን አልመለሰለትም።
40እርሱም እስራኤልን በሙሉ፥ “እናንተ በአንድ በኩል ቁሙ፥ እኔና ልጄ ዮናታን በሌላው በኩል እንቆማለን” አላቸው። ሕዝቡም ሳኦልን፥ “መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” አሉት።
41ስለዚህ ሳኦል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርን፥ “በቱሚም አሳየኝ” አለው። ዮናታንና ሳኦል በዕጣ ተያዙ፥ ሕዝቡ ግን የተመረጠ ሆነና አመለጠ።
42ከዚያም ሳኦል፥ “በእኔና በልጄ በዮናታን መክከል ዕጣ ጣሉ” አለ። ዮናታንም በዕጣ ተያዘ።
43ሳኦልም ዮናታንን፥ “ያደረግኸውን ንገረኝ” አለው። ዮናታንም፥ “በእጄ በነበረው በትር ጫፍ ጥቂት ማር ቀምሻለሁ። ይኸው ለመሞት ዝግጁ ነኝ” አለ።
44ሳኦልም፥ “ዮናታን ሆይ፥ ባትሞት እግዚአብሔር በእኔ ላይ እንዲሁ ያድርግ፥ ይጨምርም” አለ።
45ሕዝቡም ሳኦልን፥ “ለእስራኤል ይህንን ታላቅ ድል ያመጣ ዮናታን መሞት ይገባዋል? ይህ ከእርሱ ይራቅ! እርሱ ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር ሠርቷልና ሕያው እግዚአብሔርን! ከራስ ጸጉሩ አንድ በምድር ላይ አይወድቅም" አሉት። ስለዚህ ሕዝቡ ዮናታንን ከመሞት አዳነው።
46ከዚያም ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ማሳደዱን አቆመ፥ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ስፍራቸው ሄዱ።
47ሳኦል እስራኤልን መግዛት በጀመረ ጊዜ፥ በየአቅጣጫው ከነበሩ ጠላቶቹ ሁሉ ጋር ተዋጋ። እርሱም ከሞዓብ፥ ከአሞን ሰዎች፥ ከኤዶም፥ ከሱባ ነገሥታትና ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ። በደረሰበት ሁሉ በቅጣት ያሰቃያቸው ነበር።
48ከአማሌቃውያን ጋር በጀግንነት ተዋግቶ ድል አደረጋቸው። እስራኤላውያንንም ከዘራፊዎቻቸው እጅ አዳናቸው።
49የሳኦል ወንዶች ልጆች ዮናታን፥ የሱዊና ሜልኪሳ ነበሩ። የሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ስም፥ የመጀመሪያ ልጁ ሜሮብና ታናሿ ሜልኮል ይባሉ ነበሩ።
50የሳኦል ሚስት ስም አኪናሆም ነበር፥ እርሷም የአኪማአስ ልጅ ነበረች። የሠራዊቱ አዛዥ ስም፥ የሳኦል አጎት የኔር ልጅ አበኔር ነበር።
51ቂስ የሳኦል አባት ነበር፤ የአበኔር አባት ኔርም የአቢኤል ልጅ ነበር።
52በሳኦል ዘመን ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ከባድ ጦርነት ይካሄድ ነበር። ሳኦል ኃያል ወይም ብርቱ የሆነ ሰው ባየ ጊዜ ሁሉ ያንን ወደ ራሱ ይሰበስብ ነበር።