1ሳኦል መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር፤ በእስራኤል ላይ አርባ ዓመት በነገሠ ጊዜ፥
2ከእስራኤል ሦስት ሺህ ሰዎች መረጠ። አንዱ ሺህ ከዮናታን ጋር በብንያም ጊብዓ ሲሆኑ ሁለቱ ሺህ በኮረብታማው አገር በቤቴልና በማክማስ ከእርሱ ጋር ነበሩ። የቀሩትን ወታደሮች ወደየቤታቸው፥ እያንዳንዱንም ወደ ድንኳኑ አሰናበታቸው።
3ዮናታን በጊብዓ የነበረውን የፍልስጥኤማውያን ጦር ድል አደረገ፥ ፍልስጥኤማውያንም ይህንን ሰሙ። ከዚያም ሳኦል፥ “ዕብራውያን ይስሙ” በማለት በምድሪቱ ሁሉ ላይ መለከት አስነፋ።
4ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጦር እንዳሸነፈ፥ ደግሞም እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን እንደ ግም መቆጠራቸውን እስራኤላውያን በሙሉ ሰሙ። ከዚያም ወታደሮቹ በጌልገላ ሳኦልን ለመከተል በአንድ ላይ ተሰበሰቡ።
5ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት በአንድ ላይ ተሰበሰቡ፤ ሦስት ሺህ ሠረገሎች፥ ስድስት ሺህ ሠረገላ ነጂዎችና የሠራዊቱም ቁጥር በባህር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ነበሩ። እነርሱም መጥተው ከቤትአዌን በስተምሥራቅ ማክማስ ላይ ሰፈሩ።
6የእስራኤል ሰዎች ችግር ውስጥ መግባታቸውንና ሕዝቡም መጨነቁን ባዩ ጊዜ፥ ሕዝቡ በዋሻዎች፥ በየቁጥቋጦ ሥር፥ በዐለቶች፥ በገደሎችና በጉድጓዶች ውስጥ ተደበቁ።
7አንዳንድ ዕብራውያንም የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር ወደ ጋድና ገለዓድ ምድር ሄዱ። ሳኦል ግን ገና በጌልገላ ነበር፥ የተከተለው ሕዝብ በሙሉ በፍርሃት ይንቀጠቀጥ ነበር።
8እርሱም ሳሙኤል በሰጠው ቀጠሮ መሠረት ሰባት ቀን ቆየ። ነገር ግን ሳሙኤል ወደ ጌልገላ አልመጣም ነበር፥ ሕዝቡም ከሳኦል ተለይቶ መበታተን ጀምሮ ነበር።
9ሳኦልም፥ "የሚቃጠለውን መባና የሰላሙን መባዎች አምጡልኝ" አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መባ አቀረበ።
10የሚቃጠለውን መባ ማቅረቡን እንደ ጨረሰ ሳሙኤል ወደዚያ ደረሰ። ሳኦልም ሊገናኘውና ሰላምታ ሊሰጠው ሄደ።
11ከዚያም ሳሙኤል፥ "ያደረግከው ምንድነው?" አለው። ሳኦልም፥ "ሕዝቡ ትተውኝ እየሄዱ እንዳሉ፥ አንተም በቀጠሮው ሰዓት አለመምጣትህን፥ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ መሰብሰባቸውን ባየሁ ጊዜ፥
12'አሁን ፍልስጥኤማውያን ወደ ጌልገላ በእኔ ላይ ሊወርዱብኝ ነው፥ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንኩም' ብዬ አሰብኩኝ። ስለዚህ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለማቅረብ ግድ ሆነብኝ“ ብሎ መለሰለት።
13ሳሙኤልም ሳኦልን፥”ያደረግከው ስንፍና ነው። አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትዕዛዝ አልጠበቅክም። በዚህ ቀን እግዚአብሔር መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም ሊያጸናልህ ነበር።
14አሁን ግን አገዛዝህ አይቀጥልም። እግዚአብሔር ያዘዘህን አልታዘዝክምና እርሱ እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው ፈልጓል፥ እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ መስፍን እንዲሆን መርጦታል" አለው።
15ከዚያም ሳሙኤል ከጌልገላ ተነሥቶ ወደ ብንያም ጊብዓ ወጣ። ሳኦል ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ቆጠራቸው፥ ስድስት መቶ የሚያክሉ ነበሩ።
16ሳኦል፥ ልጁ ዮናታንና ከእነርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በብንያም ጊብዓ ቆዩ። ፍልስጥኤማውያን ግን በማክማስ ሰፍረው ነበር።
17ከፍልስጥኤም ጦር ሰፈር ወራሪዎች በሦስት ቡድን ተከፍለው መጡ። አንደኛው ቡድን ወደ ሦጋል ምድር ወደ ዖፍራ ታጠፈ።
18ሌላኛው ቡድን በቤትሖሮን አቅጣጫ ታጠፈ፥ ሌላኛውም ቡድን በምድረ በዳው አቅጣጫ ወደ ስቦይም ሸለቆ ቁልቁል ወደሚያሳየው ወሰን ዞረ።
19ፍልስጥኤማውያን፥ “ዕብራውያን ለራሳቸው ሰይፍ ወይም ጦር እንዳይሠሩ" ብለው ስለነበረ፥ በመላው እስራኤል ብረት ሠሪ አልተገኘም።
20ነገር ግን የእስራኤል ወንዶች ሁሉ፥ እያንዳንዱ የማረሻውን ጫፍ፥ ዶማውን፥ ጠገራውንና ማጭዱን ለማሳል ወደ ፍልስጥኤማውያን ይወርድ ነበር።
21የክፍያው ዋጋ ለማረሻው ጫፍና ለዶማው የሰቅል ሁለት ሦስተኛ፥ ጠገራ ለማሳልና መውጊያውን ለማቃናት የሰቅል አንድ ሦስተኛ ነበር።
22ስለዚህ በጦርነቱ ቀን ሰይፍና ጦር በሳኦልና በዮናታን እጅ ብቻ እንጂ ከእነርሱ ጋር ከነበሩት ወታደሮች በአንዱም እጅ ሰይፍ ወይም ጦር አልነበረም።
23የፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ወደ ማክማስ መተላለፊያ ወጣ።