መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ሳሙኤል 11

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አሞናዊው ናዖስ ሄዶ ኢያቢስ ገለዓድን ከበባት። የኢያቢስ ሰዎች ሁሉ ናዖስን፥ "ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፥ እኛም እናገለግልሃለን" አሉት።
2አሞናዊው ናዖስም፥ "የሁላችሁንም ቀኝ ዐይኖቻችሁን በማውጣት በመላው እስራኤል ላይ ኃፍረትን አመጣለሁ፥ በዚህ ቅድመ ሁኔታ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ" ብሎ መለሰላቸው።
3የኢያቢስ ሽማግሌዎችም፥ "ወደ እስራኤል ወገኖች ሁሉ መልዕክተኞችን እንድንልክ ለሰባት ቀናት ታገሰን። ከዚያም የሚያድነን አንድም ባይኖር ለአንተ እንገዛለን" በማለት መለሱለት።
4መልዕክተኞቹም ሳኦል ወደሚኖርበት ወደ ጊብዓ መጥተው የሆነውን ነገር ለሕዝቡ ነገሯቸው። ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ።
5በዚህ ጊዜ ሳኦል ከእርሻ በሬዎቹን እየነዳ መጣ። ሳኦልም፥ "ሕዝቡ ምን ሆኖ ነው የሚያለቅሰው?" አለ። እነርሱም የኢያቢስ ሰዎች ያሉትን ለሳኦል ነገሩት።
6ሳኦል የነገሩትን በሰማ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል መጣበት፥ እጅግም ተቆጣ።
7የበሬዎቹን ቀንበር ወስዶ ፈለጣቸውና ወደ እስራኤል ወሰኖች ሁሉ በመልዕክተኞች እጅ ላከው። እርሱም፥ "ሳኦልንና ሳሙኤልን ተከትሎ በማይመጣው ሁሉ በበሬዎቹ ላይ እንዲህ ይደረግበታል" አለ። ከዚያም ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍርሃት በሕዝቡ ላይ ወደቀ፥ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰብስበው መጡ።
8ቤዜቅ በተባለ ስፍራ በሰበሰባቸው ጊዜ፥ የእስራኤል ሰዎች ሦስት መቶ ሺህ፥ የይሁዳም ሰዎች ሠላሳ ሺህ ነበሩ።
9እነርሱም ለመጡት መልዕክተኞች፥ "ለኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች፥ 'ነገ ፀሐይ ሞቅ በሚልበት ሰዓት እንታደጋችኋለን' ብላችሁ ንገሯቸው" አሏቸው። መልዕክተኞቹ ሄደው ለኢያቢስ ሰዎች ነገሯቸው፥ እነርሱም እጅግ ደስ አላቸው።
10ከዚያም የኢያቢስ ሰዎች ናዖስን፥”ነገ እንገዛልሃለን፥ አንተም ደስ የሚያሰኝህን ልታደርግብን ትችላለህ“ አሉት።
11በቀጣዩ ቀን ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ቡድን ከፈላቸው። ሊነጋጋ ሲል ወደ ጦር ሠፈሩ መካከል መጡ፥ አሞናውያንንም አጠቁ፥ ቀኑ እስኪሞቅ ድረስም አሸነፏቸው። በሕይወት የተረፉትም ከእነርሱ ሁለቱ አንድ ላይ ሆነው እስከማይታዩ ድረስ ተበታተኑ።
12በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ሳሙኤልን፥ "'ሳኦል በእኛ ላይ እንዴት ይነግሣል?' ያለው ማን ነበር? እንድንገድላቸው ሰዎቹ ይምጡልን" አሉት።
13ነገር ግን ሳኦል፥ "ዛሬ እግዚአብሔር እስራኤልን ታድጎታልና በዚህ ቀን ማንም መገደል የለበትም" አላቸው።
14ሳሙኤልም ሕዝቡን፥ "ኑ፥ ወደ ጌልገላ እንሂድና በዚያ መንግሥቱን እናድስ" አላቸው።
15ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄደው በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ ሳኦልን አነገሡት። በዚያም በእግዚአብሔር ፊት የሰላምን መባ ሠዉ፥ ሳኦልና የእስራኤል ሰዎችም ሁሉ እጅግ ደስ አላቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።