መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ጴጥሮስ 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እንግዲህ ክፋትን ፣ ማታለልን ፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ።
2በድነታችሁ በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹህ የሆነውን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤
3ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ ከሆነ፣
4በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ ቅረቡ።
5ደግሞም እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት የሚያቀርቡ ቅዱሳን ካህናት ትሆኑ ዘንድ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ትሠራላችሁ።
6በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈው «እነሆ፤ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም» ።
7እንግዲህ ለምታምኑት ለእናንተ እርሱ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን፣«ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ»
8እንደዚሁም ደግሞ «ሰዎችን የሚያሰናክልና የሚጥላቸውም ዐለት ሆነ»። የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ የተመደቡት ለዚህ ነውና።
9እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር የራሱ ያደረጋችሁ ሕዝብ ናችሁ።
10ቀድሞ የእርሱ ሕዝብ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።
11ወዳጆች ሆይ፤ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ መጠን፣ ነፍሳችሁን ከሚዋጉ ከኅጢኣት ምኞቶች እንድትርቁ እለምናችኋለሁ።
12ክፉ እንደምትሠሩ አድርገው ቢያሟችሁም፣ እርሱ በሚመጣበት ጊዜ መልካሙን ሥራችሁን አይተው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ፣ በአሕዛብ መካከል አኗኗራችሁ መልካም መሆን አለበት።
13ስለ ጌታ ብላችሁ ለምድራዊ ባለ ሥልጣን ሁሉ ታዘዙ፤
14የበላይ ባለ ሥልጣን ስለ ሆነ ለንጉሥ ቢሆን፣ ወይም ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት፣ በጎ አድራጊዎችን ለማመስገን እርሱ ለሾማቸው ገዦች ታዘዙ፤
15ምክንያቱም፣ መልካም በማድረግ የአላዋቂዎችን ከንቱ ንግግር ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።
16እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት።
17ለሰው ሁሉ ተገቢውን አክብሮት ስጡ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ።
18እናንተ አገልጋዮች ፤ ለመልካሞችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለክፉዎችም በፍጹም አክብሮት ታዘዙ።
19ስለ እግዚአብሔር ሲል የግፍ መከራን የሚቀበል ሰው ምስጋናን ያገኛል።
20ክፉ ሥራ ሠርታችሁ ስትቀጡ ብትታገሡ ምን ያስመሰግናችኋል? ነገር ግን መልካም ሥራ ሠርታችሁ መከራ ስትቀበሉ ብትታገሡ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ያስመሰግናችኋል።
21የተጠራችሁት ለዚህ ነው፤ ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌ ሊተውላችሁ ነው።
22እርሱ ኅጢአት አላደረገም፥ ተንኵልም በአፉ አልተገኘበትም፤
23ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራንም ሲቀበል አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤
24ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በመስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቊስል እናንተ ተፈውሳችኋል።
25ቀድሞ ሁላችሁም እንደ ጠፉ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።