መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ጴጥሮስ 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጴጥሮስ፤ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢታንያ ተበትነው በመጻተኝነት ለሚኖሩ፤ ለተመረጡት፤
2እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ በደሙ ለተረጩትና በመንፈስ ቅዱስ ለተቀደሱት፤ ጸጋ ለእናንተ ይሁን፤ ሰላማችሁም ይብዛ።
3የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በመነሣቱ ምክንያት ላገኘነው ርስት ዋስትና እንዲሆነን በታላቅ ምሕረቱ አዲስ ልደትን ሰጠን፤
4ይህም የማይጠፋ፣ የማይበላሽ እና የማያረጅ ርስት በመንግሥተ ሰማይ ተጠብቆላችኋል።
5እናንተም በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀው መዳን በእምነት አማካይነት በእግዚአብሔር ኅይል ተጠብቃችኋል።
6ምንም እንኳን አሁን በብዙ ልዩ ልዩ ዐይነት መከራ ማዘናችሁ ተገቢ ቢሆንም፣ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል።
7ይኸውም፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ እንዲፈተን ነው። ይህ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ አምነታችሁ ምስጋናን ክብርንና፣ ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው።
8ኢየሱስ ክርስቶስን ባታዩትም እንኳ ትወዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በእርሱ ታምናላችሁ፤ ሊነገር በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት በጣም ደስ ይላችኋል፤
9አሁን የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ ነውና።
10እናንተ ስለምትቀበሉት ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ይፈልጉና በጥልቅ ይመረምሩ ነበር፤
11የሚመጣው መዳን ምን ዐይነት እንደ ሆነ ለማወቅ ይመረምሩ ነበር፤ እንዲሁም በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራና ከመከራው በኋላ ስለሚሆነው ክብር አስቀድሞ የተናገራቸው በምን ጊዜና እንዴት እንደሚፈጸም ይመረምሩ ነበር። ነቢያቱ ያገለግሉ የነበሩት እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳልነበረ ተገልጦላቸዋል፤
12ይኸውም ከሰማይ በተላከው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወንጌልን ያበሠሩአችሁ ሰዎች የነገሩአችሁን በመግለጥ ነው፤ መላእክትም እንኳ ይህ ነገር ሲገለጥ ለማየት ይመኙ ነበር።
13ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጠቁ፤ ጠንቃቆች ሁኑ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በምታገኙት ጸጋ ላይ ፍጹም መተማመን ይኑራችሁ።
14ታዛዦች ልጆች እንደ መሆናችሁ ባለማወቅ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ።
15ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ፣ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤
16ምክንያቱም «እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ» ተብሎ ተጽፎአል።
17ሳያዳላ በእያንዳንዱ ሰው ላይ እንደየሥራው የሚፈርደውን «አባት» ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፣ በእንግድነት ዘመናችሁ እርሱን በማክበር ኑሩ።
18ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር ማለትም በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤
19ይልቁንም የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው።
20ክርስቶስ የተመረጠው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ነው፤ አሁን ግን በመጨረሻው ዘመን ለእናንተ ተገለጠ።
21በእርሱ አማካይነት፣ ከሞት ባስነሣውና ክብርን በሰጠው በእግዚአብሔር ታምናላችሁ። ይኸውም እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን ነው።
22ለእውነት በመታዘዝ ለእውነተኛ የወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልብ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።
23ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ ነገር ግን በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው።
24ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር፣ ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤
25የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። የተሰበከላችሁም ወንጌል መልእክቱ ይህ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።