1ንጉሥ ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱንና ቤተ መንግሥቱን እንዲሁም ሊሠራው የፈለገውን ሌላውንም ሁሉ ከፈጸመ በኋላ፣
2እግዚአብሔር ከዚህ በፊት በገባዖን እንደ ተገጠለት አሁንም እንደገና ተገለጠለት፡፡
3ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለው፡- በፊቴ ያቀረብከውን ጸሎትና ልመና ሰምቻለሁ፤ እርሱም ለዘለዓለም ለስሜ መጠሪያ እንዲሆን የሠራኸውን ቤተ መቅደስ ቀድሼዋለሁ፤ ዘወትርም ዓይኔና ልቤ በዚያ ይሆናል፡፡
4አንተ ግን አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በቅንነትና በታማኝነት በፊቴ ብትመላለስ፣ ሕጌንና ሥርዓቴን ብትጠብቅ፣ ያዘዝኩህንም ሁሉ ብትፈጽም፣
5ለአባትህ ለዳዊት ከዘሮችህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚነግሥ ልጅ አታጣም በማለት የሰጠሁትን የተስፋ ቃል በመጠበቅ ዙፋንህ በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ እንዲኖር አደርጋለሁ፡፡
6ነገር ግን አንተ ወይም ዘሮችህ እኔን መከተል ትታችሁ የሰጠኋችሁን ሕጎችና ትእዛዞች ባትፈጽሙና ባዕዳን አማልክትን ብታመልኩና ብትሰግዱላቸው፤
7እስራኤላውያንን ከሰጠኋቸው ምድር ተነቃቅለው እንዲባረሩ አደርጋለሁ፤ ስሜ እንዲጠራበት የቀደስኩትንም ይህንን ቤተ መቅደስ እተወዋለሁ፤ በየአገሩ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ እስራኤልን መሳለቂያና መዘባበቻ ያደርጓታል፡፡
8ይህ ከፍ ከፍ ብሎ የሚታየው ቤተ መቅደስ ፈርሶ የፍርስራሽ ክምር ይሆናል፤ በዚያ በኩል የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ ይህንን አይተው በመደንገጥ እግዚአብሔር ይህንን አገርና ይህንን ቤተ መቅደስ ለምን እንዲህ አደረገ በማለት ይሳለቁበታል፡፡
9ራሳቸው በሚሰጡት መልስ፣ የእስራኤል ሕዝብ የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በመተዋቸው ምክንያት ነው፤ ከዚህም በቀር ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ታማኝነት ትተው ሌሎች አማልክት አመለኩ፤ ሰገዱላቸውም፤ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ የጥፋት መቅሠፍት ያመጣባቸውም ስለዚህ ነው የሚል ይሆናል፡፡
10ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱንና ቤተ መንግሥቱን ለመሥራት የፈጀበት ጊዜ ሃያ ዓመት ነበር፡፡
11የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዚህ ሁሉ ሥራ ለሰሎሞን የሚያስፈልገውን የሊባኖስ ዝግባ ከብዙ ወርቅ ጋር ሰጥቶት ነበር፤ ሥራውም ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ ሰሎሞን በገሊላ ምድር የሚገኙትን ሃያ ታናናሽ ከተሞችን ለኪራም ሰጠው፡፡
12ኪራምም ሄዶ ከተሞቹን አየ፤ ነገር ግን ደስ አላሰኙትም፤
13ኪራምም ወንድሜ ሆይ! የሰጠኸኝ ከተሞች እነዚህ ምንድን ናቸውን? አለው፡፡ በዚህ ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ አካባቢው በሙሉ «ካቡል» እየተባለ ይጠራል፡፡
14ኪራም ለንጉሥ ሰሎሞን የላከለት ወርቅ አንድ መቶ ሺህ መክሊት ነበር፡፡
15ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና ቤተ መንግሥቱን፣ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር የሠሩለትና ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ያለውን ሚሎ ተብሎ የሚጠራውን ጎድጓዳ ስፍራ መጥተው ያስተካከሉለት የጉልበት ሥራ ዋጋ ነበር፤ እንዲሁም ሐጸር፤ መጊዶናጊዜር ተብለው የሚጠሩ ከተሞችም እንዲሠሩለት አደረገ፡፡
16ቀደም ሲል የግብጽ ንጉሥ ፈረዖን በጌዜር ላይ አደጋ ጥሎ፣ ነዋሪዎችዋን ከነዓናውያንን ገድሎ ከተማይቱንም አቃጥሎ በቁጥጥሩ ሥር አድርጓት ነበር፤ ከዚያም በኋላ ለሴት ልጁ ለሰሎሞን ሚስት እንደ ስጦታ ሰጣት፡፡
17ሰሎሞንም ጊዜርንና የታችኛው ቤት ሖሮን እንደገና አሠራ፡፡
18ባዕላት በይሁዳ በረሓማ አገር የምትገኝ ታማር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች እንደገና ሠራ፡፡
19እነዚህም የስንቅ ማከማቻዎች፣ ፈረሶችና ሠረገሎች የሚጠበቁባቸው ከተሞችን ሠራ፡፡ ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም፤ በሊባኖስና በግዛቱ ሁሉ የሚፈልገውን ገነባ፡፡
20እነዚህም ትውልዶች የእስራኤል ወገን ያልሆኑና የሚያገለግሉ አሞራውያን፣ ሒታውያን፣ ፈሪዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡
21ለሰሎሞን የጉልበት ሥራ ይሠሩለት የነበሩት የግዳጅ ሥራ ሠራተኞች እስራኤላውያን ምድራቸውን ርስት አድርገው በወረሱ ጊዜ የገደሏቸው የከነዓን ሕዝብ ተውልዶች ነበሩ፡፡
22ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ወገን ማንንም ባሪያ አድርጎ አላሠራም፤ በዚህ ፈንታ እነርሱ ባለሥልጣኖች፣ ወታደሮች፣ የጦር መኮንኖች፣ የጦር አዛዦች፣ ሠረገላ ለሚነዱ ሁሉ ኃላፊዎችና ፈረሰኞች ሆነው ያገለግሉ ነበር፡፡
23ሰሎሞን ለሚያከናውነው የሕንጻ ሥራ የጉልበት ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለተመደቡት ሰዎች አምስት መቶ ኃምሳ ኃላፊዎች ነበሩአቸው፡፡
24የግብጽ ንጉሥ የፈረዖን ልጅ የነበረችው ሚስቱ ከዳዊት ከተማ ራሱ ወዳሠራላት ቤተ መንግሥት ከተዘዋወረች በኋላ ሰሎሞን የሚሎን ከተማ ገነባ፡፡
25ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ባሠራው መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት በዓመት ሦስት ጊዜ ያቀርብ ነበር፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ በዚህም ዓይነት የቤተ መቅደሱ ሥራ ተፈጸመ፡፡
26እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን በኤዶም ምድር በቀይ በሕር ዳርቻ በምትገኘው በኤላት አጠገብ ባለችው በዔጽዮን ጋብር መርከቦችን ሠራ፡፡
27ንጉሥ ኪራምም ከሰሎሞን ሰዎች ጋር የሚያገለግሉ የሠለጠኑ መርከበኞችን ላከለት፡፡
28እነርሱም በመርከብ ተጉዘው ወደ ኦፊር ምድር ከሄዱ በኋላ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ሲመለሱ አራት መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ ይዘውለት መጡ፡፡