መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ነገስት 10

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ንግሥተ ሳባ እግዚአብሔር ለሰሎሞን ስለ ሰጠው አስደናቂ ጥበብ የሚነገረውንም ሁሉ ሰማች፤ ስለዚህ አስቸጋሪ በሆኑ ከባድ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች፡፡
2ብዙ የክብር አጃቢዎችን በማስከተል በግመሎች የተጫነ ሽቶ፣ የከበረ ዕንቁና ብዙ ወርቅ ይዛ መጣች፤ ከሰሎሞንም ጋር በተገናኙ ጊዜ በአሳብዋ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት፤
3እርሱም ላቀረበችለት ጥያቄ ሁሉ መልስ ሰጣት፤ ከጠየቀችው ሳይመልስላት የቀረ ምንም ዓይነት እንቆቅልሽ አልነበረም፡፡
4ንግሥተ ሳባ ጥበብ የተሞላበትን የሰሎሞንን አነጋገር አዳመጠች፤ የሠራውንም ቤተ መንግሥት አየች፡፡
5በሰሎሞን ገበታ ላይ የሚቀርበውን የምግብ ዓይነት፣ የመኳንንቱን መኖሪያ አካባቢዎች፣ የቤተ መንግሥቱን አሠራርና አደረጃጃት፣ የደንብ ልብሳቸውን ዓይነት፣ በግብዣ ጊዜ የሚያገለግሉትን አሳላፊዎችና በቤተ መቅደስም ያቀረባቸውን መሥዋዕቶችን ሁሉ ተመለከተች፤ በዚህም ሁሉ የተሰማት አድናቆት ከጠበቀቸው በላይ ሆነባት፤
6ስለሥራህ ውጤትና የጥበብህ ታላቅነት በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ሁሉ እውነት ነው አለች፡፡
7ነገር ግን እዚህ ድረስ መጥቼ በዐይኔ እስካይ ድረስ የተነገረኝን ሁሉ አላመንኩም ነበር፤ በጆሮዬ የሰማሁት በዐይኔ ያየሁትን እኩሌታ እንኳ አይሆንም፤ በእርግጥም ጥበብህና ሀብትህ በአገሬ ሳለሁ ከተነገረኝ በጣም ይበልጣል፡፡
8ሁልጊዜ በፊትህ በመገኘት ጥበብ የሞላበት ንግግርህን የሚሰሙ ሚስቶችህና አገልጋዮችህ እንዴት የታደሉ ናቸው!
9አምላክህ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እርሱ አንተን መርጦ የእስራኤል ንጉሥ በማድረግ በአንተ መደሰቱን ገልጦልሃል፤ ለእስራኤል ያለውም ፍቅር ለዓላማው ስለ ሆነ ጽድቅና ፍትሕ ጸንቶ እንዲኖር ታደርግ ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎሃል፡፡
10ንግሥተ ሳባ ያመጣችለትን ስጦታ ሁሉ ለንጉሥ ሰሎሞን አበረከተችለት፤ ይኸውም ከአራት ሺህ ኪሎ የሚበልጥ ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ሽቶና የከበረ ዕንቁ ነበር፤ እርስዋ ለሰሎሞን ያበረከተችው የሽቶ ብዛት ከዚያ በኋላ ከቀረበለት የሽቶ ገጸ በረከት ሁሉ እጅግ የሚበልጥ ነበር፡፡
11ከኦፊር ወርቅ ብዙ ያመጡለት የኪራም መርከቦች ከዚያው ከኦፊር ብዙ የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቁ አምጥተውለት ነበር፡፡
12ሰሎሞን ከዚሁ ከሰንደል እንጨት የቤተ መቅደሱንና የቤተ መንግሥቱን መከታዎች፤ መዘምራን የሚያገለግሉባቸውን በገናዎችና መሰንቆዎች አሠራ፤ ይህም የሰንደል እንጨት ወደ እስራኤል አገር ከመጣው የሰንደል እንጨት ሁሉ የሚበልጥ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ይህን የመሰለ የሰንደል እንጨት ከቶ ታይቶ አይታወቅም፡፡
13ንጉሥ ሰሎሞን ከተለመደው የልግሥና ስጦታ ጋር የሳባ ንግሥት የጠየቀቸውን ሁሉ ሰጣት። ከዚህ በኋላ ንጉሥተ ሳባ ከክብር አጃቢዎችዋ ጋር ወደ አገርዋ ተመልሳ ሄደች፡፡
14ንጉሥ ሰሎሞን በየዓመቱ ሃያ ሦስት ሺህ ኪሎ ያህል የሚመዝን ወርቅ ያገኝ ነበር፤
15ይህም ሁሉ ነጋዶዎች ከሚከፍሉት ቀረጥ፤ ከንግድ ከሚገኘው ትርፍ እንዲሁም ከዐረብ ነገሥታትና ከእስራኤል ክፍላተ አገር አስተዳዳሪዎች ከሚገባለት ግብር ጋር ተጨማሪ ነበር፡፡
16ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ታላላቅ ጋሻዎች አሠርቶ እያንዳንዱን ጋሻ በሰባት ኪሎ ያህል ወርቅ አስለበጠው፡፡
17እንዲሁም ሦስት መቶ ታናናሽ ጋሻዎችን አሠርቶ እያንዳንዱን በሁለት ኪሎ ያህል ወርቅ አስለበጠው፤ እነዚህንም ሁሉ ሊባኖስ ጫካ ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ አኖራቸው፡፡
18እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን ከዝሆን ጥርስ አንድ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው፡፡
19ወደ ዙፋኑ መወጣጫ ስድስት ደረጃዎች ነበሩ፤ የዙፋኑ ጀርባ ራስጌው ክብ ነበር፤ በዙፋኑ ግራና ቀኝ የክንድ ማሳረፊያዎች ነበሩት፤ በክንድ ማሳረፊያዎቹ ጎን አንዳንድ የአንበሳ ምስሎች ቆመው ነበር፡፡
20በእያንዳንዱ ደረጃ በሁለት በኩል አንዳንድ የአንበሳ ምስል በድምሩ ዐሥራ ሁለት የአንበሳ ምስሎች ቆመዋል፡፡ ይህን የመሰለ ዙፋን በሌላ በየትኛውም አገር ተሠርቶ አያውቅም ነበር፡፡
21በሰሎሞን ዘመን ብር ምንም ዋጋ ስላልነበረው ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዋንጫዎች ሁሉና የሊባኖስ ጫካ ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ የሚገኙት ዕቃዎች በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ እንጂ ከብር አልተሠሩም፤
22ሰሎሞን ከኪራም መርከቦች ጋር በውቅያኖስ ላይ የሚጓዙ ሌሎች የተርሴስ መርከቦችም ነበሩት፤ እነርሱ በየሦስት ዓመት ወርቅ፣ ብር፣ የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችንና ዝንጀሮዎችን ያመጡለት ነበር፡፡
23ንጉሥ ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሚበልጥ ሀበታምና ጥበበኛ ነበር፤
24በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎችም ሁሉ እግዚአብሔር የሰጠውን ጥበብ የሞላበትን ንግግር ይሰሙ ዘንድ ወደ እርሱ መምጣት ይፈልጉ ነበር፡፡
25ወደ እርሱም የሚመጡት ሁሉ የብርና የወርቅ፣ የልብስ፣ የጦር መሣሪያዎች፣ የሽቶ፣ የፈረሶች የበቅሎዎች ስጦታዎች ያመጡለት ነበር፤ ይህም በየዓመቱ የሚደረግ ነበር፡፡
26ሰሎሞንም ሠረገሎችና ፈረሶች ሰበሰበ፤ እርሱም አንድ ሺህ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶኞች ነበሩት፤ ከእነርሱም ከፊሎቹን ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም፣ ሌሎቹ ደግሞ በልዩ ልዩ ከተሞች ተመድበው እንዲኖሩ አደረገ፡፡
27በግዛቱም ዘመን ሁሉ በኢየሩሳሌም ብር እንደ ድንጋይ፣ ብዛቱም እንደ ሊባኖስ ዛፍ፣ በይሁዳ ኮረብቶች ግርጌ በየትኛውም ስፍራ እንደሚበቅለው ሾላም ይቆጠር ነበር፡፡
28ሰሎሞን ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ ያስመጣ ነበር፤ የንጉሡም ነጋዴዎች ፈረሶችን በገንዘብ ገዝተው ከቀዌ ያመጡለት ነበር፡፡
29እያንዳንዱ ፈረስ በስድስት መቶ ጥሬ ብር፣ እያንዳንዱም ሠረገላ በአንድ መቶ ሃምሳ ጥሬ ብር ከግብጽ አገር ተገዛ፡፡ ከዚያም ለሒታውያንና ለሶርያውያን ነገሥታት ተሸጡ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።