መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ነገስት 8

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የዳዊት ከተማ ከሆነችው ከጽዮን ለማምጣትና ወደ ቤተ መቅደሱ ለማስገባት የእስራኤል የነገድ መሪዎችና የጎሣ አለቆች ሁሉ እርሱ ወደሚገኝበት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ ጠራ፡፡
2የእስራኤልም ወንዶች ሁሉ በዓሉ በሚከበርበት ኤታኒም ተብሎ በሚጠራው በሰባተኛው ወር ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ተሰበሰቡ፡፡
3መሪዎቹ ሁሉ በተሰበሰቡ ጊዜም ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሥተው ተሸከሙ፡፡
4ካህናቱም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት፣ የመገናኛ ድኳንና በድንኳኑም ውስጥ የነበሩትን ንዋያተ ቅዱሳት ሁሉ አምጥተው ወደ ቤተ መቅደስ አገቡ፡፡
5ንጉሥ ሰሎሞንና መላው የእስራኤል ሕዝብ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ተሰበሰቡ፤ ከብዛቱም የተነሣ ሊቆጠር የማይችል ብዙ በጎቸና የቀንድ ከብት መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ፡፡
6ከዚህም በኋላ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል፣ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ወደ ቦታው አምጥተው በኪሩቤል ክንፎች ሥር አኖሩት፡፡
7የተዘረጉ የኪሩቤል ክንፎችም የታቦቱን መሸከሚያ መሎጊያዎች ሸፍነው ነበር፡፡
8መሎጊያዎቹ ረጃጅሞች ስለ ሆኑ ጫፎቻቸው በቤተ መቅደሱ ውስጥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ለሚቆም ሰው ሁሉ በግልጽ ይታዩ ነበር፤ በሌላ አቅጣጫ የሚቆም ግን አያያቸውም፡፡ እስከ ዛሬም እዚያው ይገኛል፡፡
9የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር እንደወጡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳ በገባ ጊዜ ሙሴ በሲና ተራራ በቃል ኪዳን ታቦት ውስጥ ካኖራቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር በቃል ኪዳን ታቦት ውስጥ ሌላ ምንም ነገር አልነበረም፡፡
10ካህናቱ ከቅድስተ ቅዱሳን እንደ ወጡ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ድንገት በደመና ተሞልቶ ነበር፡፡
11በደመናውም ውስጥ የነበረው የእግዚአብሔር ክብር ቤቱን ስለ ሞላ ካህናቱ ቆመው አገልግሎታቸውን ለማከናወን አልቻሉም ነበር፡፡
12በዚህ ጊዜ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጸለየ፡- እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! አንተ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብለሃል፤
13እነሆ አሁን ግርማ ሞገስ ያለው ቤተ መቅደስ ለአንተ ሠርቻለሁ፤ እርሱም አንተ ለዘለዓለም የምትኖርበት ቦታ ይሆናል፡፡
14የእስራል ጉባኤ ሁሉ ቆመው ሳሉ፤ ንጉሥ ሰሎሞን ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ የእግዚአብሔር በረከት በእርሱ ላይ እንዲወርድ እንዲህ ሲል ጸለየ፤
15የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! ለአባቴ ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን አጽንቶ ጠብቆአል፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፡-
16ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ የሚሠራበት በመላው እስራኤል ምንም ዓይነት ከተማ አልመረጥኩም ነበር፤ አሁን ግን በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን መረጥኩ፡፡
17ቀጥሎም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን ለመሥራት አቅዶ ነበር፤
18እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን ስሜ የሚጠራበትን ቤተ መቅደስ ትሠራ ዘንድ በልብህ ማሰብህ መልካም ነው፡፡
19ነገር ግን እርሱን የሚሠራልኝ ልጅህ ነው እንጂ አንተ አይደለህም፤ ከአንተ የሚወለደው ልጅ ቤተ መቅደሴን ይሠራል አለው፡፡
20እነሆ እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቆአል፤ ስለዚህ እኔ በአባቴ ፈንታ ተተክቼ የእስራኤል ንጉሥ ሆኜአለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን ሠርቼአለሁ፡፡
21እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር ቃል ኪዳን የገባበት የድንጋይ ጽላት ለሚገኝበት ታቦት ማኖሪያ የሚሆን ቦታ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አዘጋጅቼአለሁ፡፡
22ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በሕዝቡ ፊት ተነሥቶ በእግዚአብሔር መሠዊያው ፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘረጋ፡፡
23እንዲህም አለ፡- የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአገልጋዮቹ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ከልባቸው ታማኞች እስከ ሆኑ ድረስ ፍቅሩን የሚያጸና በላይ በሰማይ በታችም በምድ እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም!
24ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውንም የተስፋ ቃል አጽንተሃል፤ በአፍህ የተናገርከውም ቃል ሁሉ እነሆ ዛሬ በእጅህ ተፈጽሞአል፡፡
25አሁን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአባቴ ለዳዊት አንተ ታደርገው በነበረው ዓይነት ልጆችህ ታዛዦች ቢሆኑና በፊቴም በቅንነት ቢመላለሱ ሁልጊዜ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚነግሥ ልጅ አላሳጣህም ስትል የተናገርከውን የተስፋ ቃል ፈጽም፡፡
26አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ! አገልጋይህ ለነበረው ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ሁሉ እንዲፈጸም አድርግ፡፡
27በውኑ እግዚአብሔር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ ሰማያት፤ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ሊይዝህ አይችልም፤ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስ ምንኛ ያንስ፡፡
28ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! ወደ አገልጋይህ ጸሎትና ልመና ተመልክት፤ ዛሬም አገልጋይህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጩኸት ስማ፡፡
29ስሜ ይጠራበታል ወዳልከው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቀንና ሌሊት ተመልከት፤ እኔም አገልጋይህ ወደዚህ ቤተ መቅደስ የምጸልየውን ጸሎት ስማ፡፡
30ፊታችንን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰን በምንጸልይበት ጊዜ የእኔንና የእስራኤልን ሕዝብ ጸሎት ስማ፤ ከመኖሪያህ ከሰማይ ሆነህ ስማን፤ ይቅርም በለን፡፡
31አንድ ሰው ባልንጀራውን መበደሉን የሚገልጥ ክስ ቀርቦበት በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደሚገኘው መሠዊያ አምጥተውት ከበደል ንጹሕ መሆኑን በመሐላ በሚያረጋግጥበት ጊዜ፣ በሰማይ ሆነህ ስማ፤
32ለአገልጋዮችህም ፍርድን ስጥ፤ ይኸውም በደል የሠራው ሰው በጥፋቱ መጠን እንዲቀጣ፣ ንጹሕ የሆነውም ነጻ እንዲወጣ አድርግ፡፡
33ሕዝብህ እስራኤል በደል ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት በጠላቶቻቸው ድል ሲሆኑ ተጸጽተው ወደ አንተ በመመለስ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢመጡና የአንትን ይቅርታ ለማግኘት ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በትሕትና ቢለምኑህ፤
34አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ በምርኮ የሚገኙትንም ሕዝብህን ኃጢአት ይቅር በማለት ለቀድሞ አባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር መልሰህ አግባቸው፡፡
35የእስራኤል ሕዝብ በደል ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት ዝናብ እንዳይዘንብላቸው አድርገህ በምትቀጣቸው ጊዜ በፈጸሙት በደል በመጸጸት ፊታቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰው በትሕትና ቢለምኑህ፤
36አንተ በሰማያት ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ የአገልጋዮችህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፣ በልብ ቅን የሆነውንም ነገር ማድረግ ይችሉ ዘንድ አስተምራቸው፤ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሆይ፣ ለዘለዓለም ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸው በዚህች ምድር ዝናብ እንዲዘንብ አድርግ።
37በምድሪቱ ላይ ረሐብ ወይም ቸነፈር በሚመጣበት ጊዜ፣ እንዲሁም እህላቸው በውርጭ በዋግና በአንበጣ ወይም በኩብኩባ መንጋ በሚወድምበት ጊዜ ወይም ጠላቶቻቸው በሕዝብህ ላይ አደጋ በሚጥሉበት ጊዜ ወይም በሕዝብህ ላይ ልዩ በሽታና ደዌ በሚደርስባቸው ጊዜ፣
38በሕዝብህ በእስራኤል መካከል ልብ የሚያሸብር መራር ሐዘን ደርሶባቸው እጃቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ በመዘርጋት በሚጸልዩበት ጊዜ፣ ጸሎታቸውን ስማ፡፡
39በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት ይቅር በላቸው፤ እርዳቸውም፣ በሰው ልብና አእምሮ ያለውን አሳብ ሁሉ መርምረህ የምታውቅ አንተ ብቻ ነህ፤ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የሚገባውን ዋጋ ስጠው፡፡
40በዚህም ዓይነት ሕዝብህ ለቀድሞ አባቶቻችን ርስት አድርገህ በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ለአንተ ታዛዦች እንዲሆኑና እንዲያከብሩህ አድርግ፡፡
41በተጨማሪም የሕዝብህ የእስራኤል ወገን ያልሆነ፣ የውጪ አገር ሰው ከስምህ የተነሣ ከሩቅ ቢመጣ፤
42ስለስምህ ገናናነት፣ ስለታላቁ እጅህና ከፍ ስላለው ክንድህ ሰምተው፣ በዚህ ቤተ መቅደስ ቢመጡና ቢጸልዩ፣
43ከምትኖርበት ከሰማይ ሆነህ የዚያን ሰው ጸሎት ስማ፤ እንድታደርግለት የሚለምንህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ሕዝብህ እስራኤላውያን እንደሚያደርጉት በመላው ዓለም የሚኖሩ ሕዝቦች አንተን በማወቅ እንዲታዘዙህና እንዲያከብሩህ አድርግ፣ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ይህ እኔ የሠራሁት ቤተ መቅደስ የአንተ ስም የሚጠራበት መሆኑን ያውቃሉ፡፡
44ጠላቶቻቸውን ለመዋጋት እንዲዘምቱ ሕዝብህን በምታዝበት ጊዜ በየትኛውም ስፍራ ሆነው ወደዚህች ወደ መረጥኻት ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው በሚጸልዩበት ጊዜ፣
45በሰማያት ሆነህ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን ስማ፤ በችግራቸውም እርዳቸው፡፡
46ሕዝብህ ኃጢአት በመሥራት አንተን ሲያሳዝኑህ አንተም ተቆጥተህ ጠላቶቻቸው ድል እንዲነሡአቸውና ወደ ሌላ አገር ማርከው እንዲወስዱአቸው በምታደርግበት ጊዜ፣ ሩቅ ወይም ቅርብ ቢሆን፣
47ምርኮኞች ሆነው በሚኖሩባት በዚያች አገር ሳሉ ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለና፤ ዐምፀናል ብለው በመናዘዝ ተጸጽተው ንስሓ ቢገቡ፣
48ማርከው በወሰዱአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸው በእውነትና በቅን መንፈስ ተጸጽተው ንስሓ በመግባት አንተ ለቀድሞ አባቶቻችን ወደ ሰጠሃቸው ወደዚህች ምድር፣ አንተም ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማ፣ እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፣
49ከዚያ በመኖሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውንና እርዳታ ፈልገው ሲለምኑህ በመስማት ፍረድላቸው፤
50ኃጢአታቸውንና አንተን ያሳዘኑበትን በደል ሁሉ ይቅር በል፤ ጠላቶቻቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ፤
51እነርሱ እንደ እቶን እሳት ከሚያቃጥል ከግብጽ ምድር ያወጣሃቸውና የመረጥካቸው ሕዝብህ ናቸው፡፡
52በጠሩህ ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለአገልጋይህና ለሕዝብህ ልመና ዓኖችህ የተገለጡ ይሁኑ፡፡
53እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! የቀድሞ አባቶቻችንን ከግብጽ ምድር ባወጣህ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ሁሉ መካከል እስራኤልን የራስህ ሕዝብ እንዲሆን የመረጥከው መሆኑን በአገልጋይህ በሙሴ አማካይነት ተናግረሃል፡፡
54ሰሎሞንም እጆቹን እንደ ዘረጋ ተንበርክኮ በመሠዊያው ፊት ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ቆይቶ ጸሎቱን ከፈጸመ በኋለ ተነሥቶ ቆመ፡፡
55ድምፁንም ከፍ አድርጎ በዚያ ተሰብስቦ የነበረውን ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ሲል ባረከ፡-
56በገባው የተስፋ ቃል. መሠረት ለሕዝቡ ለእስራኤል ሰላምን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ በአገልጋዩ በሙሴ አማካይነት ከሰጠው መልካም ተስፋ አንድም የቀረ ቃል የለም፡፡
57አምላካችን እግዚአብሔር ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር እንደነበረ ሁሉ ከእኛ ጋርም ይኑር፡፡ ምን ጊዜም አይተወን፤ አይጣለንም፡፡
58ለቀድሞ አባቶቻችን የሰጠውን ትዕዛዞች፣ ደንቦችና ሥርዓቶች በመጠበቅ ወደ እርሱ ልባችንን በማዘንበል ለእርሱ ታዛዦች እንድንሆን ያድርገን፡፡
59የእኔ የአገልጋዩና የሕዝቡ የእስራኤል የየዕለት ፍላጎት ይሟላ ዘንድ ለእግዚአብሔር ያቀረብኳቸው ልመናዎች ቀንና ሌሊት ወደ እግዚአብሔር አምላክ ይቅረቡ፡፡
60የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ መሆኑንና ከእርሱም ሌላ አምላክ አለመኖሩን ያውቃሉ፡፡
61ስለዚህም በዛሬው ቀን በድንጋጌው ለመመላለስና ትእዛዞቹንም ታከብሩ ዘንድ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ለአምላካችን በልባችሁ ታማኞች ሁኑ፡፡
62ስለዚህ ንጉሥ ሰሎሞንና እስራኤላውያን ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ፡፡
63ሰሎሞንም ሃያ ሁለት ሺህ የቀንድ ከብቶችንና አንድ መቶ ሃያ በጎችን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ፡፡ በዚህም ዓይነት ንጉሥ ሰሎሞንና እስራኤላውያን ሁሉ ቤተ መቅደሱን ለእግዚአብሔር የተለየ አድርገው ቀደሱት፡፡
64አሁንም በዚያኑ ቀን ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ያለውን አደባባይ መካከለኛ ክፍል ለእግዚአብሔር የተለየ አድርጎ ቀደሰው፤ ቀጥሎም በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህል ቁርባንና የኅብረት መሥዋዕት፣ የእንስሶች ስብ ሁሉ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ይህን ሁሉ መሥዋዕት መያዝ ስለማይችል ነው፡፡
65በዚያ ቤተ መቅደስ ሰሎሞንና የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ሰባት ቀን ሙሉ ባጠቃላይ ዐሥራ አራት ቀኖች የዳስ በዓል አክብረው ሰነበቱ፤ በስተ ሰሜን ከሐማት መተላለፊያ አንሥቶ በስተ ደቡብ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ ካለው ምድር ሁሉ የመጣው ሕዝበ እጅግ ብዙ ነበር፡፡
66በሚቀጥለው ቀን ሰሎሞን ሕዘቡን ሁሉ አሰናበተ፤ ሁሉም ሰሎሞንን መረቁ እግዚአብሔር ለአገልጋዩ ለዳዊትና ለሕዝቡ፣ ለእስራኤል ስለ አደረገው በጎ ነገር ሁሉ ደስ ብሎአቸው ወደየቤታቸው ሄዱ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።