መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ነገስት 7

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሰሎሞንም ለራሱ የሚሆን ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ቤተ መንግሥቱንም ለመሥራት ዐሥራ ሦስት ዓመት ፈጀበት፡፡
2እርሱም የሊባለኖስ ጫካ ተብሎ የተጠራውን ቤተ መንግሥት ሠራ፡፡ ርዝመቱም ወርዱ አንድ መቶ ክንድ፣ ስፋቱም አምሳ ክንድ፤ ቁመቱም ሠላሳ ክንድ ነበር፡፡ ቤተ መንግሥቱ አራት ረድፍ ሆኖ ከዝግባ እንጨት ምስሶዎች የተሠሩ ሲሆን፣ በምስሶዎቹ ላይ አግዳሚ ሠረገላዎች ተጋድመው ነበር፡፡
3የእነዚህ ዕቃ ቤቶች ጣራ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠራ ነበር፡፡ በምስሶዎቹም ላይ በነበሩ አግዳሚዎች ቤቱ በዝግባ ሳንቃ ተሸፍኖ ነበር፡፡ ምስሶዎቹም በአንዱ ረድፍ ዐሥራ አምስት፣ በአንዱ ረድፍም አምስት እየሆኑ አርባ አምስት ነበሩ፡፡
4ትይዩ የሆኑት የሕንፃው ሁለት ግንቦች እያንዳንዳቸው በመደዳ ሦስት፣ ሦስት መስኮቶች ነበሩአቸው፡፡
5በሮቹና መስኮቶቹ ሁሉ ባለአራት ማእዘን መቃኖች ነበሩአቸው፤ ለእያንዳንዱ ግንብ በረድፍ የተሠሩ ሦስት ሦስት መስኮቶች ነበሩት፤ የእያንዳንዱ ግንብ መስኮቶች ከሌላው ግንብ መስኮቶች ጋር ትይዩ ነበሩ፡፡
6ምሶሶዎች ያሉበትን ቤት ሠራ፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፣ ስፋቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ፤ በእርሱም ፊት ደግሞ ምሶሶና መድረክ ያለበት ወለል ነበረ፡፡
7ሰሎሞን ችሎት ተቀምጦ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበትም የዙፋን አዳራሽ ሠራ፡፡ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ሳንቃ የተሸፈነ ነበር፡
8ከችሎቱም አዳራሽ በስተ ኋላ በሚገኘው ሌላ አደባባይ ሰሎሞን የሚኖርበትን ሕንጻ እንደ ሌሎቹ ሕንጻዎች አድርጎ አሠራ፤ የግብጽ ንጉሥ የፈረዖን ልጅ ለነበረቸው ሚስቱም ተመሳሳይ መኖሪያ ቤት አሠራላት፡፡
9እነዚህ ሁሉ ሕንፃዎችና ታላቁ አደባባይ ጭምር ከመሠረታቸው እስከ ድምድማታቸው በጥሩ ታላላቅ ድንጋዮች አጊጠው የተሠሩ ነበሩ፣ ድንጋዮቹም በዚያ በድንጋይ መፍለጫ ስፍራ በፊትም በኋላም በልክ ተፈልፍለውና ተጠርበው የመጡ ነበር፡፡
10የቤቱ መሠረት የተሠራው በጣም ታላላቅና ውድ በሆኑ ስምንትና ዐሥር ክንድ ርዝመት ባላቸው ድንጋዮች የተሠሩ ነበር፡፡
11እነዚህም ውድና በልክ ከተፈለፈሉ ድንጋዮችና ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠሩ አግዳሚ ሠረገሎች ነበሩ፡፡
12የቤተ መንግሥቱ አደባባይ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገባው በር በእያንዳንዱ ባለ ሦስት ረድፍ የጥርብ ድንጋይ ሕንፃ ላይ አንዳንድ ረድፍ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሠረገላ የተጋደመባቸው ግንቦች ነበሩ፡፡
13ንጉሡ ሰሎሞንም ሔራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ ከተማ አመጣ፡፡
14ሔራም እናቱ ባል የሞተባት የንፍታሌም ነገድ ተወላጅ ነበረች፣ አባቱም የጢሮስ ተወላጅ ሲሆን እርሱም ነሐስ አቅልጦ በመሥራት ጥበብ የሠለጠነ ባለሙያ ነበር፡፡ ሔራም በእጅ ጥበብ ብዙ ልምድ ያለው ብልህ ሰው ነበር፤ እርሱም የነሐስ ጥበብ ሥራ ለንጉሡ ለመሥራት ወደ ንጉሥ ሰሎሞን መጣ፡፡
15ሔራም የእያንዳንዳቸው ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ፣ የዙሪያ ስፋታቸው ዐሥራ አምስት ክንድ ሁለት የነሐስ ምሶሶዎችን ሠራ፡፡
16እንዲሁም በምሶሶዎቹ ላይ የሚቆሙ የእያንዳንዳቸው ቁመት አምሰት ክንድ የሆነ ሁለት የነሐስ ጉልላቶችን ሠራ፡፡
17በምሶሶዎቹም ራስ ላይ የነበሩትን ጉልላቶች ያስጌጡ ዘንድ በሰባት ረድፍ የተሠሩ መረቦችን ሠራ፡፡ አንዱን መረብ ለአንድ ጉልላት ሁለተኛውን መረብ ለሁለተኛው ጉልላት አደረገ፡፡
18ስለዚህም ሔራም ምሶሶዎቹ ጫፍ ላይ ያሉትን ጉልላቶች ለማስጌጥ ሮማኖችን በሁለት ረድፍ ሠራ፡፡ ለየእያንዳንዱም ጉልላት እንዲሁ አደረገ፡፡
19በወለሉ ምሶሶዎች አናት ላይ ያሉት ጉልላቶች ቁመታቸው አራት ክንድ ሲሆን የሱፍ አበባን በሚመስል ሥራ ተጊጠው ነበር፡፡
20እነርሱም ከመረቡ በላይ ባለው ክብ ስፍራ እንዲቆሙ ተደረገ፤ በእያንዳንዱም ጉልላት ዙሪያ በሁለት ረድፍ የተደረደሩ ሁለት መቶ የሮማን ቅርጾች ነበሩ፡፡
21ሔራም ከነሐስ የተሠሩትን ሁለት ምስሶዎች በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ፊት ለፊት አቆማቸው፡፡ ከቤተ መቅደሱም መግቢያ በር በስተደቡብ በኩል የቆመው ምሶሶ «ያኪን» ተብሎ ተጠራ፤ በስተ ሰሜን በኩል የቆመው ምሶሶ ደግሞ «ቦዔዝ» ተባለ፡፡
22በምሶሶዎቹ ጫፍ ላይ የሱፍ አበባ የሚመስሉ ከነሐስ የተሠሩ ጉልላቶች ነበሩ፡፡ የምስሶዎቹም ሥራ በዚህ ዓይነት ተፈጸመ፡፡
23ሔራም ዐሥር ክንድ ጥልቀት፣ የክብ ማእከል ርዝመት አምስት ክንድ ዙሪያ ያለው አንድ ክብ ገንዳ ከነሐስ ሠራ፡፡ ባሕሩም ዙሪያው ሠላሳ ክንድ ነበር፡፡
24የገንዳው አፍ ውጪኣዊ ክፈፍ ሁሉ ከገንዳው ጋር አንድ ወጥ ሆነው በቅል አምሳል ከነሐስ የተሠሩና በሁለት ረድፍ የተደረደሩ ቅርጾች ነበሩት፡፡
25ገንዳውም ከነሐስ በተሠሩ ዐሥራ ሁለት የበሬ ምስሎች ጀርባ ላይ ተቀመጠ። ኮርማዎቹም በየአቅጣጫው ፊታቸውን ወደ ውጪ መልሰው ሦስቱ ወደ ሰሜን፤ ሦስቱ ወደ ደቡብ፣ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ፣ ሦስቱ ወደ ምዕራብ የሚመለከቱ ይመስሉ ነበር፡፡
26የገንዳውም ጎኖች ውፍረት አንድ መዳፍ ነበር፤ የጽዋ ቅርጽ ያለው አበባ የሚመስል የአፉ ክፈፍ የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበረው፤ ይህም ገንዳ አርባ ሺህ ሊትር ያህል ውሃ የሚይዝ ነበር፡፡
27ሔራም ዐሥር መቀመጫዎችን ከነሐስ ሠራ፡፡ የእያንዳንዱ ርዝመት አራት ክንድ፣ ቁመቱ አራት ክንድ፣ ሦስት ክንድ ስፋት ነበር፡፡
28የመቀመጫዎቹ ሥራም እንዲህ ነበር፡፡ የዕቃ መቀመጫዎቹም የተሠሩት በክንፎቹ መካከል ልሙጥ በሆነ ነገር ነበር፡፡
29ልሙጥ በሆነውም ነገር ላይ በአንበሶች፣ በበሬዎችና በኪሩቤል አምሳል የተቀረፁ ምስሎች ነበሩ፡፡ ከአንበሶቹ፣ ከበሬዎቹና ከኪሩቤሉ ቅርፆች ራስጌና ግርጌ የአበባ ጉንጉን የሚመስሉ ቅርፆች ነበሩ፡፡
30እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ከነሐስ የተሠሩ አራት መንኮራኩሮች ነበሩባቸው፡፡ መንኮራኩሮቹም የሚሽከረከሩበት የነሐስ ወስከምቶች ነበራቸው፤ እንዲሁም በአራቱ ማእዘኖች የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበሩ፤ መደገፊያዎቹም የአበባ ጉንጉን በሚመስሉ ቅርፆች አጊጠው ነበር፡፡
31የመታጠቢያ ገንዳውም አንገት አንድ ክንድ ነበር፤ እርሱም ክብ ነበር፤ ቁመቱም አንድ ክንድ ነበር፤ በአንገቱም ላይ ማስጌጫ ቅርፅ ነበረበት፤ የገንዳው ተሸካሚ ግን አራት ማእዘን ነበር እንጂ ክብ አልነበረም፡፡
32የመንኮራኩሮቹም ቁመት አንድ ተኩል ክንድ ነበር፤ መንኮራኩሮችም በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ነሐስ ሥር ነበሩ፤ የመንኮራኩሮቹም ወስከምቶች ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ፡፡
33መንኮራኩሮቹም የሠረገላ መንኮራኩሮችን ይመስሉ ነበር፡፡ ወስከምቶቻቸው፣ ቅርጾቻቸውና አቃፊዎቻቸው ሁሉም ከብረት ቀልጠው የተሠሩ ነበሩ፡፡
34እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ማእዘን በየግርጌአቸው ከእነርሱ ጋር አንድ ወጥ ሆነው ከነሐስ የተሠሩ አራት ደጋፊዎች ነበሩአቸው፡፡
35በእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ጫፍ ዙሪያ ክፈፍ ላይ ተኩል ክንድ ርዝመት ያለው አንድ ክብ ቅርፅ ነበር፤ መደገፊያዎቹና ጠፍጣፋ ነሐሶቹ ከዕቃ ማስቀመጫው ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ፡፡
36በእነዚህ መደገፊያዎችና ጠፍጣፋ ነሐሶች መካከል ባለው ክፍት ቦታ ሁሉ በኪሩቤል፣ በአንበሶችና በዘንባባ ዛፎች አምሳል ሔራም ሠራቸው፡፡ እንዲሁም ዙሪያቸው የአበባ ጉንጉን በሚመስሉ ቅርፆች አጊጠው ነበር፡፡
37እንግዲህ ዐሥሩን ባለመንኩራኩር የዕቃ ማስቀመጫዎች የሠራቸው በዚህ ዓይነት ነበር፡፡ መጠናቸውና ቅርፃቸው እኩል ስለተቀረጹ ሁሉም ተመሣሣይ ነበሩ፡፡
38ሔራም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ዐሥር የነሐስ መታጠቢያ ገንዳዎች ሠራ፡፡ የእያንዳንዱ ገንዳ ዙሪያ አጋማሽ ስፋት አራት ክንድ ያህል ሲሆን፣ አርባ ሊትር ያህል ውሃ ይይዝ ነበር፡፡
39ሔራም አምስቱን የዕቃ ማስቀመጫዎች ከቤተ መቅደሱ በስተደቡብ፣ የቀሩትንም አምስቱን ከቤተ መቅደሱ በስተሰሜን በኩል አቆመ፡፡ ገንዳውን ደግሞ በቤተ መቅደሱ ደቡባዊ ምሥራቅ ማእዘን ላይ አቆመው፡፡
40ሔራምም ድስቶችን፣ መጫሪያዎችንና ጎድጓዳ ሳህኖችን ሠራ፡፡ በዚህ ዓይነትም ለንጉሥ ሰለሞን ሊሠራለት የጀመረውን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ፈጸመ፡፡
41ሁለቱ ምሰሶዎች፣ በምሶሶዎቹም ላይ የነበሩትን ጉልላቶች የሚመስሉ ሳህኖችን፣ በምሶሶውም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጉልላቶች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መረቦች ሠራ፡፡
42በእያንዳንዱ ጉልላት ላይ በመረብ አምሳል የተሠሩት ሰንሰለቶች፣ በእያንዳንዱ ጉልላት ቅርፅ ላይ በሁለት ዘርፍ አንዳንድ መቶ ዙር የሆኑ ከነሐስ የተሠሩ አራት መቶ የሮማን ቅርፆችን ሠራ፡፡
43ዐሥሩ ባለመንኮራኩር የዕቃ ማስቀመጫዎች፣ ዐሥሩ የመታጠቢያ ገንዳዎች ነበሩ፡፡
44ውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ፣ ገንዳውን ደግፈው የሚይዙ የዐሥራ ሁለቱን በሬዎች ቅርፅ ሠራ፡፡
45ድስቶቹን፣ መጫሪያዎቹንና ጎድጓዳ ሳህኖቹን ሠራ፡፡ ሌሎችንም ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሔራም እነዚህን ሁሉ ዕቃዎች ለሰለሞን የሠራለት ከተወለወለ ንፁህ ነሐስ ነበር፡፡
46ንጉሥ ሰለሞን እነዚህን ሁሉ ያሠራው በዮርዳኖስ ሸለቆ በሱኮትና ጻርታን መካከል በሚገኘው በሸክላ ስፍራ ነበር፡፡
47ከነሐስ የተሠራው ይህ ሁሉ ዕቃ እጅግ ብዙ ስለ ነበር፣ ሰለሞን በሚዛን እንዲለካ አላደረገውም፣ ስለዚህ ክብደቱ ምን ያህል እንደሆነ ተወስኖ አልታወቀም፡፡
48ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሰለሞን ያሠራቸው ዕቃዎች ሁሉ በንጹሕ ወርቅ ያጌጡ ነበሩ፡፡ እነርሱም የወርቁ መሠዊያ፣ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ኅብስት ማኖሪያ የወርቅ ጠረጴዛ ናቸው፡፡
49በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት አምስቱ በስተደቡብ፣ አምስቱ ደግሞ በስተ ሰሜን የሚቀመጡት ዐሥሩ የወርቅ መቅረዞች፣ አበባዎች፣ የመብራት ቀንዲሎች፣ የእሳት መቆስቆሻዎች ሁሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፡፡
50ሰሎሞንም ጽዋዎችን፣ የአመድ ማጠራቀሚያዎችን፣ ጎድጓዳ ሳህኖችን፣ የዕጣን ማቅረቢያ ሳህኖችን፣ ማንደጃዎችን፣ ለቅድስተ ቅዱሳን በሮችንና ለቤተ መቅደሱ ውጪኣዊ በሮች የሚያገለግሉ ማጠፊያዎችን ከንጹሕ ወርቅ አሠራ፡፡
51በዚህ ዓይነት ንጉሥ ሰለሞን የቤተ መቅደሱን ሥራ ሁሉ ከፈጸመ በኋላ አባቱ ዳዊት ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት እንዲውል የለየውን ብሩን፣ ወርቁንና ሌላውንም ዕቃ በሙሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት ውስጥ አኖረው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።