መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ነገስት 6

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ስለዚህ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ፡፡ ይህም የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር ከወጡ ከአራት መቶ ሰማኒያ ዓመት በኋላ፣ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ዚፍ ተብሎ በሚጠራው በሁለተኛው ወር ነበር፡፡
2ቤተ መቅደሱም በውስጥ በኩል ርዝመቱ ሃያ ሰባት ሜትር፣ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፣ ቁመቱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር፡፡
3በመግቢያው በር የሚገኘው በረንዳ ቁመቱ አራት ሜትር ተኩል፣ ወርዱ ልክ እንደ ቤተ መቅደሱ ዘጠኝ ሜትር ነበር፡፡
4የቤተ መቅደሱም ሕንፃ ከውስጥ ሰፋ፣ ከውጪ ጠበብ ያሉ መስኮቶች ነበሩት፡፡
5በቤተ መቅደሱን ሕንፃ ፊት ለፊት ግድግዳ ዙሪያ ክፍሎችን ሠራ፤ በዋናው መግቢያ በር በውጪና በውስጥ ክፍሎች ሠራ፤ በዙሪያውም ክፍሎችን አደረገ፡፡
6የታችኛው ፎቅ ክፍል ወርዱ አምስት ክንድ፣ የመካከለኛ ፎቅ ክፍል ስድስት ክንድ፣ የሦስተኛው ፎቅ ክፍል ወርድ ሰባት ክንድ ነበር፤ የእንያዳንዱ ወለል ግንብ ከታች በኩል ካለው የወለል ግንብ የሳሳ ነበር፤ ሠረገሎቹ ወደ ቤተ መቅደሱ ግድግዳ እንዳይገቡ ለማድረግ ከቤተ መቅደሱ ግድግዳ ውጪ ዐረፍቶችን አደረገ፡፡
7ቤተ መቅደሱ የታነጸባቸው ድንጋዮች ተጠርበው የተዘጋጁት በዚያው በተፈለጡበት ቦታ ነበር፤ ቤተ መቅደሱ በሚሠራበት ጊዜ የመዶሻ፣ የመጥረቢያ ወይም የሌላ ብረት ነክ መሣሪያ ድምፅ አይሰማም ነበር፡፡
8ከቤተ መቅደሱ በስተደቡብ በኩል በምድር ደረጃው ላይ መግቢያ በር ነበር፡፡ ከዚያ በደረጃዎቹ መካከለኛ ደረጃ ወደ ላይ ያስኬዳል፡፡ እንዲሁም ከመካከለኛው ደረጃ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ይወስዳል፡፡
9በዚህ ሁኔታ ሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ሕንፃ ሥራ ፈጸመ፤ ጣራውንም ከውስጥ በኩል ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ አግዳሚ ሠረገላና ጠርብ ቤቱን ሸፈነው፡፡
10የእያዳንዱ ፎቅ ቁመት አምስት ክንድ ከፍታ ሆኖ ከውጪ በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ተጠግቶ የተሠራው ባለ ሦስት ፎቅ ተጨማሪ ሕንፃ ከዋናው ሕንፃዎች ከሊባኖስ ዛፍ በተሠሩት አግዳሚ ወራጆች የተያያዘ ነበር፡፡
11የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሰሎሞን እንዲህ ሲል መጣ፡-
12እየተሠራ ያለውን ቤተ መቅሰደስ በተመለከተ፣ በትእዛዜ መንገድ ብትሄድና ቅን ፍርድ ብታደርግ ለአባትህ ለዳዊት እንዳደረግሁ የሰጠሁትን ተስፋ አጸናልሃለሁ፡፡
13በሕዝቤ በእስራኤል መካከል እኖራለሁ፣ ከቶም አልተዋቸውም፡፡
14ስለዚህ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ጨረሰ፡፡
15ከዚያ የቤተ መቅደሱን የውስጥ ግድግዳዎች በሊባኖስ ዝግባ ሠራ፤ ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርበው በተሠሩ ሳንቃዎች ለበደ፤ የወለሉም ጣውላ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠራ ነበር፡፡
16ውስጣዊ ክፍል ከቤተ መቅደሱ በስተ ኋላ ገባ ብሎ ተሠራ፣ የእርሱም ርዝመት ዘጠኝ ሜትር ሲሆን ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተከፈለ ነበር፤ ይህንን ክፍል ቅድሰተ ቅዱሳን ውስጠኛ ክፍል እንዲሆን ነው፡፡
17ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት የሚገኘውም የተቀደሰ ክፍል ርዝመት አርባ ክንድ ነበር፡፡
18የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሳንቃዎች በአበባ እንቡጦችና በፈኩ አበባዎች ቅርጽ አጊጠው ነበር፤ ውስጡም ሁሉ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ ስለ ተለበጠ የግንቡ ድንጋዮች አይታዩም ነበር፡፡
19ሰሎሞንም ከቤተ መቅደሱ ውስጥ በስተኋላ በኩል የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት የሚቀመጥበት ውስጣዊ ክፍል አዘጋጀ፡፡
20ይህም ውስጣዊ ክፍል ርዝመቱ ዘጠኝ ሜትር፣ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፣ ቁመቱ ዘጠኝ ሜትር ሲሆን፣ በሙሉ በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ነበር፤ መሠዊያውም ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተለበጠ ነበር፡፡
21ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን በውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ እርሱም ክፈፉን በተሸጋገሩ የወርቅ ሰንሰለቶች አስጌጠው፡፡
22የቅድስት ቅዱሳኑ ውስጠኛ በወርቅ ለበጠው፡፡
23ሰሎሞንም እያንዳንዱ ዐሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት በሁለት ኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ሥዕሎች በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ሠራ፡፡
24የኪሩቡ አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ፤ የኪሩቡም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስከ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ ዐሥር ክንድ ነበረ፡፡
25ሁለተኛውም ኪሩብ ዐሥር ክንድ ነበረ፤ የሁለቱም ኪሩቤል ቅርጽና መጠን ተመሳሳይ ነበር፡፡
26የአንዱ ኪሩብ ቁመት ዐሥር ክንድ ነበረ፤ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ፡፡
27ኪሩቤልንም በቅድስት ቅዱሳኑ ውስጥ እንዲቆሙ አደረገ፤ ስለዚህም የተዘረጉ ሁለቱ ክንፎቻቸው በክፍሉ መካከለኛ ቦታ ላይ ተገናኝተው ሌሎቹ ሁለቱ ክንፎቻቸው ደግሞ በተዘረጉበት አቅጣጫ ግንቦቹን ይነኩ ነበር፡፡
28ሰሎሞንም ሁለቱን ኪሩቤል በወርቅ ለበጣቸው፡፡
29የዋናውን ክፍልና የውስጠኛውን ክፍል ግንቦች በሙሉ በኪሩቤል፣ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው፡፡
30እርሱም ከውስጥና ከውጪ በኩል ያሉትን ክፍሎች ወለል በወርቅ ለበጣቸው፡፡
31ከወይራ እንጨት የተሠራ ሁለት ተካፋች በር በቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ እንዲቆም አደረገ፤ በሩም አምስት ማእዘን ያለው ሆኖ አናቱ ላይ ቀጥ ብሎ የተሠራ ቅስት ነበር፡፡
32ሁለቱን በሮች በኪሩቤል፤ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው፤ እርሱም በሮቹን፣ ኪሩቤልን፣ የዘንባባ ዛፎቹንና ቅርጾቹን በወርቅ ለበጣቸው፡፡
33በዚህ ዓይነት ሰሎሞን ደግሞ ወደ ዋናው ክፍል ለሚያደርሰው መግቢያ በር ከወይራ እንጨት የተሠራ ባለ አራት ማእዘን ክፈፍ አበጀለት፡፡
34ሁሉቱንም በሮች ከዝግባ እንጨት ሠራ፤ አንዱ በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፤ ሁለተኛውም በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፡፡
35እነርሱን ሙሉ በሙሉ በወርቅ በተለበጡ በኪሩቤል፣ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው፡፡
36በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አንድ የውስጥ አደባባይ ሠራ፤ በዚህም አደባባይ ዙሪያ በየሦስቱ ዙር የድንጋይ ረድፍ አንድ የሊባኖስ ዛፍ ሠረገላ ሳንቃ የተጋደመበት ግንብ አደረገ፡፡
37የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረቱ የተጣለው ሰሎሞን በነገሠ በአራተኛው ዓመት ዚፍ ተብሎ በሚጠራው በሁለተኛው ወር ነበር፡፡
38ሰሎሞን በነገሠ በዐሥራ አንደኛ ዓመቱ ቡል ተብሎ በሚጠራው በስምንተኛው ወር ላይ የቤተ መቅደሱ ሁሉም ክፍሎችና ሁሉም ንድፍ ተጠናቀቀ፡፡ ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ሰባት ዓመት ወሰደበት፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።