መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ነገስት 5

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ከዳዊት ጋር ወዳጅነቱን አጽንቶ ቆይቶ ነበር፤ እርሱም ሰሎሞን በአባቱ በዳዊት ፈንታ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ መልእክተኞቹን ላከ፡፡
2ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፡፡
3አባቴ ዳዊት በዙሪያው ከነበሩት ከብዙ ጦርነቶች የተነሣ ለእግዚአብሕሔር አምላክ በስሙ ቤተ መቅደስ ለመሥራት አለመቻሉን ታውቃለህ፤ እግዚአብሔርም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ጠላቶቹን ከእግሩ በታች አንበረከካቸው፡፡
4አሁን ግን አምላኬ እግዚአብሔር በሁሉም ድንበር እረፍት ሰጥቶኛል፡፡ ምንም ዓይነት ጠላት ወይም አደጋ የሚጥል የለብኝም፡፡
5ስለዚህ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት፡- ከአንተ በኋላ የማነግሠው ልጅህ ለእኔ በስሜ ቤተ መቅደስ ይሠራልኛል ሲል ተናግሮት ስለነበር፤ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር በስሙ ቤተ መቅደስ ለመሥራት አሁን አቅጃለሁ፡፡
6ስለዚህም የሊባኖስ ዛፍ እንጨት የሚቆርጡ ሰዎች ወደ ሊባኖስ ላክልኝ፡፡ የእኔም ሰዎች ከእነርሱ ጋር አብረው እንዲሠሩ አደረጋለሁ፤ ለአንተም ሰዎች የምትወስነውን ደመወዝ እከፍላለሁ፤ አንተም እንደምታውቀው፣ የእኔ ሰዎች ስለ ዛፍ አቆራረጥ የአንተን ሰዎች ያህል ዕውቀት የላቸውም፡፡
7ኪራም የሰሎሞን መልእክት ሲደርሰው እጅግ ተደሰቶ፣ በእርሱ ፈንታ ተተክቶ በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ እንዲነግሥ ይህን የመሰለ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠው እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን አለ፡፡
8ከዚህ በኋላ ኪራም ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ለሰሎሞን ላከ፤ የላክልኝን መልእክት ሰምቻለሁ፤ የምትፈልገውን ሁሉ፣ የሊባኖሱን ዛፍና የዝግባውን ግንድ አዘጋጅልሃለሁ፡፡
9የእኔ ሰዎችም ግንዶችን ከሊባኖስ ወደ ባሕር ያወርዳሉ፤ አስረውም አንተ ወደምትፈልገው ጠረፍ በውኃ ላይ ተንሳፍፈው እንዲደርሱ ያደርጋሉ፤ በዚያም የእኔ ሰዎች ማሰሪያውን ፈተው ለአንተ ሰዎች ያስረክቡአቸዋል፤ አንተም በበኩልህ ለቤተ ሰቤ ምግብ በመስጠት ፍላጎቴን ትመልስልኛለህ፡፡
10በዚህ ዓይነት ኪራም ለሰሎሞን የሚያስፈልገውን የሊባኖሱን ዛፍና የዝግባ ግንድ ሁሉ ሰጠው፡፡
11ሰሎሞንም በበኩሉ ለኪራም ቤተ ሰቦች ቀለብ የሚሆን ሃያ ሺህ መስፈሪያ ስንዴና ሃያ መስፈሪያ ንጹሕ ዘይት ሰጠ፡፡ ይህንንም በየዓመቱ ይሰጥ ነበር፡፡
12እግዚአብሔር አስቀድሞ የሰጠውን የተስፋ ቃል በመጠበቅ ለሰሎሞን ጥበብ ሰጠው፤ በሰሎሞንና በኪራም መካከል ሰላም ነበር፤ ሁለቱም የጋራ ስምምነት አደረጉ፡፡
13ንጉሥ ሰሎሞን ከመላው እስራኤል ሠራተኞችን መለመለ፤ የግዳጅ ሠራተኞችም ሠላሳ ሺህ ነበሩ፡፡
14ዐሥር ሺህ የሚያህሉትን ለአንድ ወር ወደ ሊባኖስ በፈረቃ ላካቸው፡፡ ለአንድ ወር በሊባኖስ ሁለት ወር በቤታቸው ነበሩ፡፡ አዶኒራም የተባለው ሰው በግዳጅ ሠራተኞች ላይ ኃላፊ ነበር፡፡
15ንጉሥ ሰሎሞን በኮረብታማው አገር ድንጋይ የሚፈልጡ ሰማኒያ ሺህ፣ የተፈለጠውን ድንጋይ ተሸክመው የሚያመጡ ሰባ ሺህ ሰዎች ነበሩት፡፡
16የእነዚህ ሠራተኞች የበላይ ሆነው ሥራውን የሚቆጣጠሩ ሦስት ሺህ ሦስት መቶ ሰዎች ነበሩ፡፡
17በዚህ ዓይነት ሠራተኞቹ በንጉሥ ሰሎሞን ትእዛዝ ለቤተ መቅደሱ መሠረት የሚሆን ታላላቅ ድንጋዮችን ፈለጡ፡፡
18የሰሎሞንና የኪራም አናጢዎችና ግንበኞች የጌባላውያንም ሰዎች ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የሚያስችላቸውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ አዘጋጁ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።