መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ነገስት 3

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሰሎሞን የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ሴት ልጅ በማግባት ከንጉሡ ጋር ወዳጅነት መሠረተ። የፈርዖንንም ልጅ አምጥቶ ቤተ መንግሥቱን፣ ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ ቅጥር ዙሪያውን ሠርቶ እስኪጨርስ ድረስ በዳዊት ከተማ አኖራት።
2በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደሱ ገና አልተሠራም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ በየኮረብታው መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር።
3ሰሎሞን እግዚአብሔርን ይወድ ነበር፤ የአባቱንም የዳዊትን መመሪያ ይጠብቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ እንስሶችን እያረደ በተለያዩ ኮረብቶች ላይ መሥዋዕት ያቀርብና ዕጣንም ያጥን ነበር።
4ታላቅ መሠዊያ የሚገኘው በገባዖን ስለነበር አንድ ቀን ንጉሥ ሰሎሞን መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ። በዚያም መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።
5እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት በገባዖን ለሰሎሞን በሕልም ተገለጠለትና ምን እንድሰጥህ ትፈልጋህ? ጠይቅ አለው።
6ሰሎሞንም እንዲህ ሲል መለሰ፡- አገልጋይህ የነበረው አባቴ ዳዊት፣ ታማኝና ቅን ሰው በመሆኑ ጽኑ ፍቅርህን አሳይተኸዋል። ዛሬም በእርሱ ፈንታ በዙፋኑ የሚቀመጥ ልጅ በመስጠት ታላቅና ጽኑ የሆነውን የማያቋርጥ ፍቅርህን ገልጠህለታል።
7እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ እነሆ እኔ በዕድሜዬ ልጅ ብሆንም በአባቴ ቦታ ተተክቼ እንድነግሥ ፈቃድህ ሆኖአል። እኔም መግባትንና መውጣትን የማልችል ነኝ።
8እነሆ፣ የአንተ እንዲሆን በመረጥከውና ከብዛቱ የተነሣ ሊቆጠር በማይችል ሕዝብ መካከል አለሁ።
9ስለዚህ ክፉውንና በጎውን በመለየት ሕዝብህን በማስተዋል በትክክኛ ፍርድ ለመምራት የሚያስችለኝን ጥበብ ስጠኝ። ይህ ካልሆን ይህን ታላቅ ሕዝብህን ሊመራ ማን ይችላል?
10ይህ የሰሎሞን ጥያቄ እንግዚአብሔርን ደስ አሰኘው፤
11ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ አለው፡- ለራስህ ረጅም ዕድሜ ወይም ሀብት ለማግኘት ወይም ጠላቶችህ እንዲጠፉልህ መመኘት ሳይሆን በትክክለኛ ፍርድ ማስተዳደር የምትችልበትን ጥበብ ጠይቀሃል።
12እነሆ የጠየቅኸውን አደርጋለሁ፤ እንዲያውም ማንም ሰው ከዚህ በፊት ካገኘውና ወደ ፊት ሊያገኘው ከሚችለው የሚበልጥ ጥበብንና አስተዋይነትን እሰጥሃለሁ።
13ከዚህም በላይ አንተ ያልጠየቅከውንም ሁሉ ጨምሬ ሰጥቼሃለሁ፤ ይኸውም በዘመንህ ማናቸውም ንገሥታት ያላገኙትን ብጽግናና ክብር አሰጥሃለሁ።
14አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ብትሄድ ለእኔም ብትታዘዝ ሕጌንና ትእዛዞቼንም ብትፈጽም ረጅም ዕድሜ እሰጥሃሁ።
15ሰሎሞን ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እግዚአብሔር በሕልም ተገልጦ ያነጋገረው መሆኑን ተገነዘበ፤ ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆሞ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ከዚህም በኋላ ለአገልጋዮቹ ሁሉ ግብዣ አደረገ።
16አንድ ቀን ሁለት ሴተኛ አዳሪዎች መጥተው በሰሎሞን ፊት ቀረቡ፡፡
17ከእነርሱም አንደኛይቱ እንዲህ አለች ንጉሥ ሆይ ይህች ሴትና እኔ በአንድ ቤት አብረን ስንኖር፣ በዚያውም በምንኖርበት ቤት ወንድ ልጅ ወለድኩ።
18እኔ በወለድኩ በሦስተኛው ቀን እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደች። በዚያ ቤት ውስጥ ከሁለታችን በቀር ሌላ ማንም አልነበረም።
19ከዕለታት አንድ ቀን ሌሊት በላዩ ላይ ተኝታበት ስለ ታፈነ ልጇ ሞተ።
20እኔ ተኝቼ ሳለሁ ሌሊት ተነሥታ ታቅፌው የተኛሁትን ልጄን ወስዳ በእርስዋ አልጋ ላይ ካስተኛች በኋላ የሞተውን ልጅዋን አምጥታ በእኔ አልጋ ላይ በጎኔ አስተኛችው።
21በማግስቱ ማለዳ ተነሥቼ ልጄን ለማጥባት ስዘጋጅ ሞቶ አገኘሁት፤ ትኩር ብዬ ስመለከተው እኔ የወለድኩት ልጅ አለመሆኑን ተገነዘብኩ።
22ሁለተኛይቱ ሴት ግን አይደለም፣፣ በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፣ የሞተው ግን የአንቺ ነው አለች። የመጀመሪያይቱ ሴት አይደለም የሞተው የአንቺ ነው፤ በሕይወት ያለው ግን የእኔ ልጅ ነው አለች። በዚህ ዓይነት በንጉሡ ፊት ተከራከሩ።
23ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን አንደኛዋ በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፣ የሞተው ግን የአንቺ ነው ትላለች፤ ሌላይቱም ደግሞ አይደለም የአንቺ ልጅ ሞቶአል፤ የእኔ ልጅ በሕይወት ያለው ነው ትላታለች አለ።
24ንጉሡም ሰይፍ እንዲያመጡለት አዘዘ፤ ሰይፍም አመጡለት።
25በሉ እንግዲህ በሕይወት ያለውን ልጅ ለሁለት ቁረጡና ለእያንዳንዱ ሴት ግማሽ አካሉን ስጡ ሲል አዘዘ፡፡
26እውነተኛይቱ ግን ለልጅዋ በመራራት አዝና ንጉሥ ሆይ፣ እባክህ ልጁን አትግደለው፤ ለእርስዋ ይሰጣት አለች። ሌላይቱ ሴት ግን፣ ለእኔም ለእርስዋም አይሁን፤ ለሁለት ይቆረጥ አለች።
27ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ሕፃኑን አትግደሉት፤ እውነተኛይቱ እናት እርስዋ ስለሆነች ለመጀመሪያይቱ ሴት ስጡአት ሲል አዘዘ።
28እስራኤላውያን ይህን የፍርድ ውሳኔ በሰሙ ጊዜ ሰሎሞን የሕዝብ ጉዳዮችን በትክክለኛ ፍርድ የሚወስንበትን ጥበብ እግዚአብሔር የሰጠው መሆኑን ስለ ተገነዘቡ ታላቅ አክብሮት ሰጡት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።