መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ነገስት 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ዳዊት የሚሞትበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን ጠርቶ እንዲህ ሲል አዘዘው፤
2እነሆ እኔ ሰው ሁሉ እንደሚሞት የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ እንግዲህ በርታ ቆራጥ ሰው ሁን፡፡
3አምላክህ እግዚአብሔር እንድታደርግ የሚያዝህን ሁሉ አድርግ፣ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ የምታደርገው ማናቸውም ነገር እንዲከናወንልህ በሙሴ አማካይነት በተሰጠው ሕግ የተጻፉትን የእግዚአብሔርን ሕግ ትእዛዝ፣ ሥርዓትና ፈቃድ ሁሉ ጠብቅ፡፡
4በዚህ ሁሉ ታዛዥ ሆነው ቢኖሩ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በፊቴ በቅንነት ቢመላለሱ በእስራኤል ዙፋን ላይ ነግሦ የሚገዛ ዘር አላሳጣህም ብሎ የነገረኝን የተስፋ ቃል ይፈጽማል፡፡
5የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ በእኔና የእስራኤል ሕዝብ የጦር መሪዎች በነበሩት በሁለቱ፣ በኔር ልጅ በአበኔርና በዬቴር ልጅ በአሜሳይ ላይ ያደረገውን ታውቃለህ፤ ሁለቱ በጦርነት ጊዜ ላፈሰሱት ደም ተበቅሎ በሰላም ጊዜ እነርሱን በመግደል የወገቡን ቀበቶና የእግሩን ጫማ በደም በከለ።
6እንግዲህ ባለህ ጥበብ በኢዮአብ ላይ ልትፈጸምበት የሚገባውን አድርግ፤ ዕድሜ ጠግቦ በሰላም እንዲሞት አትፍቀድለት።
7ይሁን እንጂ የገለዓዳዊው የቤርዜሊ ልጆች ከወንድምህ ከአቤሌሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ ወደ እኔ መጥተው የቸርነት ሥራ ስላደረጉልኝ፣ መልካም አድርግላቸው፤ በማዕድህም ከሚመገቡ መካከል ይሁኑ።
8ከዚህም ጋር መረሳት የሌለበት የብንያም ክፍል በሆነችው በባሑሪም ከተማ ውስት የሚኖረው የጌራ ልጅ ሳሚ ወደ መሃናይም በሄድኩበት ቀን በእኔ ላይ የስደብ ውርጅብኝ አውርዶብኛል፤ ይሁን እንጂ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ባገኘኝ ጊዜ እንደማላስገድለው በእግዚአብሔር ስም ምየለታለሁ።
9ስለዚህ አንተ እርሱንም ከቅጣት ነጻ አታድርገው። አንተ ጥበበኛ ሰው ስለሆንህ ምን መደረግ እንዳለበት ታውቃለህ። በሸመገለም ጊዜ በሞት ትቀጣዋለህ፡፡
10ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ።
11ዳዊት በኬብሮን ሰባት ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት፣ በድምሩ አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ነገሠ።
12ሰሎሞንም በአባቱ ዙፋን ተተክቶ ነገሠ፤ የመንግሥቱም ሥልጣን እጅግ የጸና ሆነ።
13የአጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ። ቤርሳቤህም ወደ እኔ የመጣኸው በሰላም ነውን? ስትል ጠየቀችው፤ እርሱም አዎን በሰላም ነው ሲል መለሰላት።
14ቀጠል አድርጎም እኔ የምጠይቅሽ ጉዳይ አለኝ አላት። እርስዋም ጉዳይህን ተናገር አለችው።
15አዶንያስም እንዲህ አላት፣ ንጉሥ መሆን የሚገባኝ እኔ እንደ ነበርኩና ይህንንም የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በተስፋ ይጠባበቅ እንደ ነበር አንቺ ታውቂያለሽ። ነገር ግን ጉዳዩ ከእግዚአብሔር ስለ ተወሰነ ነገሩ ተለውጦ መንግሥቱ ለወንድሜ ተሰጥቶአል።
16አሁንም የምጠይቅሽ አንድ ጉዳይ ስላለኝ እምቢ በማለት አታሳፍሪኝ። ቤርሳቤህም ጉዳይህን ተናገር አለችው።
17እርሱም እንዲህ አላት፡- ንጉሥ ሰሎሞን አንቺን እምቢ እንደማይልሽ አውቃለሁ፤ ስለዚህ አቢሳ ተብላ የምትጠራውን ሱነማይት ልጃገረድ ሚስት ትሆነኝ ዘንድ እንዲሰጠኝ እባክሽ አማልጅኝ አላት።
18እርስዋም መልካም ነው፤ ይህን ለንጉሡ እነግርልሃለሁ አለችው።
19ስለዚህ ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጉዳይ ልትነግረው ወደ ንጉሡ ገባች። ንጉሡም ከተቀመጠበት ተነሥቶ እናቱን እጅ በመንሣት ተቀበላት። እርሱም በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ በኋላ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት።
20እርስዋም እንድትፈጽምልኝ የምጠይቅህ አንድ ትንሽ ጉዳይ አለኝ፣ እባክህ እምቢ በማለት አታሳፍረኝ አለችው። ንጉሡም እናቴ ሆይ አላሳፍርሽምና ጠይቂኝ አላት።
21እርስዋም ወንድምህ አዶንያስ አቢሳን እንዲያገባት ፍቀድለት አለችው።
22ንጉሡም አቢሳን ለሚስትነት እንድሰጠው ብቻ ለምን ትጠይቂኛሽ? መንግሥቴንም ጭምር እንድለቅለት ለምን አልጠየቅሽኝም? እርሱ ታላቅ ወንድሜ ነው፤ ለምንስ ለካህኑ አብያታርና ለኢዮአብም ልዩ አስተያየት እንዳደርግላቸው አትጠይቂላቸውም? አላት።
23ከዚህ በኋላ ሰሎሞን፣ በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ሲል ማለ፡- አዶንያስ ይህን በመናገሩ በሕይወቱ እንዲከፍል ባላደርግ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ በበለጠም ይቅጣኝ አለ።
24እግዚአብሔር በአባቴ በዳዊት ዙፋን ላይ አስቀምጦኝ መንግሥቴን የጸና አድጎልኛል፤ ይህን መንግሥት ለእኔና ለዘሮቼ በመስጠት ቃሉን ጠብቆአል፤ እንግዲህ አዶንያስ በዚህ በዛሬው ቀን በሞት እንደሚቀጣ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ።
25ስለዚህ አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን ለዮዳሄ ልጅ ለበናያስ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያስም ሄዶ አዶንያስን ገደለው።
26ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ካህኑን አብያታርን እንዲህ አለው፡- በአናቶት ወዳለው እርሻህ ሂድ፤ አንተ በሞት ልትቀጣ ይገባህ ነበር፣ ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለተሸከምህ፣ ከእርሱም ጋር የመከራው ሁሉ ተካፋይ ስለ ነበርክ እኔ አሁን አልገድልህም።
27ከዚህ በኋላ ሰሎሞን አብያታርን የእግዚአብሔር ካህን ሆኖ ከሚያገለግልበት የክህነት ሥልጣን ሽሮ አባረረው፤ በዚህም ዓይነት እግዚአብሔር በሴሎ ስለ ካህኑ ዓሊ፣ ስለ ትውልዱ የተናገረው ቃል ተፈጸመ።
28የአቤሌሎም ደጋፊ ባይሆንም የአዶንያስ ደጋፊ የነበረው ኢዮአብ፣ ይህን የተፈጸመውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ስለዚህም ሸሽቶ ወደ ጌታ እግዚአብሔር ድንኳን ሄደ፤ በዚያም የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ተማጠነ።
29ኢዮአብ ወደ ጌታ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መገኘቱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ ኢዮአብን እንዲገድለው ለበናያስ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡
30እርሱም ወደ ጌታ እግዚአብሔር ድንኳን ሄዶ ኢዮአብን ከዚህ ድንኳን እንድትወጣ ንጉሡ አዞሃል አለው። ኢዮአብ ግን፣ አልወጣም እዚሁ እሞታለሁ አለ። በናያስም ተመልሶ ኢዮአብ ያለውን ለንጉሡ ነገረው።
31ሰሎሞን በናያስን እንዲህ አለው፡- ኢዮአብ እንዳለህ ግደለውና ቅበረው፤ በዚህ ሁኔታ ኢዮአብ ካፈሰሰው ንጹሕ ደም የእኔንና የአባቴን ቤት የነጻን ታደርገናለህ።
32አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ ስለ ገደላቸው ስለ እነዚያ ሁለት ሰዎች ደም እግዚአብሔር ኢዮአብን ይቀጣዋል፤ ኢዮአብ ከእርሱ የተሻሉትን ሁለት ንጹሓን ሰዎች ገድሎአል፤ እነርሱም የአስራኤል ጦር አዛዥ አበኔርና የይሁዳ ጦር ኣዛዥ አሜሳይ ነበሩ።
33ኢዮአብ እነዚህን ሰዎች በመግደሉ ደማቸው በእርሱና በዘሮቹ ለዘለዓለም ይመለስባቸው። ነገር ግን ለዳዊትና ለዘሮቹ፣ ለቤቱና በዙፋኑ ለሚቀመጡት የእግዚአብሔር ሰላም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር።
34ስዚህ በናያስ በታዘዘው መሠረት ኢዮአብን ገደለው፤ በቤቱም አጠገብ በሚገኘው በረሓ ተቀበረ።
35ንጉሥ ሰሎሞን በኢዮአብ ፈንታ በናያስን የሠራዊት አዛዥ፣ በአብያታርም ፈንታ ሳዶቅን ካህን አድርጎ ሾማቸው።
36ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ ሲል አዘዘው፡- በዚህ በኢየሩሳሌም የራስህን መኖሪያ ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ከዚያ የትም እንዳትሄድ፤
37ከከተማይቱ ወጥተህ የቄድሮንን ወንዝ ተሻግረህ ብትገኝ በእርግጥ ትሞታለህ፤ ለደምህም ተጠያቂው ራስህ ነህ።
38ሳሚም ንጉሥ ሆይ፣ ውሳኔህ መልካም ነው። አገልጋይህ አንተ ጌታዬ እንዳልከው አደርጋለሁ ሲል መለሰ። ስለዚህ በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ።
39ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ሁለቱ የሳሚ አገልጋዮች የመዓካ ልጅ ወደ ሆነው አንኩስ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ጌት ንጉሥ ኮብልለው ሄዱ፤ ሳሚም ባሪያዎቹ በጌት መኖራቸው ተነገረው።
40ሳሚም አህያውን ጭኖ እነርሱን ለመፈለግ በጌት ወደሚኖረው ወደ ንጉሥ አንኩስ ሄደ፤ እነርሱንም በዚያ ስላገኛቸው ወደ ቤት መልሶ አመጣቸው።
41ንጉሥ ሰሎሞን ሳሚ ከኢየሩሳም ወደ ጌት ሄዶ መመለሱን ሰማ።
42ንጉሡም ሳሚን አስጠርቶ ከኢየሩሳሌም እንዳትወጣ በእግዚአብሔር ስም አስምዬህ አልነበረምን? ወጥተህ ብትገኝ ግን በእርግጥ እንደምትሞት አስታውቄህ አልነበረምን? በዚህስ ተስማምተህ ትእዛዜን እንደምትፈጽም ቃል ገብተህልኝ አልነበረምን? አለው።
43ታዲያ በእግዚአብሔር ስም ከማልህ በኋላ ትእዛዜንስ ስለምን አላከበርክም?
44በአባቴ በንጉሥ ዳዊት ላይ የፈጸምከውን በደል ሁሉ በሚገባ ታውቃለህ፤ አንተ ስላደረግኸው ክፉ ነገር እግዚአብሔር ራሱ ይቀጣሃል።
45እኔን ግን እግዚአብሔር ይባርከኛል፤ የዳዊት መንግሥትም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።
46ከዚህም በኋላ ለዮዳሄ ልጅ ለበናያስ ሳሚን እንዲገድል ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያስም ሄዶ ሳሚን ገደለው፤ በዚህም ዓይነት መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ የጸና ሆነ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።