1ከጥቂት ጊዜ በኋላ ናቡቴ ተብሎ የሚጠራ ሰው በኢይዝራኤል በሚገኘው በንጉሥ አክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ የራሱ ርስት የሆነ አንድ የወይን ተክል ቦታ ነበረው፡፡
2አንድ ቀን አክዓብ ናቡቴን የወይን ተክል ቦታህን ስጠኝ፤ በቤተ መንግሥቴ አጠገብ ስለ ሆነ የአትክልት ቦታ ላደርገው እፈልጋለሁ፤ በምትኩ ከእርሱ የተሻለ የወይን ተክል ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ልትሸጠው ብትፈልግም የተሻለ ዋጋ እከፍልሃለሁ አለው፡፡
3ናቡቴም ይህንን የወይን ተክል ቦታ የወረስኩት ከቅድም አያቶቼ ነው፤ ለአንተ ከመስጠትስ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ! ሲል መለሰለት፡፡
4አክዓብ ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ ከአባቶቼ የወረስኩትን ለአንተ አልሰጥህም ስላለው በንዴት እየተበሳጨ ወደ ቤቱ ገባ፤ ፊቱንም ወደ ግድግዳ አዙሮ በአልጋው ላይ ተጋደመ፤ ምግብ መብላትም አልፈቀደም፡፡
5ሚስቱም ኤልዛቤል ወደ እርሱ ቀርባ እንደዚህ ያበሳጨህ ነገር ምንድን ነው? ስለምንስ ምግብ አትበላም? ስትል ጠየቀችው፡፡
6እርሱም እኔን ያበሳጨኝ ከናቡቴ ያገኘሁት መልስ ነው፤ ይኸውም የእርሱን የወይን ተክል ቦታ እንድገዛ ወይም ከፈለገ ልዋጩን እንድሰጠው ብጠይቀው የወይን ተክል ቦታውን አልሰጥህ ብሎ አናደደኝ ሲል መለሰላት፡፡
7ኤልዛቤልም እንግዲህ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ሆነህ ሳለህ እንደዚህ መሆን ይገባሃልን? ይልቅስ ተነሥ ተደሰት፤ እህል ውሃም ቅመስ፡፡ እኔ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ እንድታገኝ አደርጋለሁ አለችው፡፡
8ስለዚህ እርስዋ ደብዳቤ ጽፋና በአክዓብ ስም ፈርማ የእርሱን ማኅተም አተመችበት፤ ደብዳቤውንም ናቡቴ ወደሚኖርባት ወደ ኢይዝራኤል ባለሥልጣኖችና ሽማግሌዎች ላከች፡፡
9ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፡- የአንድ ቀን ጾም አውጁ፤ ሕዝቡንም በአንድነት ሰብስቡ፤ ለናቡቴም የክብር ቦታ ስጡት፤
10እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው የሚናገሩ ሁለት የሐሰት ምስክሮችንም አቅርቡ፤ ከዚያ በኋለ ናቡቴን ከከተማው ውጪ አወጥታችሁ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት፡፡
11ስለዚህ የኢይዝራኤል ባለሥልጣኖችና ሽማግሌዎችም በደብዳቤው እንደተገለጸው ኤልዛቤል ያዘዘቻቸውን አደረጉ፡፡
12የአንድ ቀን ጾም አወጁ፤ ሕዝቡንም በአንድነት ሰበሰቡ፤ ለናቡቴም የክብር ቦታ ሰጡት፡፡
13ሁለቱም የሐሰት ምስክሮች ተነሥተው ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው በሕዝቡ ፊት በሐሰት መሰከሩበት፤ ስለዚህም ከከተማይቱ ውጪ በመውሰድ በድንጋይ ወግረው ገደሉት፡፡
14ናቡቴ ተወግሮ ተገድሎአል የሚል መልእክትም ወደ ኤልዛቤል ላኩ፡፡
15ኤልዛቤልም መልእክቱን እንደ ተቀበለች ወዲያውኑ አክዓብን ናቡቴ ሞቶአል፤ አሁን ተነሥተህ ሂድና ለአንተ ለመሸጥ እምቢ ያለውን የወይን ቦታ ርስት አድርገህ ውሰድ አለችው፡፡
16አክዓብም የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ ለመውረስ ወዲያውኑ ተነሥቶ ሄደ፡፡
17ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስቢያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፡፡
18ተነሥተህ ሂድና የእስራኤልን ንጉሥ አከዓብን በሰማርያ አግኘው፤ እርሱ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ ለመውረስ ሄዶአል፣ በዚያው ታገኘዋለህ፤
19እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ መናገር አለብህ፣ ናቡቴን ገድለህ ሀብቱንም ወሰድክበትን? ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ የናቡቴን ደም ውሾች በላሱበት ስፍራ የአንተንም ደም እንደዚሁ ይልሱታል።
20አክዓብ ኤልያስን ባየው ጊዜ ጠላቴ ሆይ አገኘኸኝን? አለው፡፡ እርሱም እንዲህ አለ፣ አዎን አግኝቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ለማድረግ ራስህን ሸጠከውን? አለው፡፡
21ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል፣ እነሆ በአንተ ላይ መቅሠፍትን አመጣብሃለሁ፤ አንተን ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ ከቤተ ሰብህም ውስጥ ወንድ የሆነውን ሁሉ ባሪያ ሆነ ነጻ ሰው አጠፋለሁ፡፡
22እስራኤልን ወደ ኃጢአት በመምራታችሁ ቁጣዬን ስለ አነሣሣህ ቤተ ሰብህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ንጉሥ ኢዮርብዓም ቤተ ሰብና እንደ አኪያ ልጅ እንደ ንጉሥ ባኦስ ቤተ ሰብ ለጥፋት የተጋለጠ ይሆናል፡፡
23ስለ ኤልዛቤልም እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፡- በኢይዝራኤል ከተማ ውስጥ ሬሳዋን ውሾች ይበሉታል፡፡
24ከአክዓብም የሆነውን ሁሉ በከተማው ውስጥ የሚሞተውን ማንኛውንም ሰው ውሾች ይበሉታል፤ በገጠርም በየሜዳው የሚሞተውን ሁሉ የሰማይ አሞራዎች ይበሉታል፡፡
25በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር በማድረግ ለኤልዛቤል ኃጢአት ራሱን አሳልፎ የሸጠ አክዓብን የሚመሰል ማንም አልነበረም፡፡ ይህን ሁሉ ያደረገው ሚስቱ ኤልዛቤል ወደ ክፋት ስለ መራችው ነው፡፡
26አክዓብ ከፈጸመው አሳፋሪ በደል ሁሉ ዋናው እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት ነቃቅሎ ያጠፋቸውን የአሞራውያንን ጣዖት ማምለኩ ነበር፡፡
27አከዓብም ይህንን በሰማ ጊዜ፡- ልብሱን ቀዶ ማቅ ለበሰ፤ ማቁን እንደ ለበሰ ይተኛ ነበር፤ ሲሄድም ከጭንቀቱ ብዛት የተነሣ አዝኖ ነበር፡፡
28የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ቴስቢያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፡-
29አክዓብ በእኔ ፊት ራሱን እንዴት እንዳዋረደ ተመልክተሃልን? እግዚአብሔርም በፊቴ ራሱን ስላዋረደ በሕይወቱ ዘመን መቅሠፍትን በአክዓብ ቤተ ሰብ ላይ አላመጣበትም፤ የማመጣውም በልጁ ዘመን ይሆናል፡፡