1በእስራኤልና በሶሪያ መካከል ያለ ጦርነት ሦስት ዓመት አለፈ፡፡
2ይሁን እንጂ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ለመጎብኘት ሄደ፡፡
3የእስራኤል ንጉሥ ለአገልጋዮቹ እንዲህ አለ፡- በገለዓድ የምትገኘውን ራሞት ከሶርያ ንጉሥ ለማስመለስ ምንም ዓይነት እርምጃ ያልወሰድነው ስለምንድን ነው? ራሞት እኮ የእኛ ይዞታ ናት አላቸው፡፡
4ስለዚህ እርሱም ኢዮሣፍጥን ለጦርነት ወደ ራሞት ከእኔ ጋር ትሄዳለህን? ሲል ጠየቀው፡፡ ኢዮሣፍጥም እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ አንተ ሕዝብ ነው፤ ፈረሶቼም እንደ አንተ ፈረሶች ናቸው አለው፡፡
5ኢዮሳፍጥም፣ ነገር ግን መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቅ ሲል መለሰለት፡፡
6ከዚያም አክዓብ አራት መቶ የሚሆኑትን ነቢያቱን ጠርቶ ወደ ራሞት ለጦርነት ልውጣ ወይስ ልቅር? ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ሄደህ ተዋጋ፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣል ሲሉ መለሱለት፡፡
7ኢዮሣፍጥ ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቅበት ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ የለምን? ሲል ጠየቀ፡፡
8አክዓብም የይምላ ልጅ የሆነ ሚክያስ የተባለ ሌላ ነቢይ አለ፤ ነገር ግን እኔ እርሱን አልወደውም፤ እርሱ ምን ጊዜም ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም ሲል መለሰለት፡፡ ኢዮሣፍጥም ይህን ማለት አይገባህም፤ አለው፡፡
9ከዚያም አክዓብ ከቤተ መንግሥቱ አገልጋዮች አንዱን ጠርቶ የይምላ ልጅ ሚክያስን ፈልገህ በማግኘት በፍጥነት እንዲመጣ አድርግ ሲል አዘዘው፡፡
10የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሁለቱ ነገሥታት ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው በሰማርያ የቅጥር በር አጠገብ በሚገኘው ሜዳ በየዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡ ነቢያቱም ሁሉ በነገሥታቱ ፊት ቀርበው ትንቢት ይናገሩ ነበር፡፡
11ከእነርሱም አንዱ ሴዴቅያስ ተብሎ የሚ. ጠራው የክንዓና ልጅ ከብረት የተሠሩ ቀንዶች ይዞ አክዓብን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከብረት በተሠሩ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ወግተህ ፍጹም የሆነ ድልን ትቀዳጃለህ አለው፡፡
12ሌሎቹም ነቢያት ይህንኑ ቃል በመደገፍ በራሞት ላይ ዝመት፣ ታሸንፋለህ፤ እግዚአብሔርም ድልን ይሰጥሃል አሉት፡፡
13ሚክያስን ለመጥራት ሄዶ የነበረው መልእክተኛ በዚሁ ጊዜ ሚክያስን ሌሎቹ ነቢያት በሙሉ ንጉሥ አክዓብ ድል የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ የትንቢት ቃል ተናግረዋል፤ ስለዚህ አንተም እንደእነርሱ ብታደርግ ይሻልሃል አለው፡፡
14ሚክያስ ግን እግዚአብሔር የሚገልጥልኝን ቃል ብቻ እንደምናገር በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! ሲል መለሰለት፡፡
15ሚክያስም ወደ ንጉሥ አክዓብ ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ፣ ሚክያስ ሆይ፣ ንጉሥ ኢዮሣፍጥና እኔ ወደ ራሞት ሄደን ጦርነት እንክፈት ወይስ እንተው? ሲል ጠየቀው፡፡ ሚክያስም ዘምተህ አደጋ ጣልባት ታሸንፋለህ፤ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ ይሰጥሃል፤ ሲል መለሰለት፡፡
16ከዚያም አክዓብ፣ አንተ ግን በእግዚአብሔር ስም የትንቢትን ቃል ስትነግረኝ እውነቱን መግለጥ እንደሚገባህ ስንት ጊዜ እነግርሃለሁ አለው፡፡
17ሚክያስም መላው የእስራኤል ሠራዊት ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በኮረብታዎች ላይ ተበታትነው አያለሁ፤ እግዚአብሔርም፣ እነዚህ ሰዎች መሪ የላቸውም፤ ስለዚህ ወደየቤታቸው በሰላም ይመለሱ ብሎአል ሲል መለሰለት፡፡
18አክዓብም ኢዮሣፍጥን እርሱ ሁልጊዜ ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም ብዬህ አልነበረምን? አለው፡፡
19ሚክያስም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለውን ስማ፤ እግዚአብሔር በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ መላእክቱም ሁሉ በቀኝና በግራው ቆመው አየሁ፡፡
20እግዚአብሔርም አክዓብን ወደ ራሞት ሄዶ በዚያ እንዲገደል ሊያሳስተው የሚችል ማን ነው? አለ፤ ከመላእክቱም መካከል አንዱ ሌላ ነገር ሌላውም ሌላ ነገር አለ፡፡
21በመጨረሻ ግን አንድ መንፈስ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቀርቦ እኔ ላሳስተው እችላለሁ አለ፡፡
22እግዚአብሔርም እንዴት አድርገህ ልታሳስተው ትችላለህ? አለው፡፡ መንፈሱም፣ ሄጄ የአክዓብ ነቢያት ሁሉ ሐሰት እንዲናገሩ አደርጋለሁ ሲል መለሰለት፤ እግዚአብሔርም እንግዲያውስ ሄደህ አሳስተው፤ ይከናወንልሃል አለው፡፡
23ሚክያስም እነሆ እግዚአብሔር እነዚህን የአንተን ነቢያት የሐሰት ቃለ እንዲነግሩህ ያደረገው እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ በአንተ ላይ ጥፋት ሊያመጣብህ እግዚአብሔር ራሱ ወስኖአል! ሲል ንግግሩን ደመደመ፡፡
24ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወደ ሚክያስ ቀርቦ በጥፊ መታውና ከመቼ ወዲህ ነው የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ አልፎ አንተን ያነጋገረህ? አለው፡፡
25ሚክያስም በውስጥ ወዳለው ክፍል ሄደህ በምትሸሽግበት ጊዜ ታውቀዋለህ ሲል መለሰለት፡፡
26በዚህን ጊዜ ንጉሥ አክዓብ ከጦር መኮንኖቹ አንዱን ሚክያስን ያዘው፤ ወደ ከተማይቱ ገዢ ወደ አሞንና ወደ ልዑል ኢዮአስ ውሰደው፤
27እኔም በደህና እስክመለስ ድረስ እስር ቤት አስገብተው ደረቅ እንጀራና ውሃ ብቻ እየሰጡት እንዲቆይ ያድርጉ ሲል አዘዘው፡፡
28ሚክያስም አንተ በደህና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት አልተናገረም ማለት ነው! አለው፤ ቀጥሎም ድምፁን ከፍ በማድረግ በዚህ የምትገኙ ሕዝቦች ሁሉ እኔ የተናገርኩትን ሁሉ ልብ ብላችሁ አድምጡ አለ፡፡
29ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ገለዓድ ምድር ወደምትገኘው ራሞት ከተማ ለመዋጋት ሄዱ፡፡
30አክዓብም ኢዮሣፍጥን ወደ ጦርነት ለመሄድ ስንነሣ እኔ ሌላ ሰው መስዬ ለመታየት ተራ ልብስ እለብሳለሁ፣ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ አለው፡፡ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ሌላ ልብስ ለብሶ ማንነቱን በመሰወር ዘመተ፡፡
31የሶርያ ንጉሥም በንጉሡ ላይ እንጂ በሌላ በማንም ላይ አደጋ አትጣሉ ብሎ ለሠላሳ ሁለቱ የሠረገላ ጦር አዛዦች ትአዛዝ አስተላለፈ፡፡
32ስለዚህ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ በርግጥ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ ነው ብለው በእርሱ ላይ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም በጮኸ ጊዜ፣
33እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በማረጋገጥ በእርሱ ላይ አደጋ ከመጣል ተመለሱ፡፡
34ነገር ግን በአጋጣሚ አንድ የሶርያ ወታደር ፍላጻ በማስፈንጠር ንጉሥ አክዓብን በጦር ልብሱ መገናኛ ላይ ወጋው፤ ንጉሥ አክዓብም የሠረገላ ነጂውን ክፉኛ ቆስያለሁ፤ ስለዚህ ሠረገላውን መልሰህ ከጦር ሜዳው ውጣ! ሲል አዘዘው፡፡
35ጦርነቱም በተፋፋመ ጊዜ ንጉሥ አክዓብ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ በዚያውም ቀን ምሽት ሞተ፡፡
36ፀሐይ በመጥለቅ ላይ እያለች፣ እያንዳንዱ ሰው ወደየአገሩና ወደየከተማው ይመለስ የሚል ትእዛዝ ከእስራኤል ጦር አዛዦች ተነገረ፡፡
37ስለዚህ ንጉሥ አክዓብ ሞተ፤ ሬሳውም ወደ ሰማርያ ተወስዶ ተቀበረ፡፡
38ሠረገላውም በሰማርያ ኩሬ ታጠበ፤ እግዚአብሔርም አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ደሙን ውሾች ላሱት፤ በዚያም ኩሬ ሴተኛ አዳሪዎች ታጠቡበት፡፡
39ንጉሥ አክዓብ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ምን እንደ ሠራና የሠራቸውም ከተሞች ሁኔታ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
40ንጉሥ አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፈንታ ልጁ አካዝያስ ተተክቶ ነገሠ፡፡
41የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
42ኢዮሣፍጥም በሠላሳ አምስት ዓመት ዕድሜው ነግሦ ሃያ አምስት ዓመት በኢየሩሳሌም ገዛ፡፡ እናቱም ዐዙባ ተብላ የምትጠራ የሺልሒ ልጅ ነበረች፡፡
43ኢዮሣፍጥ ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ አባቱ አሳ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ አደረገ፡፡ ሆኖም ግን የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን አልደመሰሰም ነበር፤ ስለዚህም ሕዝቡ በእነዚያ ቦታዎች መሥዋዕት ማቅረብና ዕጣን የማጠን ተግባሩን አልተወም ነበር፡፡
44ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ሰላም መሠረተ፡፡
45ኢዮሣፍጥ ያደረጋቸው ነገሮች፣ በጦርነት ላይ ያሳየው ጀግንነትም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
46ከአባቱ ከአሳ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የተረፉትንና በአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎች የጣዖት አመንዝራዎችን ሁሉ አስወገደ፡፡
47በዚያን ዘመን የኤዶም ምድር የራስዋ ንጉሥ አልነበራትም፤ ከዚህም የተነሣ በይሁዳ ንጉሥ በሚሾመው እንደራሴ ትገዛ ነበር፡፡
48ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ውቅያኖስን አቋርጠው ከኦፊር ወርቅ የሚያመጡለትን የተርሴስ ዓይነት መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ነገር ግን መርከቦቹ በኤጽዮንጋብር ወደብ ላይ ስለ ተሰበሩ መጓዝ አልቻሉም፡፡
49ከዚያ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ መርከበኞቹ ከኢዮሣፍጥ መርከበኛች ጋር በኅብረት እንዲሠሩ የውል ድርድር አቅርቦ ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን አሳቡን አልተቀበለም፡፡
50ንጉሥ ኡዮሣፍጥ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ አዮራም ነገሠ፡፡
51የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ በሰማርያ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፡፡
52እርሱም የአባቱን የአክዓብን፣ የእናቱን የኤልዛቤልንና የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት የመራውን የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል በእግዚአብሔር ፊት በደል ሠራ፡፡
53ከእርሱም በፊት እንደ ነበረው እንደ አባቱ ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ በመስገድና በማገልገል የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሣ፡፡