መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ነገስት 20

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ መላ ሠራዊቱን በአንድነት ሰበሰበ፡፡ ብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች ያሉአቸው ሠላሳ ሁለት ነገሥታት ከእርሱ ጋር ነበሩ፡፡ የእስራኤል ዋና ከተማ የሆነችውን ሰማርያ ጦርነት ገጠመ፡፡
2እርሱም ሀዳድ በከተማይቱ ወደሚገኘው ወደ እስራኤል ነጉሥ ወደ አክዓብ፣ ቤን ሀዳድ እንዲህ ይላል ብሎ መልእክተኞችን ላከ፡-
3ብርህና ወርቅህ ውብ የሆኑት ሚስቶችህና ልጆችህ ምርጥ የሆኑ ሁሉ የእኔ ናቸው፡፡
4የእስራል ንጉሥም ጌታዬ ንጉሥ አንተ እንዳልከው ይሁን ብሎ መለሰ፡፡ እኔ የእኔ የሆነ ሁሉ የአንተ ናቸው አለ፡፡
5ከጥቂት ጊዜም በኋላ እነዚያው መልእክተኞች ከንጉሥ ቤን ሀዳድ ሌላ ትእዘዝ ይዘው እንደገና ወደ አክዓብ መጡ፤ ትዕዛዙ እንዲህ የሚል ነበር፤ ብርህን፣ ሚስቶችህንና ልጆችህን ማስረክብ እንዳለብህ መልእክት ልኬብህ ነበር፡፡
6አሁን ደግሞ ቤትህንና የአገልጋዮችህን ቤት ሁሉ ይበረብራሉ፡፡ በርብረውም በዓይናቸው ደስ ያላቸውን ንብረት ሁሉ ይዘው እንዲመጡ የጦር መኮንኖቼን ነገ በዚህ ጊዜ እልካለሁ፡፡ እነርሱም ነገ ጧት በዚሁ ሰዓት እዚያ ይደርሳሉ፡፡
7የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የአገሪቱን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ ይህ ሰው ምን ዓይነት ጠብ እንደሚፈልግ ተመልከቱ አለ፡፡ ከዚህ በፊት ሚስቶቼንና ልጆቼን፣ ብሬንና ወረቄን እንዳስረክበው ጠይቆኝ ተስማምቼ ነበር አላቸው፡፡
8ሽማግሌዎቹና ሕዝቡም ሁሉ እርሱ ለሚልህ ነገር ሁሉ ግምት አትስጠው፤ ከፍላጎቱ ጋር አትስማማው አሉት፡፡
9ስለዚህም አክዓብ ለቤን ሀዳድ መልእክተኞች ለጌታዬ ለንጉሡ ከዚህ በፊት ባቀረብክልኝ ጥያቄ ተስማምቼ ነበር፤ አሁን ባቀረብክልኝ በሁለተኛው ጥያቄ ግን ልስማማበት አልችልም ብሎአል ብላችሁ ንገሩት አላቸው፡፡ መልእክተኞቹም ተመልሰው በመሄድ መልሱን ነገሩት፤
10ቤን ሀዳድም በሰማርያ ለእያንዳንዱ ወታደር አንዳንድ ጭብጥ ዐፈር ሊዳረስ እስከማይችል ድረስ ብዙ ወታደሮችን ባላሰልፍ አማልክት ይቅሠፉኝ ብሎ የዛቻ መልእክቱን መልሶ ላከበት፡፡
11የእስራኤል ንጉሥ መልእክተኞቹን፣ በወታደር መኩራራት የሚገባው ከጦርነት ድል በኋላ እንጂ ከጦርነት በፊት አይደለም፣ ብላችሁ ለንጉሥ ቤን ሀዳድ ንገሩት ሲል መለሰላቸው፡፡
12ቤን ሀዳድና የእርሱ የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞቹ የሆኑ ሌሎችም ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው ሲጠጡ ሳሉ የአክዓበ መልእክት ደረሳቸው፤ በዚህን ጊዜ ቤን ሀዳድ ለጦርነት እንዲዘጋጁ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ስለዚህም ፈጥነው በመንቀሳቀስ ከተማውን ለማጥቃት ቦታ ቦታቸውን ያዙ፡፡
13በዚያን ጊዜ አንድ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ አክዓብ ቀርቦ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ይህንን ታላቅ ጦር አየህን? እነሆ እግዚአብሔር ዛሬ የቤን ሀዳድን ሠራዊት በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፡፡ አንተም ደግሞ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ ይልሃል አለው፡፡
14አክዓብም ግንባር ቀደም ሆኖ የሚዘምተው ማን ይሁን? ሲል ጠየቀ፡፡ ነቢዩም እግዚአብሔር በአውራጃ አስተዳዳሪዎች የሚታዘዙ ወጣት ወታደሮች ግንባር ቀደም ሆነው ይዝመቱ ይላል አለው፡፡ ንጉሡም ጦርነቱን ማን ይጀምር? ሲል ጠየቀ፡፡ ነቢዩም አንተ ራስህ ጀምር አለው፡፡
15ስለዚህ ንጉሡ ብዛታቸው ሁለት መቶ ሠላሳ ሁለት ብቻ የሆነ በአውራጃ አስተዳዳሪዎች ትእዛዝ ሥር የሆኑትን ወጣት ወታደሮችን ጠራ፡፡ ቀጥሎም ጠቅላላ ብዛቱ ሰባት ሺህ የሆነ የእስራኤልን ሠራዊት ጠራ፡፡
16እነርሱም እኩለ ቀን ላይ ሄዱ፡፡ ቤን ሀዳድና የእርሱ የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞች የሆኑ ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ በመጠጥ ሰክረው ነበሩ፡፡
17ወጣቶቹም ወታደሮች ግንባር ቀደም ሆነው ወደ ፊት አመሩ፡፡ ቤን ሀዳድ ልኮአቸው የነበሩትም ቃፊሮች አንድ የወታደር ቡድን ከሰማርያ ወጥቶ ወደዚህ እየመጣ መሆኑን ነገሩት፡፡
18ቤን ሀዳድም ቃፊሮቹን፣ አመጣጣቸው ለጦርነትም ይሁን ለሰላም ይዛቸሁ አምጡልኝ ሲል አዘዘ፡፡
19ስለዚህ በእስራኤል ሠራዊት ደጀንነት በአውራጃ አስተዳደሪዎች የሚታዘዙ ወጣቶቹ ወታደሮች ግንባር ቀደም ሆነው ወጡ፡፡
20እያንዳንዱም ውጊያ የገጠመውን ጠላቱን ገደለ፡፡ ሶርያውያንም ሸሹ፤ እስራኤላውያንም ያሳድዱአቸው ጀመር፡፡ ቤን ሀዳድ ግን በፈረሱ ላይ ተቀምጦ ከጥቂት ፈረሰኞች ጋር ሸሽቶ አመለጠ፡፡
21ንጉሥ አክዓብም ወደ ጦሩ ሜዳ ገብቶ የጠላትን ፈረሶችና ሠረገሎችን ማረከ፡፡ በሶርያውያን ላይ ታላቅ ጥፋት በማድረስ ድል አደረጋቸው፡፡
22ስለዚህ ነቢዩ ወደ ንጉሥ አክዓብ ቀርቦ፡- የሶርያ ንጉሥ በሚመጣው የጸደይ ወራት እንደገና አደጋ ስለሚጥልብህ ተመልሰህ ሂድና ሠራዊትህን በማጠናከር አደራጅ፤ ጥንቃቄ የሞላበትንም የጦርነት ስልት አዘጋጅ አለው፡፡
23አገልጋዮቹም ንጉሥ ቤን ሀዳድን እንዲህ አሉት፡- የእስራኤል አማልክት የተራራ አማልክት ናቸው፡፡ እስራኤላውያን እኛን ማሸነፍ የቻሉት ስለዚህ ነው፡፡ በሜዳማ ስፍራዎች ጦርነት ብንገጥማቸው ግን እናሸንፋለን፡፡
24ስለዚህ አሁን ሠላሳ ሁለቱን ነገሥታት ከጦር አዛዥነታቸው ሽረህ በእነርሱ ቦታ ሌሎችን የጦር አዛዦች ሹም፡፡
25ከዚህ በፊት የተደመሰሰውን የሚያህል ብዙ ሠራዊትና በቀድሞዎቹ ልክ ፈረሶችንና ሠረገሎችን አደራጅ፤ ከዚያ በኋላ እስራኤላውያንን በሜዳ ተዋግተን ድል እንነሣቸዋለን፡፡ ስለዚህ ቤን ሀዳድም በእነርሱ ምክር ተስማምቶ ለመፈጸም ወሰነ፡፡
26ከዚያም በተከታዩ የጸደይ ወቅት ሠራዊቱን በአንድነት ጠርቶ እስራኤልን ለመዋጋት ወደ አፌቅ ከተማ ገሠገሠ፡፡
27እስራኤላውያን ተጠርተው ከሚያስፈልጋቸው ስንቅና ትጥቅ ጋር ለጦርነት ተዘጋጁ፤ እነርሱም ወደ ጦርነቱ በመዝመት በሁለት ቡድን ተከፍለው ከሶርያውያን ፊት ለፊት ባለው ቦታ ሰፈሩ፡፡ የእስራኤል ወታደሮች ቁጥር አገሩን ካጥለቀለቀው ከሶርያውያን ሠራዊት ብዛት ጋር ሲነጻጻር ከሁለት የተከፈለሉ የጥቂት ፍየሎች መንጋዎች ይመስሉ ነበር፡፡
28አንድ የእግዚአብሔር ነቢይ ወደ ንጉሥ አክዓብ ቀርቦ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ ሶርያውያን፡- እግዚአብሔር የኮረብቶች አምላክ እንጂ የሜዳዎች አምላክ አይደለም ብለዋል፤ ከዚህም የተነሣ እኔ እጅግ ብዙ የሆነውን ሠaርዊታቸውን በእጅህ አሳልፌ እሰጣለሁ፡፡ አንተና ሕዝብህም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ አለው፡፡
29ስለዚህ ሶርያውያንና እስራኤላውያን ፊት ለፊት ተፋጠው በየጦር ሰፈራቸው እስከ ሰባት ቀን ቆዩ፤ በሰባተኛውም ቀን ጦርነት ጀምረው በዚያኑ ቀን እስራኤላውያን አንድ መቶ ሺህ የሶርያውያንን እግረኛ ጦር ወታደሮችን ገደሉ፡፡
30ከሞት የተረፉትም ሶርያውያን ሸሽተው ወደ አፌቅ ከተማ ገቡ፤ በዚያም ቁጥራቸው ሃያ ሰባት ሺህ በሚሆኑት ወታደሮች ላይ የከተማው ቅጥር ተንዶባቸው አለቁ፡፡ ቤን ሀዳድም አምልጦ ወደ ከተማይቱ ገብቶ ከአንድ ቤት በስተ ኋላ በኩል ባለው ክፍል ውስጥ ተደበቀ፡፡
31የቤን ሀዳድ አገልጋዮች ወደ እርሱ ቀርበው፣ የእስራኤል ነገሥታት ምሕረት አድራጊዎች መሆናቸውን ሰምተናል፤ ስለዚህ በወገባችን ማቅ ታጥቀን፣ በራሳችንም ገመድ ጠምጥመን ወደ እስራኤል ንጉሥ ሄደን ምሕረት እንድንጠይቀው ፍቀድልን፤ ምናልባትም ሕይወትህን ያተርፍ ይሆናል አሉት፡፡
32ከዚህም በኋላ እነርሱ በወገባቸው ማቅ ታጥቀው በራሳቸውም ገመድ ጠምጥመው ወደ ንጉሥ አክዓብ በመሄድ አገልጋይህ ቤን ሀዳድ ምሕረት አድርገህ ሕይወቱን እንድታተርፍለት ይማጠንሃል አሉት፡፡ አክዓብም እርሱ እስከ አሁን በሕይወት አለ ማለት ነውን? ከሆነስ መልካም ነው፤ እንግዲህ እርሱ ለእኔ እንደ ወንድም ነው ሲል መለሰላቸው፡፡
33የቤን ሀዳድ አገልጋዮችም የምሕረት መልእክት ይጠባበቄ ስለ ነበር አክዓብ ወንድሜ ሲል በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ቀበል አድገርው አንተ እንዳልከው ቤን ሀዳድ በእርግጥ ወንድምህ ነው አሉት፡፡ አክዓብም ወደ እኔ አምጡት! አላቸው፡፡ ቤን ሀዳድም በመጣ ጊዜ አክዓብ ወደ ሠረገላው ገብቶ እንዲቀመጥ ቤን ሀዳድን ጋበዘው፡፡
34ቤን ሀዳድም አክዓብን አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልስልሃለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ አንተም በደማስቆ ለራስህ የንግድ ማእከል ልታቋቁም ትችላለህ አለው፡፡ አክዓብም እንግዲያውስ በዚህ ስምምነት መሠረት እኔም በነጻ እለቅሃለሁ ሲል መለሰለት፡፡ አክዓብም በዚህ ዓይነት ከእርሱ ጋር የውል ስምምነት አድርጎ በነጻ እንዲሄድ ፈቀደለት፡፡
35የነቢያት ወገን የሆነ አንድ ነቢይ በእግዚአብሔር ታዞ የእርሱ ጓደኛ የሆነውን ሌላ ነቢይ ምታኝ አለው፡፡ ነቢዩ ግን እርሱን ለመምታት እምቢ አለ፡፡
36ስለዚህም ያ ነቢይ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም እምቢ ስላልክ ከእኔ ተለይተህ እንደ ሄድክ ወዲያውኑ አንበሳ ይገድልሃል አለው፤ ከእርሱ ተለይቶ እንደ ሄደ አንበሳ በድንገት ወደ እርሱ መጥቶ ገደለው፡፡
37ከዚህም በኋላ ነቢዩ ወደ ሌላ ሰው ሄዶ ምታኝ አለው፣ ያም ሰው መትቶ አቆሰለው፤
38ነቢዩ ማንነቱ እንዳይታወቅ ፊቱን በጨርቅ ሸፈነ፤ ሄዶም በዚያ በኩል የሚያልፈውን የእስራኤል ንጉሥ ለመጠበቅ በመንገድ ዳር ቆመ፡፡
39ንጉሡም በአጠገቡ ሲያልፍ ነቢዩ ተጣርቶ እንዲህ ሲል ጮኸ፡- ንጉሥ ሆይ እኔ በጦርነት ውስጥ በውጊያ ላይ ነበርኩ፤ በዚያን ጊዜም ከወታደሮቹ አንዱ ከጠላት ወገን አንድን ሰው ማርኮ በማምጣት ይህን ሰው ጠብቅ፣ ቢያመልጥ ግን በእርሱ ፈንታ አንተ ትገደላለህ ወይም ሠላሳ አንድ መክሊት የሚመዝን ብር መቀጫ ትከፍላለህ አለኝ፡፡
40ነገር ግን እኔ ሥራ በዝቶብኝ ወዲያ ወዲህ ስል ሰውየው አምልጦ ሄደ፡፡ ንጉሡም በራስህ ላይ ስለ ፈረድህ መቀጣት ይገባሃል አለው፡፡
41ነቢዩ ፊቱ የተሸፈነበትን ጨርቅ ፈጥኖ አወለቀ፤ ንጉሡም ይህ ሰው ከነቢያት ወገን አንዱ መሆኑን ወዲያውኑ አወቀ፡፡
42ነቢዩም ንጉሡን እንዲህ አለው፡- እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ እኔ ይገደል ብዬ የፈረድኩበት ሰው እንዲያመልጥ ስለ ፈቀድህ በእርሱ ፈንታ አንተ በሞት ትቀጣለህ፤ የዚያ ሰው ሠራዊት አምልጦ እንዲሄድ ስላደረገ ሠራዊትህም ይደመሰሳል፡፡
43ስለዚህ ንጉሡ እያዘነና እየተበሳጨ ወደ ቤቱ ወደ ሰማርያ ተመልሶ ሄደ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።