መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ነገስት 19

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኤልያስ ያደረገውን ሁሉና የባዓልንም ነቢያት በሙሉ እንዴት እንደ ገደላቸው ንጉሥ አክዓብ ለሚስቱ ለኤልዛቤል ነገራት፡፡
2ስለዚህ እርስዋ በእነዚያ ነቢያት ላይ ያደረግኸውን እኔም ነገ ልክ በአሁኑ ሰዓት በአንተ ላይ ሳላደርግብህ ብቀር አማልክት በሞት ይቀሥፉኝ ስትል ወደ ኤልያስ የዛቻ መልእክት ላከች፡፡
3ኤልያስም ስለ ፈራ ሕይወቱን ለማትረፍ ከአገልጋዩ ጋር በይሁዳ ወደምተገኘው ወደ ቤርሳቤህ ከተማ ሄደ፡፡ አገልጋዩንም በዚያ ተወው፤
4ኤልያስ ራሱ አንድ ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዘ፡፡ ከዚህ በኋላ፣ በአንድ የክትክታ ዛፍ ጥላ ሥር ተቀመጠ፣ ሞቱንም በመመኘት እግዚአብሔር ሆይ፣ አሁንስ ይብቃኝ፤ ከቀድሞ አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ! ሲል ጸለየ፡፡
5ከዚህ በኋላ በዛፉ ሥር ጋደም እንዳለ እንቅልፍ ወሰደው፤ በድንገትም አንድ መልአክ መጥቶ በመዳሰሰ ቀሰቀሰውና ተነሥተህ ብላ! አለው፡፡
6ኤልያስ ተነሥቶ ዞሮ በተመለከተ ጊዜ በድንጋይ ሙቀት የበሰለ የዳቦ ሙልሙልና አንድ ገንቦ ውሃ በራስጌው ተቀምጦ አየ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ እንደገና ተኛ፡፡
7የእግዚአብሔርም መልአክ ተመልሶ መጥቶ የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ስለ ሆነ ተነሥተህ ብላ! ሲል ዳግመኛ ኤልያስን ቀሰቀሰው፡፡
8ኤልያስም ተነሥቶ ምግቡን በላ፤ ውሃውንም ጠጣ፡፡ ከዚያም ምግብ ባገኘው ኃይል እስከ ተቀደሰው የሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ተጓዘ፡፡
9እዚያም እንደ ደረሰ ወደ አንድ ዋሻ ገብቶ እዚያ ዐደረ፡፡ በድንገትም እግዚአብሔር፣ ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ? ሲል ጠየቀው፡፡
10ኤልያስም ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትህንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔንም እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ! ሲል መለሰ፡፡
11እግዚአብሔርም ኤልያስን ካለህበት ወጥተህ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም አለው፤ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በአጠገቡ አለፈ፤ ብርቱ ነፋስም በፊቱ በመላክ ኮረብቶችን ሰነጣጠቀ፤ ዐለቶችንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፡፡ ነፋሱም ከቆመ በኋላ ምድሪቱ ተናወጠች፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም፡፡
12ከምድሪቱም ነውጥ በኋላ እሳት መጣ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም በኋላ የሹክሹክታ ድምፅ ተሰማ፡፡
13ኤልያስ የሹክሹክታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጎናጸፊያ ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው መግቢያ በር አጠገብ ቆመ፤ አንድ ድምፅም ኤልያስ ሆይ፣ እዚህ ምን ታደርጋለህ? ሲል ጠየቀው፡፡
14ኤልያስም ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ፣ እኔ ለአምላኬ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትህንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔን እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ ሲል መለሰ፡፡
15እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ በደማስቆ ከተማ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓ ተመልሰህ ሂድ፤ እዚያም በደረስህ ጊዜ አዛሄልን ቀብተህ በሶርያ ላይ አንግሠው፤
16የናሜሲን ልጅ ኢዩንም ቀብተህ በእስራኤል ላይ አንግሠው፤ የአቤል ምሖላ ተወላጅ የሆነውን የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕንም ቀብተህ በአንተ ፈንታ ነቢይ እንዲሆን አድርገው፡፡
17ከአዛሄል እጅ ከመገደል ተርፎ የሚያመልጠውን ማንኛውንም ሰው ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩ እጅ የሚያመልጠውንም ኤልሳዕ ይገድለዋል፡፡
18ይሁን እንጂ ለእኔ ታማኞች የሆኑ ለባዓል ያልሰገዱና ለምስሉም ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን በእስራኤል ምድር በሕይወት እንዲተርፉ አደርጋለሁ፡፡
19ኤልያስም ከዚያ ከሄደ በኋላ የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ሁለት በሬዎች ጠምዶ ሲያርስ አገኘው፤ ከእርሱም ጋር በፊቱ በአሥራ አንድ ጥማድ በሬዎች የሚያርሱ ደቦኞች ነበሩ፤ ኤልሳዕም በመጨረሻ አሥራ ሁለተኛውን ጥማድ ያርስ ነበር፤ ኤልያስም መጎናጸፊያውን አውልቆ በኤልሳዕ ላይ ደረበለት፡፡
20በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ በሬዎቹን ተቶ ወደ ኤልያስ በመሮጥ አባቴና እናቴን ስሜ እንድሰናበት ፍቀድልኝ፤ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ አለው፡፡ ኤልያስም፣ እሺ ተመልሰህ ሂድ፤ እኔ አልከለክልህም! ሲል መለሰለት፡፡
21ከዚህ በኋላ ኤልሳዕ ወደ ጥማድ በሬዎቹ ተመልሶ አረዳቸው፡፡ የተጠመዱበትንም ቀንበር በማንደድ ሥጋቸውን ቀቅሎ ለሰዎቹ አቀረበላቸው፤ እነርሱም በሉ፤ ከዚህ በኋላ ኤልያስን ተከትሎ በመሄድ ረዳቱ ሆነ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።