1ንጉስ ዳዊትም ሸምግሎ እና እድሜውም ገፍቶ ነበር። ምንም እንካ ልብስ ቢድርቡለትም፣ ሊያሞቀው አልቻለም።
2ስለዚህ አገልጋዮቹ፣ "ለንጉስ አንዲት ወጣት ልጃገረድ እንፈልግለት እና ታገልግለው ትንከባከበውም። ንጉሱም እንዲሞቀው ክንዱ ውስጥ ትተኛ፣' አሉት።
3ስለዚህም አንዲት ቆንጆ ልጃገረድ ለማግኘት በመላው እስራኤል ፈለጉ። ሱነማዊቱን አቢሳን አገኙ፤ ወደ ንጉሡም አመጡአት።
4እርስዋም እጅግ ውብ ነበረች፤ እርስዋም ንጉሡን አገለገለችው፣ ተንከባከበችውም፤ ነገር ግን ንጉሡ ከእርስዋ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት አላደረገም።
5በዚያን ጊዜ የአጊት ልጅ አዶንያስ “ንጉሥ እሆናለሁ” በማለት ራሱን ከፍ አደረገ። ስለዚህ በፊቱ የሚሮጡ ሃምሳ ፈረሰኞችንና ሠረገሎችን ለራሱ አዘጋጀ።
6አባቱም ይህን ወይም ያንን ለምን ታደርጋለህ ብሎ ገስጾት አያውቅም ነበር። አዶንያስም ከአቤሴሎም በኋላ የተወለደ፣ እጅግ መልከ መልካም ነበር።
7እርሱም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር አሤረ፤ እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ረዱት።
8ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅ፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ነቢዩ ናታን፣ ሳሚ፣ ሬሲምና ዳዊትን የሚደግፉ ኃያላን አዶንያስን አልተከተሉትም።
9አዶንያስም ዓይንሮጌል አቅራቢያ ባለው በዞሔሌት ድንጋይ ላይ በጎችን፣ በሬዎችንና የሰቡ ወይፈኖችን ሠዋ። እርሱም፣ የንጉሡን ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፣ የይሁዳን ሰዎች ሁሉና የንጉሡን አገልጋዮች ጋበዛቸው።
10ነገር ግን ነቢዩ ናታንን፣ በናያስን፣ ኃያላን ሰዎችን፣ ወይም ወንድሙን ሰሎሞንን አልጋበዛቸውም።
11ከዚያም ናታን፣ ለሰሎሞን እናት ለቤርሳቤህ እንዲህ ሲል ነገራት፦ “ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ መንገሡን አልሰማሽምን?
12ስለዚህ የራስሽንና የልጅሽን የሰሎሞንን ሕይወት ለማትረፍ እንድትችዪ ልምከርሽ።
13ወደ ንጉሥ ዳዊት ሂጂ፤ እንዲህም በዪው፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣’ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፣ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ ለአገልጋይህ ምለህልኝ አልነበረምን? ታዲያ አዶንያስ የሚነግሠው ለምንድን ነው?”።
14በዚያም ከንጉሡ ጋር በመነጋገር ላይ እያለሽ እኔም ካንቺ በኋላ እገባና የተናገርሽው ሁሉ እውነት መሆኑን አረጋግጣለሁ” አላት፡፡
15ስለዚህ ቤርሳቤህ ወደ ንጉሡ ክፍል ሄደች። ንጉሡ እጅግ ስለ ሸመገለ ሱነማይቱ አቢሳ ታገለግለው ነበር።
16ቤርሳቤህም ራስዋን ዝቅ አድርጋ ለንጉሡ እጅ ነሣች፤ ንጉሡም፣ “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት፡፡
17እርሷም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ ሆይ፣ ለአገልጋይህ፣ ‘በእርግጥ ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፣ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ በአምላክህ በጌታ እግዚአብሔር ስም ምለህ ነበር፡፡
18ይኸው አሁን አዶንያስ ነግሦአል፤ አንተም ጌታዬ ንጉሡ ይህንን አታውቅም።
19ስለዚህ በሬዎችን፣ የሰቡ ኮርማዎችንና ብዙ በጎች ሠውቷል። ደግሞም የንገሡን ልጆች፣ ካህኑን አብያታርንና የሠራዊቱን አዛዥ ኢዮአብን ጋብዟቸዋል፤ አገልጋይህን ሰሎሞንን ግን አልጋበዘውም፡፡
20ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ከአንተ ከጌታዬ በኋላ በዙፋንህ የሚቀመጠው ማን መሆኑን አንድታስታውቀው በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡
21አለበለዚያ ግን ጌታዬ ንጉሡ ከአባቶቹ ጋር በሚያንቀላፋበት ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ወንጀለኛ እንቆጠራለን።
22እርስዋ ለንጉሡ በመናገር ላይ እያለች ነቢዩ ናታን ገባ።
23አገልጋዮቹም ለንጉሡ፣ “ነቢዩ ናታን እዚህ ነው” ብለው ነገሩት። እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በቀረበ ጊዜ በግምባሩ ምድር ላይ በመደፋት ለንጉሡ ሰላምታ አቀረበ።
24ናታንም፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ‘አዶንያስ ከእኔ በኋላ ይነግሣል፣ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለሃልን?
25እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችን፣ የሰቡ ጥጆችንና በጎችን ሠውቷል፤ ደግሞም የንጉሡን ልጆች ሁሉ፣ የሠራዊቱን አዛዥ ኢዮአብንና ካህኑን አብያታርን ጋብዟል። ንጉሥ አዶንያስ ለዘላለም ይኑር! በማለት በፊቱ በመብላትና በመጠጣት ላይ ናቸው፡፡
26ነገር ግን እኔን አገልጋይህን፣ ካህኑን ሳዶቅን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስንና አገልጋይህን ሰሎሞንን ወደ ግብዣው አልጠራንም።
27ከአንተ በኋላ በዙፋንህ ላይ የሚቀመጠው ማን እንደሆነ ለእኛ ለአገልጋዮችህ ሳትነግረን ይህንን ያደረግኸው ጌታዬ ንጉሡ ነህን?”
28ከዚያም ንጉሡ ዳዊት፣ “ቤርሳቤህን ጥሩልኝ” አለ። እርስዋም ንጉሡ ወዳለበት መጥታ በፊቱ ቆመች።
29ንጉሡም ማለና፣ “ከደረሰብኝ መከራ ሁሉ የታደገኝ ጌታ እግዚአብሔር ሕያው የመሆኑን ያህል፤
30‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፣ በዙፋኔም ላይ በእኔ ቦታ ይቀመጣል’ ብዬ በእስራኤል አምላክ በጌታ እግዚአብሔር ስም የማልኩትን መሓላ ዛሬ እፈጽመዋለሁ” አላት።
31ቤርሳቤህም ወደ መሬት በግንባሯ በመደፋት ለንጉሡ አክብሮቷን ካሳየች በኋላ፣ “ጌታዬ ንጉሡ ዳዊት ለዘለዓለም ይኑር!” አለች።
32ንጉሥ ዳዊትም፣ “ካህኑን ሳዶቅን፣ ነቢዩን ናታንን እና የዮዳሄን ልጅ በናያስን ጥሩልኝ” አለ። እነርሱም በንጉሡ ፊት ቀረቡ።
33ንጉሡም እንዲህ አላቸው፡- የጌታችሁን አገልጋዮች ከእናንተ ጋር ውሰዱ፤ ልጄን ሰሎምንንም እኔ በምቀመጥባት በቅሎ አስቀምጡትና ወደ ግዮን አውርዱት።
34ካህኑ ሳዶቅና ነቡዩ ናታን ቀብተው በእስራኤል ላይ ያንግሡትና መለከት በመንፋት “ንጉሥ ሰለሞን ለዘላለም ይኑር!” በሉ።
35ከዚያም ተከትላችሁት ትመጣላችሁ፣ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል፤ በእኔ ምትክ ይነግሣልና። በእስራኤልና በይሁዳ ላይ እንዲገዛ ሾሜዋለሁ”።
36የዮዳሄ ልጅ በናያስም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፡- “ይሁን! ይህንንም የጌታዬ የንጉሡ አምላክ ጌታ እግዚአብሔር ያጽናው።
37ጌታ እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር እንደ ሆነ እንዲሁ ከሰሎሞን ጋር ይሁን፤ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሥ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርገው” አለው፡፡
38ስለዚህ ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ከሊታውያንና ፈሊታውያን ወረዱ፤ ሰሎሞንን በንጉሥ ዳዊት በቅሎ ላይ በማስቀመጥ ወደ ግዮን አመጡት።
39ካህኑ ሳዶቅ ዘይት ያለበትን ቀንድ ከድንኳን ወስዶ ሰሎሞንን ቀባው። በዚያን ጊዜ መለከት ነፉ፣ ሕዝቡም፣ “ንጉሥ ሰሎሞን ለዘላለም ይኑር!” አሉ።
40ሕዝቡም ሁሉ ተከትሎት ወጣ፣ ሕዝቡም እምቢልታ እየነፉ በታላቅ ደስታ ደስ አላቸው፣ ከድምፃቸው የተነሣ ምድር ተንቀጠቀጠች።
41አዶንያስና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንግዶች ሁሉ ምግባቸውን እንደጨረሱ ይህንን ድምፅ ሰሙ። ኢዮአብ የእምቢልታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ፣ “ይህ በከተማ ውስጥ የሚሰማው ሁካታ ምንድን ነው?” አለ።
42እርሱ ገና በመናገር ላይ እያለ የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ። አዶንያስም፣ “ና ግባ፤ አንተ ጥሩ ሰው ስለሆንክ መልካም ዜና ይዘህ ሳትመጣ አትቀርም” አለው።
43ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ሲል መለሰለት፡- “ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን እንግሦታል፤
44ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካህኑን ሳዶቅን፣ ነቢዩን ናታንን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን፣ ከሊታውያንን እና ፈሊታውያንን ልኳል። እነርሱም ሰለሞንን በንጉሡ በቅሎ ላይ አስቀመጡት።
45ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታንም በግዮን ቀብተው አነገሡት፤ ደስ እያላቸውም ከዚያ ወጡ፣ በከተማው ሁካታ የሆነው ለዚህ ነው። የሰማችሁት ድምፅም ይኸው ነው።
46ደግሞም ሰሎሞን በመንግሦቱ ዙፋን ላይ ተቀምጧል።
47ከዚህም በላይ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ባለሟሎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ዳዊት ቀርበው አምላክህ እግዚአብሔር ሰሎሞንን ከአንተ ይበልጥ ዝናውን ያግንነው፣ መንግሥቱንም ይበልጥ ታላቅ ያድርገው ሲሉ አክብሮታቸውን ገልጠዋል፤ ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት በአልጋው ላይ ሳለ ለእግዚአብሔር ሰገደ፡፡
48ዛሬ ከእኔ ዘሮች መካከል አንዱ በእኔ እግር ተተክቶ እንዲነግሥ ያደረገና ይህን ለማየት ያበቃኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ሲል እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡
49አዶንያስ የጠራቸው ተጋባዦች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ሁሉም ተነሡ፤ እያንዳኑዱም በየፊናው ተበተነ፤
50አዶንያስም ሰሎሞንን ስለፈራ ወደ ተቀደሰው ድንኳን ሄዶ የመሠዊያውን ቀንዶች በመያዝ ተማጠነ፡፡
51ሰዎቹም ሰሎሞንን፣ አዶንያስ አንተን ከመፍራቱ የተነሣ የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ከሁሉ በፊት ንጉሥ ሰሎሞን የማይገድለኝ መሆኑን በማረጋገጥ በመሐላ ቃል ይግባልኝ በማለት እየተማጠነ ነው ሲሉ ነገሩት፡፡
52ንጉሥ ሰሎሞንም መልካም ሰው ከሆነ ከራስ ጠጉሩ አንዲት እንኳን አትነካበትም፤ ክፉ ሆኖ ከተገኘ ግን ይሞታል ሲል መለሰ።
53ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን አዶንያስን ከመሠዊያው አውርደው ያመጡት ዘንድ መልእክተኞችን ላከ፤ አዶንያስ ወደ ንጉሡ ፊት በመቅረብ ወደ መሬት ራሱን ዝቅ አድርጎ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም ወደ ቤትህ ሂድ አለው።