1ከብዙ ጊዜ በኋላ በሦስተኛው ዓመት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፡- ሄደህ ራስህን ለንገሥ አከዓብ ግለጥለት እኔም በምድር ላይ ዝናብን አዘንባለሁ አለው፡፡
2ኤልያስም በታዘዘው መሠረት ወደ አከዓብ ሄደ፤ በዚህ ጊዜ በሰማርያ ረሃብ እጅግ ጸንቶ ነበር፡፡
3ስለዚህ ንጉሥ አክዓብ የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነውን አብድዩን ጠራው፤ አብድዩ እግዚአብሔርን የሚፈራ መንፈሳዊ ሰው ነበር፡፡
4ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ታስገድል በነበረበት ጊዜ አብድዩ አንድ መቶ የሚሆኑትን የእግዚአብሔርን ነቢያት ከሁለት ከፍሎ ኀምሳ ኀምሳውን በዋሻዎች ከሸሸጋቸው በኋላ እህልና ውሃ በማቅረብ መግቦአቸው ነበር፡፡
5አከዓብ አብድዩን ፈረሶችንና በቅሎዎችን ከሞት የምናድንበት በቂ ሣር እናገኝ እንደሆን በምድሪቱ ወደሚገኘው ምንጭና ወንዝ እስቲ ሂድና እይ፡፡ ምናልባት እንስሳትን ከሞት ማዳን እንችል ይሆናል አለው፡፡
6እያንዳንዳቸው በአገሪቱ ወደየትኛው ክፍል ሄደው መፈለግ እንዳባቸው ከተስማሙ በኋላ አክዓብና አብድዩ ለየብቻቸው በሁለት አቅጣጫ ተሰማሩ፡፡
7አብድዩ በሚሄድበት መንገድ ላይ ሳለ በድንገት ኤልያስን አገኘው፤ ኤልያስ መሆኑንም ስላወቀ በግንባሩ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ከነሣው በኋላ ጌታዬ ኤልያስ በእውነት አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው፡፡
8ኤልያስም አዎን እኔ ነኝ፤ እዚህ መሆኔን ሄደህ ለጌታህ ንገረው ሲል መለሰለት፡፡
9አብድዩም እንዲህ አለው፤ ንጉሥ አክዓብ እኔን ባሪያህን ይገድለኝ ዘንድ በእጁ አሳልፈህ የምትሰጠኝ ምን በደል ሠርቼ ነው?
10ንጉሡ አንተን ለማግኘት ፈልጎ በዓለም ላይ መልእክተኛ ያልላከበት አገር እንደሌለ በአምላክህ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ የአንድ አገር መሪ አንተ በአገሩ ውስጥ አለመኖርህን ለንጉሥ አክዓብ በመሐላ እያረጋገጠለት ቆይቶአል፡፡
11አሁን አንተ ግን ኤልያስ ተገኝቶአል ብለህ ለጌታህ ንገር ትለኛለህ፡፡
12እኔ ከዚህ እንደ ሄድኩ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ አንተን ወዳልታወቀ ቦታ ቢወስድህ እኔ ምን ይበጀኛል? አንተ በዚህ ቦታ መኖርህን ለአከዓብ ነግሬው ሳያገኝህ ቢቀር እኔን በሞት ይቀጣኛል፤ ከልጅነቴ ጀምሬ እግዚአብሔርን የምፈራ ሰው መሆኔን አስታውስ፡፡
13ደግሞስ ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ስታስገድል በነበረችበት ጊዜ አንድ መቶ የሚሆኑትን ነቢያት ከሁለት በመክፈል ኀምሳ ኀምሳውን በዋሻ ውስጥ ሸሽጌ እህልና ውሃ በማቅረብ ስመግባቸው መኖሬን አልሰማህምን?
14ታዲያ፣ አሁን አንተ እዚህ መሆንህን ሄደህ ለንጉሥ አክአብ ንገር ትለኛለህን? ይህን ባደርግ ንጉሡ ይገድለኛል!»
15ኤልያስም «ዛሬ ለንጉሡ እንደምገለጥለት በማገለግለውና ሁሉን ቻይ በሆነው በእግዞአብሔር ስም ቃል እገባልሃለሁ!» ሲል መለሰለት፡፡
16ከዚህ በኋላ አብድዩ ሄዶ ለንጉሥ አክዓብ ነገረው፤ አክዓብም ተነሥቶ ኤልያስን ለመገናኘት ሄደ፤
17አክዓብ ኤልያስን ባየው ጊዜም «በእስራኤል ላይ ይህን ችግር ያመጣህ አንተ እዚህ ነህን?» አለው፡፡
18ኤልያስም እንዲህ ሲል መለሰ፡- «የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመጣስ ባዓል ተብሎ ለሚጠራው የባዕድ አምላክ ምስሎች በመስገድ ችግር የምታመጡ አንተና የአባትህ ቤተ ሰብ ናችሁ እንጂ እኔ በእስራኤል ላይ ችግር የማመጣ አይደለሁም!
19ይልቅስ እስራኤላውያንን ሁሉ እንዳገኛቸው አራት መቶ ሃምሳ የበዓል ነቢያትንና በንግሥት ኤልዛቤል ማእድ የሚቀለቡትን አራት መቶ የኤሼራ ነቢያትን በቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብልኝ፡፡»
20ስለዚህም አክዓብ ለእስራኤላውያን ሁሉና ለነቢያት በሙሉ ጥሪ አድርጎ በቀርሜሎስ ተራራ እንዲሰበሰቡ አስደረገ፡፡
21ኤልያስም ወጥቶ ለሰዎቹ፡- «እስከ መቼ ድረስ በሁለት ልብ ስታወላውሉ ትኖራላችሁ? እንግዲህ እግዚአብሔር እውነተኛ አምላክ ከሆነ እርሱን አምልኩ! ወይም ባዓል እውነተኛ አምላክ ከሆነ እርሱኑ አምልኩ!» አላቸው፡፡ ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል እንኳ አልመለሱም፡፡
22ከዚህ በኋላ ኤልያስ እንዲህ አለ፡- «ከእግዚአብሔር ነቢያት የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፡፡ አራት መቶ ኀምሳ የባዓል ነቢያት ግን እነሆ በዚህ አሉ፡፡
23እንግዲህ ሁለት ኮርማዎችን አምጡና የባዓል ነቢያት አንዱን ወስደው ይረዱት፤ ሥጋውንም ቆራርጠው እንጨት በመረብረብ በዚያ ላይ ያኑሩት፤ ነገር ግን እሳት አያድርጉበት፡፡ እኔም ሁለተኛውን ኮርማ ወስጄ እንደዚሁ አደርጋለሁ፡፡
24ከዚህ በኋላ የባዓል ነቢያት ወደ አምላካቸው ይጸልዩ፤ እኔም ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ እሳትን ወደ መሥዋዕቱ በመላክ መልስ የሚሰጥ እርሱ እውነተኛ አምላክ ይሁን፡፡ ሕዝቡም ድምፁን ከፍ አድረጎ ይህ መልካም ነው በማለት መልስ ሰጡ፡፡
25ከዚህ በኋላ ኤልያስ የባዓልን ነቢያት እናንተ ብዙ ስለ ሆናችሁ በመጀመሪያ አንዱን ኮርማ መርጣቸሁ በማረድ ወደ አምላካችሁ ጸልዩ፤ ነገር ግን እንጨቱ ላይ እሳት አታደርጉበት አላቸው፡፡
26እነርሱም የመጣላቸውን ኮርማ ወስደው በመሥዋዕት አዘጋጅተው እስከ እኩለ ቀን ድረስ ወደ ባዓል ጸለዩ፡፡ ባዓል ሆይ እባክህ ስማን! እያሉ ጮኹ፡፡ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እየዘፈኑ ዞሩ፤ ነገር ግን ምንም መልስ አላገኙም፡፡
27እኩለ ቀን ሲሆን ኤልያስ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጸልዩ! እርሱ አምላክ አይደለም እንዴ? እርሱ በአሳብ ተውጦ ይሆናል! ወይም ራሱን ያዝናና ይሆናል! ወይም ወደ ሩቅ አገር ሄዶ ይሆናል! ወይም ተኝቶ ያንቀላፋ ይሆናልና እንዲነቃ ቀስቅሱት! እያለ ያፌዝባቸው ጀመር፡፡
28ስለዚህም ነቢያቱ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየጸለዩ በሥርዓታቸው መሠረት ደማቸው እስኪፈስ ድረስ በቢላዋና በጩቤ ሰውነታቸውን ያቆስሉ ነበር፡፡
29እኩለ ቀን ካለፈም በኋላ የሠርክ መሥዋዕት እስከሚቀርብበት ጊዜ ድረስ እየተራወጡ ይቀባጥሩ ነበር፤ ይሁን እንጂ ምንም መልስ አላገኙም፤ ድምፅም አልተሰማም፡፡
30ከዚህ በኋላ ኤልያስ ሰዎቹን ወደ እኔ ቅረቡ አላቸው፤ ሁሉም በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ እርሱም ፈርሶ የነበረውን የእግዚአብሔር መሠዊያ በማደስ ሠራው፡፡
31እግዚአብሔር ከዚያ በፊት እስራኤል ብሎ ከሰየመው ከያዕቆብ ልጆች በዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ስም ዐሥራ ሁለት ድንጋዮችን ወሰደ፡፡
32እነዚህንም ድንጋዮች ረብርቦ በእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፡፡ በዙሪያውም ዐሥራ አራት ሊትር ውሃ የሚይዝ ጉድጓድ ማሰ፡፡
33እንጨቱንም በመሠዊያው ላይ በመረብረብ ኮርማውን በብልት በብልቱ ቆራርጦ በእንጨቱ ላይ አኖረ፡፡
34በአራት ጋን ውሃ ሞልታችሁ በመሥዋዕቱና በእንጨቱ ላይ አፍስሱት! አላቸው፡፡ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ አሁንም ጨምሩበት አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፡፡
35ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ጉድጓዱንም ሞላው፡፡
36ከቀትር በኋላ የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ሰዓት ነቢዩ ኤልያስ ወደ መሠዊያው ቀርቦ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንህን፣ እኔም እግዚአብሔር ሆይ፣ የአንተ አገልጋይ መሆኔን፣ እኔም ይህንን ሁሉ ያደረግኹት በቃልህ መሠረት መሆኑን አንተ ራስህ ግለጥ፡፡
37አምላኬ ሆይ፣ ይህ ሕዝብ አንተ እውነተኛ አምላክ መሆንህንና ወደ አንተም ያቀረብከው አንተ ራስህ መሆንህን እንዲያውቅ እባክህ መልስ ስጠኝ፤ አምላክ ሆይ ስማኝ!
38ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እሳትን ላከ፤ ያ እሳት መሥዋዕቱን፣ እንጨቱንና ድንጋዩን በላ፤ ምድሩንም ለበለበ፤ በጉድጓዱ የነበረውንም ውሃ አደረቀ፡፡
39ሰዎቹም ይህን ባዩ ጊዜ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፍተው በመደነቅ እግዚአብሔር አምላክ ነው! እውነተኛ አምላክ እርሱ ብቻ ነው! አሉ፡፡
40ኤልያስም የባዓል ነቢያትን ያዙ፤ አንድም ሰው እንዳያመልጥ ሲል አዘዘ፡፡ ሕዝቡም በሙሉ ያዛቸው፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ እየመራ ወስዶ በዚያ ሁሉንም ገደላቸው፡፡
41ከዚህ በኋላ ኤልያስ ንጉሥ አክዓብን እንግዲህ ሄደህ እህልና ውሃ ቅመስ፤ እኔ አሁን የከባድ ዝናም ነጎድጓድ ድምፅ መቃረቡን እየሰማሁ ነው አለው፡፡
42አክዓብ እህልና ውሃ ለመቅመስ ሲሄድም ኤልያስ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣ፤ እዚያም በሁለቱ ጉልበቶቹ መካከል ራሱን ወደ መሬት ደፋ፡፡
43አገልጋዩን፣ ሂድና ወደ ባሕሩ አቅጣጫ ተመልከት አለው፡፡ አገልጋዩም ሄዶ ሲመለስ ምንም ነገር አይታየኝም አለው፤ አገልጋዩ እየተመላለሰ ያይ ዘንድ ኤልያስ ሰባት ጊዜ አዘዘው፤
44በሰባተኛውም ጊዜ አገልጋዩ ተመልሶ ከአንድ ሰው መዳፍ የማትበልጥ ትንሽ ደመና ከባሕር ስትወጣ አየሁ አለው፡፡ ኤልያስም ወደ ንጉሥ አክዓብ ሂድና ዝናቡ ሳያቆምህ በፍጥነት ወደ ሠረገላህ ገብተህ ወደ ቤትህ ተመልሰህ ሂድ ብለህ ንገረው ሲል አዘዘው፡፡
45ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሰማዩ በጥቁር ደመና ተሸፈነ፤ ነፋሱም ነፈሰ፤ ብርቱ ዝናብም ይዘንብ ጀመረ፡፡ ነጉሥ አክዓብም በሠረገላው ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ፤
46የእግዚአብሔርም ኃይል በኤልያስ ላይ ወረደ፤ ኤልያስም ልብሱን በወገቡ ዙሪያ ጠበቅ አድረጎ በመታጠቅ እስከ ኢይዝራኤል መግቢያ በር ድረስ በአክዓብ ፊት ቀድሞ ይሮጥ ነበር፡፡