1በገለዓድ የምትገኘው ቴስቢያዊው ነቢዩ ኤልያስ ነጉሥ አክዓብን በእኔ ቃል ካልሆነ በቀር በሚቀጥሉት ዓመቶች በምድር ላይ ጠል ወይም ዝናብ እንደማይኖር እኔ በማገለግለው በእስራኤል አምላክ በሕያው እግዚአብሔር ስም እነግርሃለሁ አለው፡፡
2የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፤
3ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፤ እዚያም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ኮራት ተብሎ በሚጠራው ሸለቆ ተሸሽግ፡፡
4የምትጠጣውንም ውሃ ከዚያው ወንዝ ታገኛለህ፤ ቁራዎችም ምግብ እንዲያመጡልህ አዝዣለሁ፡፡
5ኤልያስም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሄዶ በኮራት ሸለቆ ተቀመጠ፡፡
6ከወንዙም ውሃ ጠጣ፤ ቁራዎችም ዘወትር ጧትና ማታ እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፡፡
7ነገር ግን ዝናብ ጠፍቶ ድርቅ ከመሆኑ የተነሣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያ ወንዝ ደረቀ፡፡
8የእግዚአብሔርም ኤልያስን እንዲህ አለው፡-
9እንግዲህ አሁን ከዚህ ተነሥተህ ሂድ፤ በሲዶና በምትገኘው በስራፕታ ከተማ ተቀመጥ፤ እነሆ በዚያ የምትኖር አንዲት መበለት እንድተመግብህ እዝዣለሁ አለው፡፡
10ስለዚህ ኤልያስ ወደ ሰራፕታ ሄደ፤ ወደ ከተማይቱም ቅጥር በር በደረሰ ጊዜ አንዲት ባልዋ የሞተባት ሴት እንጨት ስተለቅም አይቶ እባክሽ የምጠጣው ውሃ አምጪልኝ አላት፡፡
11ውሃም ልታመጣለት በመሄድ ላይ ሳለች ወዲያውኑ ጠርቶ እባክሽ በተጨማሪ ትንሽ እንጀራ አምጪልኝ አላት፡፡
12እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰችለት፡- ምንም እንጀራ እንደሌለኝ በአምላክህ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ በዱቄት ዕቃዬ ውስጥ ካለችው ከአንድ እፍኝ ዱቄትና በማሰሮዬ ውስጥ ካለችው ከጥቂት የወይራ ዘይት በቀር ምንም የለኝም፤ ወደዚህ የመጣሁት ትንሽ እንጨት ለቃቅሜ ቤቴ በመመለስ ይህችኑ ትንሽ ዱቄት ለእኔና ለልጄ ለመጋገር ነው፤ ይህችም የመጨረሻ ምግባችን ናት፤ ከዚያ በኋላ ይህችኑ በልተን እንሞታለን፡፡
13ኤልያስም እንዲህ አላት፣ አይዞሽ አትጨነቂ፤ ሄደሽ ምግብሽን አዘጋጂ፤ አስቀድመሽ ግን ከዚች ካለችሽ ዱቄት ለእኔ ትንሽ እንጎቻ ጋግረሽ አምጪልኝ፤ የቀረውንም ለራስሽና ለልጅሽ ጋግሪው፡፡
14የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- እኔ እግዚአብሔር ዝናብን እስከማወርድ ድረስ ዱቄቱ ከማስቀመጫው ዕቃ፣ ዘይቱም ከማሰሮው ከቶ አያልቅም ሲል ተናግሮአል፡፡
15አርስዋም ሄዳ ኤልያስ እንደ ነገራት አደረገች፤ እርስዋ፣ ቤተ ሰብዋና ኤልያስ ለብዙ ቀን የሚሆን በቂ ምግብ አገኙ፡፡
16እግዚአብሔር በኤልያስ አማካይነት በሰጠው ተስፋ መሠረት ዱቄቱ ከማኖሪያው ዕቃ፣ ዘይቱም ከማሰሮው አላለቀም፡፡
17ከጥቂት ጊዜም በኋላ የዚያች ባልዋ የሞተባት ሴት ልጅ ታመመ፤ ሕመሙም እየባሰበት ስለ ሄደ በመጨረሻ ሞተ፡፡
18እርስዋም ኤልያስን የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ ስለምን ይህን አደረግህብኝ? ወደዚህ የመጣኸው ኃጢአቴን አስታውሰህ ልጄ እንዲሞትብኝ ለማድረግ ነውን? ስትል ጠየቀችው፡፡
19ኤልያስም ልጅሽን ወደ እኔ አምጪው አላት፡፡ ልጁንም ከዕቅፍዋ ወስዶ እርሱ ወደሚኖርበት ሰገነት አውጥቶ በአልጋው ላይ አጋደመው፡፡
20ከዚህ በኋላ ኤልያስ ድምፁን ከፍ በማድረግ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ ስለምን በዚህች ባልዋ በሞተባት ሴት ላይ ይህን የመሰለ አሠቃቂ ነገር አደረግህ? እርስዋ እኔን በማስተናገድ ታላቅ ቸርነት አድርጋልኛለች፤ ታዲያ አንተ ስለምን ልጅዋ እንዲሞት አደረግህ ሲል ጸለየ፡፡
21ከዚህ በኋላ ኤልያስ በልጁ ላይ ሦስት ጊዜ ተዘርሮ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፣ እባክህ ይህን ልጅ ከሞት አስነሣው ሲል ጸለየ፡፡
22እግዚአብሔርም የኤልያስን ጸሎት ሰማ፤ የልጁም እስትንፋስ እንደገና ተመልሶለት ዳነ፡፡
23ኤልያስም ልጁን ከሰገነት ወደ ምድር ቤት አውርዶ ለእናቱ ሰጣትና እነሆ ልጅሽ ከሞት ወደ ሕይወት ተመልሶአል! አላት፡፡
24እርስዋም እነሆ አንተ የእግዚአብሔር ሰው መሆንህንና እግዚአብሔርም በአንተ አማካይነት የተናገረው እውነት መሆኑን አሁን ዐወቅሁ! ስትል መለሰችለት፡፡