1በሐናኒ ልጅ በነቢዩ ኢዩ አማካይነት እግዚአብሔር ስለ ባኦስ የተናገረው ቃል እንዲህ ሲል መጣ፡-
2እኔ ግን ከትቢያ አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ እንድትሆን ከፍ ከፍ አደረግሁህ፤ ታዲያ አንተ እንደ ኢዮርብዓም ኃጢአት ሠራህ፤ ሕዝቤንም ወደ ኃጢአት መራህ፤ የኃጢአታቸውም ብዛት የእኔን ቁጣ አነሣሥቶአል፡፡
3ስለዚህ ኢዮርብዓምን እንዳሰወገድኩ አንተንና ቤተ ሰብህንም አስወግዳለሁ፡፡
4በከተማይቱ ውስጥ የሚሞተውን ማንኛውንም የባኦስ ቤተ ሰብ ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳ ላይ የሚሞተውንም የሰማይ አሞራዎች ይበሉታል፡፡
5ባኦስ ያደረገው ሌላው ነገርና የጀግንነት ሥራዎቹም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
6ባኦስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቲርጻም ተቀበረ፡፡ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ኤላ ነገሠ፡፡
7እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባኦስና በቤተ ሰቡ ላይ የትንቢት ቃል የተናገረው፣ ባኦስ በፈጸመው ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ በማድረጉ ነበር፡፡ ባኦስ እግዚአብሔርን ያስቆጣውም ከእርሱ ፊት የነበረው ንጉሥ ባደረገው ዓይነት ስለ ሠራው ክፉ ነገር ብቻ ሳይሆን የኢዮርብዓምንም ቤተ ሰብ ሁሉ በመግደሉ ጭምር ነበር፡፡
8አሳ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ስድስተኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል መንገሥ ጀመረ፡፡ በቲርጻም ሁለት ዓመት ገዛ፡፡
9የሠረገላዎቹ እኩሌታ ኃላፊ የሆነ ዚምሪ ከጦር መኮንኖቹ አንዱ በንጉሡ ላይ ዐደመ፡፡ ኤላም በቲርጻ ከተማ የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ በሆነው አርጻ ተብሎ በሚጠራው ባለሟሉ ቤት ብዙ መጠጥ ጠጥቶ ሰክሮ ነበር፡፡
10በዚህ ጊዜ ዚምሪ ወደዚያ ቤት ገብቶ ኤላን ገደለው፤ እርሱም በኤላ ፈንታ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ተተክቶ ነገሠ፡፡
11ዘምሪም በዙፋን ላይ እንደተቀመጠ ወዲያውኑ የባኦስ ቤተ ሰብ አባላት የሆኑትን በሙሉ ገደለ፤ የባኦስ ዘመድና ወዳጅ የሆነውን ወንድ አንድ እንኳ ሳይቀር ሁሉንም በሞት ቀጣ፡፡
12እግዚአብሔር ነቢዩ በኢዩ አማካይነት በባኦስ ላይ በተናገረው ትንቢት መሠረት ዚምሪ የባኦስን ቤተ ሰብ በሙሉ ፈጀ፡፡
13ይህም የሆነበት ምክንያት ባኦስና ልጁ ኤላ ጣዖት በማምለካቸውና የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት በመምራታቸው፣ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቁጣ በማነሣሣታቸው ነው፡፡
14ኤላ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
15አሳ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዚምሪ በቲርጻ ለሰባት ቀኖች ብቻ በእስራኤል ላይ ነገሠ፡፡ በዚያን ጊዜ የአስራኤል ወታደሮች በፍልስጥኤም የምትገኘውን የገባቶንን ከተማ ከበው ነበር፡፡
16ዘምሪ ዐምፆ ንጉሡን መግደሉን በሰሙ ጊዜ በዚያው እንዳሉ ወዲያውኑ የጦር አዛዥ የነበረውን ዖምሪን አነገሡ፡፡
17ዖምሪና ወታደሮቹ የገባቶንን ከበባ አቆሙ፤ ከዚያም ገሥግሠው ሄደው ቲርጻን ከበቡ፡፡
18ዘምሪ ከተማይቱ እንደተያዘች ባየ ጊዜ በቤተ መንግሥቱ ውስጠኛ ክፍል ወዳለው ምሽግ ውስጥ ገብቶ በቤተ መንግሥቱ ላይ እሳት ለቀቀበት፤ እርሱም በእሳት ነበልባል ተቃጥሎ ሞተ፡፡
19ይህ የሆነው እርሱ በሠራው ኃጢአትና እስራኤልንም ወደ ኃጢአት በመምራቱ ምክንያት ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ ኢዮርብዓም እግዚአብሔርን ስላስቆጣው ነው፡፡
20ዘምሪ የሠራው ሌላው ነገር ሁሉና ያደረገውም ሤራ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ የሚገኝ አይደለምን?
21በዚያን ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ከሁለት ተከፍለው ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ አንደኛው ክፍል ታምኒን ተብሎ የሚጠራውን የጎናትን ልጅ ለማንገሥ ሲፈልግ ሌላው ክፍል ደግም ዖምሪን ለመደገፍ ይፈልግ ነበር፡፡
22ነገር ግን የዖምሪ ተከታዮች ከጎናት ልጅ ታምኒን ይልቅ ጠንካራ ነበሩ፡፡ ስለዚህም ታምኒን ተገደለ፤ ዖምሪም ንጉሥ ሆነ፡፡
23በዚህ ዓይነት አሳ በይህዳ በነገሠ በሠላሳ አንደኛው ዓመት ዖምሪ በእስራኤል ላይ ነግሦ ዐሥራ ሁለት ዓመት ገዛ፡፡ የመጀመሪያዎቹን ስድስት ዓመቶች የገዛውም መቀመጫውን በቲርጻ አድርጎ ነበር፡፡
24ከዚያም በኋላ ሳምር ተብሎ ከሚጠራው ሰው የሰማርያ ኮረብታን በስድስት ሺህ ጥሬ ብር ገዛው፡፡ ዖምሪ በኮረብታው ላይ ከተማ ቆረቆረ፤ ከተማይቱንም ቀድሞ የኮረብታው ባለንብረት በሆነው በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ሰየማት፡፡
25ዖምሪ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ነገሥታት ይበልጥ የከፋ ኅጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
26እርሱ በሠራው ኃጢአትና አስራኤልን ወደ ኃጢአት በመምራት ዋጋ ወደሌላው ጣዖት አምልኮ መምራቱ ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ ኢዮርብዓም የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሣ፡፡
27ዖምሪ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉና ያከናወነውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
28ዖምሪም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ አክዓብ ነገሠ፡፡
29የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዖምሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ነገሠ። የዖምሪ ልጅ አክዓብ በሰማርያ ሃያ ሁለት ዓመት ነገሠ፤
30የዖምሪ ልጅ አክዓብ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ የባሰ ክፉ ነገር በያህዌ ፊት አደረገ።
31አክዓብ ንጉሥ ኢዮርብዓም የሠራውን ኅጢአት እንደ ቀላል ነገር አድርጎ በመቁጠር እርሱም ራሱ ያንኑ ኃጢአት ሠራ፤ ከዚህም ሁሉ አልፎ የሲዶና ንጉሥ የኤትበዓል ልጅ የሆነችውን አረማዊቷን ኤልዛቤልን አገባ፤ ባዓል ተብሎ የሚጠራውንም ጣዖት አመለከ፤ ሰገደለትም፡፡
32በሰማርያ ለባዓል ቤተ መቅደስ አሠርቶ መሠዊያ ሠራለት፡፡
33አሼራ ተብላ የምትጠራውንም የሴት አምላክ ምስል አቆመ፤ ከእርሱ በፊት ከነበሩትም የእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚያነሣሣ ኃጢአት ሠራ፡፡
34በአክዓብ ዘመነ መንግሥት አኪኤል ተብሎ የሚጠራ የቤቴል ተወላጅ ኢያሪኮን መልሶ ሠራ፤ እግዚአብሔር በነዌ ልጅ በኢያሱ አማካይነት አስቀድሞ በተናገረው ቃል መሠረት አኪኤል የኢያሪኮን የመሠረት ድንጋይ በሚያኖርበት ጊዜ በነዌም ልጅ በኢያሱ እንደ ተነገረው እንደ እግዚብሔር ቃል፣ የበኩር ልጁ አቢሮን ሞተበት፤ የቅጥርዋንም በሮች በሚሠራበት ጊዜ ታናሹ ልጁ ሠጉብ ሞተ፡፡