1ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አቢያ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
2እርሱም በኢየሩሳሌም ሦስት ዓመት ነገሠ፡፡ የእናቱ ስም ማዕካ ሲሆን፣ እርስዋም የአቤሴሎም ልጅ ነበረች፡፡
3አቢያም እንደ ቀደሙት አባቶቹና እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር አምላክ ዘንድ ፍፁም ታማኝ ሆኖ አልተገኘም፡፡ አባቱ ሮብዓም ይፈፅመው የነበረውን ኃጢአት ሁሉ መሥራት ቀጠለ፡፡
4የሆነ ሆኖ ከእርሱ በኋላ በኢየሩሳሌም እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምንም እንዲያጠናክር አምላኩ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል ለአቢያ አንድ ወንድ ልጅ ሰጠው፡፡
5እግዚአብሔር ይህንን ያደረገበት ምክንያት ዳዊት በሂታዊው ኦርዮን ላይ ከፈጸመው ኃጢአት በቀር በእግዚአብሔር ፊት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ትክክለኛ ነገር አድርጎአል፤ ከትእዛዙም ፈቀቅ አላለም፡፡
6በሮብዓምና ኢዮርብዓም ዘመን ተጀምሮ የነበረው ጦርነት፣ በአቢያ ዘመነ መንግሥትም ነበር፡፡
7አቢያ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
8አቢያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፡፡ በእርሱም ፈንታ ልጁ አሳ ተተክቶ ነገሠ፡፡
9ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ በነገሠ በሃያኛው ዓመት አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
10እርሱም በኢየሩሳሌም አርባ አንድ ዓመት ገዛ፡፡ አያቱም ማዕካ ተብላ የምትጠራ የአቤሌሎም ልጅ ነበረች፡፡
11አሳም አያቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ደስ የሚያሰኝ ነገር ሠራ፡፡
12ንጉሥ አሳ የቤተ ጣዖት አመንዝራዎችን ሁሉ ከአገሩ አስወገደ፤ ከእርሱም በፊት የነበሩ ነገሥታት የሠሩአቸውን ጣዖታት ሁሉ ነቃቅሎ ጣለ፡፡
13አያቱ ማዕካ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ አስጸያፊ ጣዖት ስለ ሠራች ከእቴጌነት ሽሮ ከቤተ መንግሥት አስወጣት፤ የሠራችውንም ጣዖት ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ በእሳት አቃጠለው፡፡
14አሳ በኮረብቶች ላይ የሚገኙ የአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎችን በሙሉ አላስወገደም፤ ይሁን እንጂ በዘመኑ ሁሉ የአሳ ልብ ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር ፍጹም ነበር፡፡
15አባቱ ለእግዚአብሔር ቤት የተለዩ እንዲሆኑ ያደረጋቸውንና እርሱም ራሱ የለያቸውን ወርቅና ብር አሠርቶ ንዋያተ ቅዱሳትን ሁሉ በቤተ መቅደስ አኖረ፡፡
16የይሁዳ ንጉሥ አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በሥልጣን በነበሩበት ዘመን ሁሉ የእርስ በርስ ጦርነት ነበር፡፡
17የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ማንም ሰው አሳ በሚገዛበት በይሁዳ ምድር እንዳይወጣና እንዳይገባ ለመከላከል ራማን ምሽግ አድርጎ መሥራት ጀመረ፡፡
18ከዚያም ንጉሥ አሳ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ የተረፈውን ወርቅና ብር ሁሉ ወሰደ፡፡ እርሱም በአገልጋዮቹ እጅ በደማስቆ ከተማ ለነበረው የአዚን ልጅ የጣብሪሞን ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ ስጦታ አድርጎ ላከለት፡፡ እርሱም እንዲህ አለ፡-
19የእኔ አባትና የአንተ አባት ያደርጉት በነበረው ዓይነት በመካከላችን ቃል ኪዳን ይኑር፡፡ እነሆ ብርና ወርቅ ስጦታ እንዲሆንህ ልኬልሃለሁ፡፡ የእሰራኤል ንጉሥ ባኦስ እኔን እንዲለቀኝ ቀደም ሲል ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን ቃል ኪዳን አሁን እንድታቋርጥ ይሁን፡፡
20ንጉሥ ቤን ሀዳድም አሳ ባቀረበው አሳብ ተስማምቶ የጦር አዛዦቹንና ሠራዊቱን በመላከ በእስራኤል ከተሞች ላይ አደጋ እንዲጥሉ አደረገ፡፡ እነርሱም ዒዮን፣ ዳን፣ አቤልቤተማሪካና የገሊላ ባሕር ተብለው የሚጠሩ ከተሞች በገሊላ ባሕር አጠገብ የሚገኘው አገርና የንፍታሌም ግዛት ሁሉ ናቸው፡፡
21ንጉሥ ባኦስ የሆነውን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ የራማን ምሽግ መሠራት እንዲቆም አድርጎ ወደ ቲርጻ ሄደ፡፡
22ከዚህም በኋላ ንጉሥ አሳ ባኦስ ራማን ለመመሸግ አከማችቶት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ከዚያ ለማንሣት እንዲረዳው ሕዝቡ አንድም ሳይቀር እንዲመጣ ወደ ይሁዳ ግዛቶች ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ንጉሥ አሳ ከዚያ የተገኘውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ ወስዶ በምጽጳና በብንያም ግዛት ውስጥ የምትገኘውን የጌባዕን ከተማ ምሽግ አድርጎ ሠራበት፡፡
23ንጉሥ አሳ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ የጀግንነት ሥራውና የሠራቸውም ከተሞች በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን? ንጉሥ አሳ በዕድሜ በሸመገለ ጊዜ ከእግሩ ሕመም የተነሣ ሽባ ሆኖ ነበር፡፡
24ንጉሥ አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መቃብር ተቀበረ፡፡ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ኢዮሣፍጥ ነገሠ፡፡
25አሳ በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የአዮርብዓም ልጅ ናዳብ የእስረኤል ንጉሥ ሆነ፡፡ እርሱም ሁለት ዓመት ገዛ፡፡
26ከእርሱም በፊት እንደ ነበረው እንደ አባቱ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት በመሥራት የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት መራ፡፡
27የይሳኮር ነገድ የሆነው የአኪያ ልጅ ባኦስ ናዳብን ድል አድርጎ ገደለው፤ በዚያም ጊዜ ናዳብና ሠራዊቱ በፍልስጥኤም ግዛት የምትገኘውን የገባቶንን ከተማ በመክበብ ላይ ነበሩ፡፡
28ይህም የሆነው የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ነው፤ በዚህ ዓይነት ባኦስ በናዳብ ፈንታ ተተክቶ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፡፡
29ንጉሥ ባኦስ እንደነገሠ ወዲያውኑ የኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ በሙሉ ገደለ፡፡ እግዚአብሔር በአገልጋዩ በሴሎኣዊው በነቢዩ አኪያ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት የኢዮርብዓም ወገን በሙሉ ተገደሉ፡፡ በሕይወት የተረፈ አንድም አልነበረም፤
30ይህም የሆነበት ምክንያት ኢዮርብዓም ራሱ በሠራው ኃጢአትና የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቁጣ ስላነሣሣ ነው፡፡
31ናዳብ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
32የይሁዳ ንጉሥ አሳ እና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በሥልጣን ዘመናቸው ሁሉ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ ነበሩ፡፡
33አሳ በይሁዳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፡፡ እርሱም በቲርጻ ሃያ አራት ዓመት ገዛ፡፡
34ከእርሱም በፊት እንደ ነበረው እንደ ንጉሥ ኢዮርብዓም ባኦስ ኃጢአት በመሥራትና የእስራኤልንም ሕዝብ ወደ ኃጢአት በመምራት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፡፡