1በዚያን ጊዜ የንጉሥ ኢዮርብዓም ወንድ ልጅ አቢያ በጠና ታሞ ነበር፡፡
2ስለዚህ ኢዮርብዓም ሚስቱን እንዲህ አላት፡- የእኔ ሚስት መሆንሽን ማንም እንዳያውቅ ልብስሽን ለውጠሽ ሌላ ሴት በመምሰል እኔ የእስራኤል ንጉሥ እንደምሆን የትንቢት ቃል የተናገረው ነቢይ አኪያ ወደሚኖርባት ወደ ሴሎ ሂጂ፡፡
3ዐሥር እንጀራ፣ ጥቂት ሙልሙል ዳቦና አንድ ገንቦ ማር ውሰጂለት፤ ስለ ልጁ ሁኔታ እርሱ ይነግርሻል፡፡
4ስለዚህ የኢዮርብዓም ሚስት ይህን ሁሉ አዘጋጅታ በሴሎ ወደሚገኘው ወደ አኪያ ቤት ሄደች፡፡ ነቢዩ አኪያም በዕድሜው ከመሸምገሉ የተነሣ ዓይኖቹ ፈዘው ስለነበር ለማየት አልቻለም፡፡
5እግዘዚአብሔር ለአኪያ እንዲህ አለው፡- የኢዮርብዓም ሚስት ስለታመመው ልጅዋ ልትጠይቅህ እየመጣች ነው፡፡ የኢዮርብዓም ሚስት እዚያ በደረሰች ጊዜ ሌላ ሴት ለመምሰል ስለምትሞክር ይህንኑ ተናገራት፡፡
6ነገር ግን ነቢዩ አኪያ ወደ በሩ ስትቀርብ የኮቴን ድምፅ ሰምቶ እንዲህ አላት፤ ግቢ፣ የኢዮርብዓም ሚስት መሆንሽን አውቃለሁ፤ ሌላ ሴት ለመምሰል ስለምን ሞከርሽ? ለአንቺ እነግርሽ ዘንድ የታዘዝኩት አሳዛኝ ዜና አለ፡፡
7ወደ ኢዮርብዓም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለውን ንገሪው፤ ቃሉም ይህ ነው፤ ‹ከሕዝብ መካከል መርጬ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፡፡
8መንግሥትንም ከዳዊት ትውልድ ወስጄ ለአንተ ሰጠሁህ፤ ነገር ግን አንተ ታማኝ ሆኖ ትእዛዜን እንደጠበቀውና እኔ ደስ የምሰኝበትን እንዳደረገ እንደ አገልጋዬ እንደ ዳዊት ሆነህ አልተገኘህም፡፡
9ይልቁንም ከአንተ በፊት መሪዎች ከነበሩ ሰዎች የከፋ ኃጢአት ሠራህ፤ እኔንም ትተህ ጣዖቶችንና ከብረት የተሠሩ ምስሎችን ለማምለክ በመነሣትህ ቁጣዬን አነሣሥተሃል፡፡
10በዚህ ምክንያት እነሆ፣ በኢዮርብዓም ቤት ላይ ክፉ ነገርን አመጣለሁ፤ ከቤቱም ነፃም ሆነ ባርያ ወንድ ልጅን ሁሉ ከእስራኤል አጠፋለሁ፤ ፋንድያን አቃጥለው እንደሚጨርሱት የኢዮርብዓምን ቤት አወድማለሁ፡፡
11በከተማ የሚሞተውን ማንኛውንም የቤተ ሰብህን አባል ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳ ላይ የሚሞቱንም የሰማይ አሞራ ይበላቸዋል፤ ይህን የተናገርኩት እኔ እግዚአብሔር ነኝ፡፡”
12አኪያም የሚናገረውን የትንቢት ቃል በመቀጠል ለኢዮርብዓም ሚስት እንዲህ አላት፣ እንግዲህ አሁን ወደ ቤትሽ ተመልሰሽ ሂጂ፤ ወደ ከተማም እግሮችሽ እንደረገጡ ወዲያውኑ ልጁ ይሞታል፡፡
13እስራኤላውያንም ሁሉ አዝነውና አልቅሰው ይቀብሩታል፡፡ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተደሰተበት ልጅ እርሱ ብቻ ስለሆነ ከኢዮርብዓም ቤተ ሰብ ሥርዓተ ቀብር በሚገባ የሚፈፀምለት እርሱ ብቻ ይሆናል፡፡
14እግዚአብሔርም በዚያን ቀን የኢዮርብዓምን ቤት የሚያጠፋ ንጉሥ ያስነሣል፡፡ ይኸውም አሁን ነው፡፡
15እግዚአብሔር እስራኤልን ይቀጣል፤ እርሱም በውሃ ውስጥ እንደሚወዛወዝ ሸንበቆ ይወዛወዛል፡፡ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ጣዖት በመሥራት እግዚአብሔርን ስላስቆጡት፣ የእስራኤልን ሕዝብ ቀድሞ ለአባቶቻቸው ከሰጣቸው መልካም ምድር ይነቅላል፤ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ እንዲበታተኑም ያደርጋል፡፡
16ኢዮርብዓም ኃጢአት ከመሥራቱ የተነሣና የእስራኤልንም ሕዝብ ወደ ኃጢአት ስለመራ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ይተዋል፡፡»
17ስለዚህ የኢዮርብዓም ሚስት ተነሥታ ወደ ቲርሳ ተመልሳ ሄደች፡፡ ወደ ቤትዋ ደጃፍ አንደ ደረሰች ወዲያውኑ ልጁ ሞተ፡፡
18እግዚአብሔር በአገልጋዩ በነቢዩ አኪያ በኩል በነገረው መሠረት እስራኤላውያን በሐዘን አልቅሰው ቀበሩት፡፡
19ንጉሥ ኢዮርብዓም ያደረጋቸው ሌሎች ነገሮች ሁሉ፣ የተዋጋቸው ጦርነቶችና አገዛዙም እንዴት እንደ ነበር ሁሉም ነገር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
20ኢዮርብዓም ለሃያ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ ከአባቶቹም ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ናዳብ በእርሱ ፈንታ ተተክቶ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፡፡
21የሰለሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመቱ ነበር፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ከመላው የእስራኤል ነገዶች ለስሙ መጠሪያ እንድትሆን በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም መኖሪያውን አድርጎ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፡፡ የሮብዓምም እናት አሞናዊት ስትሆን፣ ስምዋም ናዕማ ነበር፡፡
22የይሁዳ ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው ሲያደርጉት ከነበረው ይበልጥ ክፉ ነገር በማድረጋቸው የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሡት፡፡
23ለባዕዳን አማልክትም የማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ፤ በኮረብታዎች ላይና በዛፍ ጥላ ሥር የሚያመልኩአቸውን የድንጋይ ቅርፆችና የኤሼራን ምስሎች አቆሙ፡፡
24ከእነዚህም ሁሉ የከፋ በእነዚያ ሕዝቦች የማምለኪያ ስፍራዎች የቤተ ጣዖት አመንዝራዎች ነበሩ፡፡ አሕዛብ ይፈፅሙት የነበረውን እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት ነቃቅሎ ያባረራቸውን አሳፋሪ ነገር ሁሉ ይፈፅሙ ነበር፡፡
25ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ጣለ፡፡
26በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ተከማችቶ የነበረውንም ሀብት ሁሉ፣ ሰለሞን ከወርቅ ያሠራቸውን ጋሻዎች ጭምር ዘርፎ ወሰደ፡፡
27እነርሱንም ለመተካት ንጉሥ ሮብዓም ጋሻዎችን ከነሐስ አሠርቶ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር በር በሚጠብቁ አለቆች እንዲጠበቁ አደረገ፡፡
28ንጉሡ ወደ ቤተ መቅደሱ በመጣ ቁጥር፣ የቤተ መቅደሱ ዘበኞች ጋሻዎችን አንግበው ይቀበሉታል፤ ከሄደም በኋላ ጋሻዎቹን መልሰው ዘበኞች በሚጠበቁበት ማከማቻ ያኖሩ ነበር፡፡
29ንጉሥ ሮብዓም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
30በዚህም ዘመን ሁሉ ሮብዓምና ኢዮርብዓም እርስ በርሳቸው በማያቋርጥ ጦርነት ላይ ነበሩ፡፡
31ሮብዓም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታቱ መካነ መቃብር ተቀበረ፡፡ ልጁም አቢያ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ነገሠ፡፡