መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ነገስት 13

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የእግዚአብሔርን ቃል ይዞ አንድ ነብይ ከይሁዳ ወደ ቤቴል ደረሰ፤ ኢዮርብዓም ዕጣን ለማጠን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ነበር፡፡
2ነቢዩም እንዲህ ሲል በጩኸት የትንቢት ቃል ተናገረበት፡- «መሠዊያ! መሠዊያ ሆይ! እግዚአብሔር ስለ አንተ የሚለው ቃል ይህ ነው፡- ‹እነሆ ከዳዊት ቤተ ሰብ ኢዮአስ ተብሎ የሚጠራ ልጅ ይወለዳል፤ እርሱም በኮረብታ ላይ ለተሠራው ለአህዛብ መሠዊያ አገልጋዮች ሆነው መሥዋዕት የሚያቀርቡትን ካህናት በአንተው ላይ ያርዳቸዋል፤ የሰዎችንም አጥንት በአንተ ላይ ያቃጥላል፡፡
3በዚያው ቀን ነቢዩ ምልክት ሰጠ፤ ይህ መሠዊያ ተሰባብሮ ይወድቃል፤ በእርሱም ላይ ያለው አመድ ይበተናል፤ ይህንንም የትንቢት ቃል በእኔ አማካኝነት የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር ለመሆኑ ምልክት ይሆናል›» አለው፡፡
4ንጉሥ ኢዮርብዓምም ይህን በሰማ ጊዜ እጁን አንሥቶ ወደ ነቢዩ በማመልከት ያዙት የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤ የንጉሡም ክንድ ወዲውኑ ድርቅ ብሎ ቀረ፤ የዘረጋውን እጁን መመለስ አልቻለም፡፡
5የእግዚአብሔርም ነቢይ በእግዚአብሔር ስም በተናገረው የትንቢት ቃል መሠረት የተሰጠው ምልክት ተፈጸመ፤ መሠዊያው ወዲያውኑ ተሰባብሮ ወደቀ፤ አመዱም መሬት ላይ ፈሰሰ፡፡
6ንጉሡ ኢዮርብዓምም፣ እባክህ እጄ እንዲመለስልኝ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልኝ ሲል የእግዚአብሔርን ነቢይ ለመነው፡፡ የእግዚአብሔርም ነቢይ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮለት የንጉሡ እጅ ዳነች፡፡ እንደ ቀድሞም ሆነች፡፡
7ከዚህ በኋላ ንጉሡ ነቢዩን ና ከእኔ ጋር አብረህ ወደ ቤቴ ግባ፤ እህልም ቅመስ፤ ስጦታ እሰጥሃለሁ አለው፡፡
8የእግዚአብሔር ነቢይ ግን የሀብትህን እኩሌታ ብትሰጠኝ እንኳ ወደ ቤትህ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ እህል ውሃም እዚህ ቦታ አልቀምስም አለ፡፡
9ምንም ዓይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስና ወደ ቤቴ ስመለስም በመጣሁበት መንገድ እንኳ እንልሄድ እግዚአብሔር አዞኛል ሲል መለሰለት፡፡
10ስለዚህ ወደ ቤቴል የመጣበትን መንገድ በመተው በሌላ መንገድ ተመልሶ ሄደ፡፡
11በዚያን ጊዜ በቤቴል የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፡፡ ወንዶች ልጆቹ ወደ እርሱ ቀርበው፣ ከይሁዳ የመጣው ነቢይ በቤቴል ስላደረገውና በንጉሥ ኢዮርብዓምም ላይ ስለ ተናገረው ቃል ሁሉ አወሩለት፡፡
12አባታቸውም ታዲያ ያ የእግዚአብሔር ነቢይ ከዚያ ተነሥቶ በየትኛው መንገድ ሄደ? ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱም የሄደበትን መንገድ በማመልከት አሳዩት፤
13ከዚህም በኋላ እርሱ አህያዬን ጫኑልኝ አላቸው፤ ልጆቹም አህያውን ጭነውለት፣ ሽማግሌው ነቢይ በአህያው ላይ ተቀምጦ፣
14ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ የሄደበትን መንገድ አቅጣጫ ይዞ ተከተለው፤ በአንድ የወርካ ዛፍ ሥር ተቀምጦም አገኘው፡፡ ሽማግሌውም ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ነቢይ አንተ ነሀን? ሲል ጠየቀው፡፡ እርሱም አዎን እኔ ነኝ ሲል መለሰለት፡፡
15ሽማግሌውም ወደ ቤቴ ገብተህ ከእኔ ጋር እህል ብላ አለው፡፡
16ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ ግን ከአንተ ጋር አብሬ ወደ ቤትህ መሄድም ሆነ በዚህ ቦታ ከአንተ ጋር ምንም ዓይነት እህል ውሃ መቅመስ አልችልም ሲል መለሰለት፡፡
17በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስ፣ በመጣሁበት መንገድ እንኳ ተመልሼ እንዳልሄድ እግዚአብሔር አዞኛል አለው፡፡
18ከዚህ በኋላ ከቤቴል የመጣው ሽማግሌው ነቢይ፣ እኔም እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ወስጄ እንዳስተናግድህ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ነግሮኛል አለው፡፡ ነገር ግን ሽማግሌው ነቢይ የተናገረው በውሸት ነበር፡፡
19ስለዚህ ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ ከሽማግሌው ነቢይ ጋር አብሮት ወደ ቤቱ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር ተመገበ፡፡
20በገበታም ቀርበው ሳሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሽማግሌው ነቢይ መጣ፡፡
21ከይሁዳ ለመጣው የእግዚአብሔር ሰው እንዲህ አለው፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ ባለመታዘዝ የእግዚአብሔርን ቃል አልታዘዝክም፡፡
22ይህን በማድረግ ፈንታ እኔ በዚያ ምንም ዓይነት እህል ውሃ እንዳትቀምስ ወዳዘዝኩህ ወዳዚያ ቦታ ተመልሰህ በላህ፤ ይህንንም በማድረግህ ምክንያት ትገደላለህ፤ ሬሳህም በቤተ ሰብህ መቃብር አይቀበርም፡፡
23ከተመገቡም በኋላ ሽማግሌው ነቢይ ከይሁዳ መልሶ ላመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ አህያውን ጫነለት፤
24እርሱም በአህያው ላይ ተቀምጦ ሄደ፤ በመንገድም አንበሳ አገኘውና ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆመው ነበር፡፡
25ሰዎች በዚያ በኩል ሲያልፉ አጠገቡ ከቆመው አንበሳ ጋር ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ አዩ፣ ሽማግሌው ነቢይ ወደሚኖርበት ወደ ቤቴል ከተማ መጥተውም አወሩለት፡፡
26ሽማግሌው ነቢይ ይህን በሰማ ጊዜ፣ ያ ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ያልጠበቀው ነቢይ ነው፤ ስለዚህም እግዚአብሔር እንደ ተናገረው አንበሳ ቦጫጭቆ እንዲገለው አሳልፎ ሰጥቶታል ማለት ነው አለ፡፡
27ከዚህም በኋላ ልጆቹን አህያዬን ጫኑልኝ አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት፡፡
28በአህያው ላይ ተቀምጦ ሄደ፤ በነቢዩ ሬሳ አጠገብ አህያውና አንበሳው እስካሁን እንደ ቆሙ በመንገድ ላይ ተጋድሞ አገኘው፡፡ አንበሳውም የነቢዩን ሬሳ አልበላም፤ በአህያውም ላይ አደጋ አላደረሰበትም ነበር፡፡
29ሽማግሌው ነቢይ ሬሳውን አንሥቶ በአህያው ላይ ጫነው፤ እንዲለቀስለትና እንዲቀበር ወደ ቤቴል መልሶ ወሰደው፡፡
30ሽማግሌውም ነቢይ በገዛ ራሱ ቤተ ሰብ መቃብር ቀበረው፤ እነርሱም ወንድሜ ሆይ ወንድሜ ሆይ እያሉ አለቀሱለት፡፡
31ከቀብሩም ሥነ ሥርዓት በኋላ ሽማግሌው ነቢይ ለልጆቹ እንዲህ አላቸው፤ እኔ ስሞት በዚህ መቃብር ቅበሩኝ፤ ሬሳዬንም ከእርሱ ሬሳ አጠገብ አጋድሙት፡፡
32በቤቴል በሚገኘው መሠዊያ ላይና በሰማርያ ታናናሽ ከተሞች በየኮረብታው ባሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ላይ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ይህ የእግዚአብሔር ነቢይ የተናገረው የትንቢት ቃል በእርግጥ ይፈጸማል፡፡
33ይህም ሁሉ ሆኖ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም ከሚያደርገው ክፉ ነገር ሁሉ አልተመለሰም፤ ይልቁንም እርሱ በሠራቸው መሠዊያዎች የሚያገለግለውን ማንኛውንም ሰው ካህን አድርጎ ይሾመው ነበር፡፡
34ይህም ኃጢአቱ ለቤተ ሰቡ መጥፋትና ከምድር ገጽ ለመደምሰሱ ምክንያት ሆነ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።