መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ነገስት 12

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሮብዓምም ወደ ሴኬም ሄደ፤ ምክንያቱም እስራኤል ሁሉ እርሱን ለማንገሥ ወደ ሴኬም መጥተው ነበር፡፡
2ከንጉሡ ሰሎሞን በመሸሽ ወደ ግብጽ ኮብልሎ በዚያው በግብጽ ይኖር የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ወሬ በሰማ ጊዜ ተመልሶ መጣ፡፡
3ስለዚህ የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ወደ እርሱ ልከው ጠሩት፤ ወደ ሮብዓም ቀርበው እንዲህ አሉት፡-
4አባትህ ሰሎሞን በእኛ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር አክብዶብን ነበር፡፡ አሁን አባትህ የጫነብንን ከባድ የሥራ ሸክም አቃልልን፣ ለአንተም እንገዛልሃለን አሉት፡፡
5ሮብዓምም ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ኑ አላቸው፤ ስለዚህ ሕዝቡ ሄዱ፡፡
6ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የአባቱን የሰሎሞን ዘመን አማካሪዎች የነበሩትን ሽማግሌዎች በአንድነት ሰብስቦ እንግዲህ ለዚህ ሕዝብ መልስ መስጠት እንድችል ምን ትመክሩኛላችሁ? ሲል ጠየቃቸው፡፡
7ሽማግሌዎቹም ዛሬ ለእነዚህ ሰዎች ታዛዥ ሆነህ ብታገለግላቸው ለጥያቄአቸውም ተስማሚ የሆነ መልስ ብተሰጣቸው እነርሱም ዘወትር በታማኝነት ያገለግሉሃል ሲሉ መለሱለት፡፡
8ነገር ግን ሮብዓም የሽማግሌዎቹን ምክር ቸል በማለት አብሮ አደጎቹ ወደነበሩት አሁን ደግሞ አማካሪዎቹ ወደሆኑት ወጣቶች ሄደ፡፡
9የአገዛዝ ቀንበር እንዳቀልላቸው ለጠየቁኝ ምን መልስ እንደምሰጣቸው ምን ትመክሩኛላችሁ? ሲል ጠየቃቸው፡፡
10እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ አንተ የምተሰጣቸው መልስ ይህ ነው፤ የእኔ ታናሽ ጣት ከአባቴ ወገብ ይበልጥ ትወፍራለች!
11አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፣ እኔ ደግሞ የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፣ አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን በሚናደፍ ጊንጥ እገርፋችኋለሁ!
12ከሦስት ቀን በኋላ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ ንጉሡ በሰጣቸው ቀጠሮ መሠረት ተመልሰው ወደ ሮብዓም መጡ፡፡
13ንጉሥ ሮብዓምም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ትቶ ሕዝቡን በማመናጨቅ መልስ ሰጣቸው፡፡
14ወጣቶቹ በሰጡት ምክር መሠረት አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ! ሲል መለሰላቸው፡፡
15ይህም ከሴሎ በመጣው በነቢዩ አኪያ አማካይነት ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም እግዚአብሔር የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው። ነጉሥ ሮብዓምም የሕዝቡን አሳብ ችላ በማለት ሳይቀበል የቀረበትም ምክንያት እግዚአብሔር ይህን ለውጥ ለማድረግ ስለ ወሰነ ነው፡፡
16ሕዝቡ ንጉሥ ሮብዓም ጥያቄውን እንዳልተቀበለው በተገነዘበ ጊዜ ከዳዊት ጋር ምን ድርሻ አለን? የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ወደየቤትህ ሂድ! ዳዊት ሆይ፣ የራስህን ቤት ጠብቅ ብለው መለሱለት፡፡ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ወደየቤቱ ሄደ፡፡
17ሮብዓምም በይሁዳ ግዛት በሚኖሩት ሕዝብ ላይ ብቻ ነገሠ፡፡
18ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የግዳጅ ሥራ ኃላፊ የነበረውን አዶኒራምን ወደ እስራኤላውያን እንዲሄድ ላከው፤ እነርሱ ግን በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ በዚህ ጊዜ ሮብዓም በፍጥነት ወደ ሠረገላው ገብቶ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ አመለጠ፡፡
19ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ሰሜናዊው ክፍል እስራኤል በሚል በዳዊት ሥርወ መንግሥት ላይ ዐመፀ፡፡
20እስራኤልም ሁሉ ኢዮርብዓም ከግብጽ ተመልሶ መምጣቱን በመገንዘብ ወደ ጉባዔያቸው ጠርተው በእስራኤል ላይ አነገሡት፤ ለዳዊት ትውልዶች ታማኝ ሆኖ የቀረው የይሁዳ ነገድ ብቻ ነበር፡፡
21ሮብዓም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከይሁዳና ከብንያም ነገዶች ተውጣጥተው የተመለሱ አንድ መቶ ሰማኒያ ምርጥ ወታደሮች ጠርቶ በአንድነት ሰበሰበ፤ ይህም የእስራኤልን ነገዶች ለመዋጋትና እንደገና መንግሥትን ወደ ሰሎሞን ልጅ ሮብዓም ለመመለስ ነበር፡፡
22ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሳማያ እንዲህ ሲል መጣ፡፡
23ለሮብዓምና ለመላው የይሁዳና የብንያም ነገዶች ለቀሩትም ሕዝብ ሁሉ እንዲህ በል፡-
24ከወንድሞቻችሁ ከእስራኤላውያን ጋር በመዋጋት አደጋ አትጣሉ፤ ሁላችሁም ወደየቤታችሁ ሂዱ፤ ይህ የሆነው በእኔ ፈቃድ ነው ብሎ አዘዘው፡፡ እነርሱም ለእግዚብሔር ቃል በመታዘዝ ወደየቤታቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡
25ኢዮርብዓምም በኮረብታማው በኤፍሬም አገር የምትገኘውን ሴኬምን ከተማ አድርጎ ሠርቶ ኖረባት፡፡ ከዚያም ተነሥቶ የጵንኤልን ከተማ ሠራ፡፡
26ኢዮርብዓምም አሁን መንግሥቱ ወደ ዳዊት ቤት ይመለሳል ብሎ በልቡ አሰበ፡፡
27ይህ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መስዋዕት የሚያቀርብ ከሆነ፣ የሕዝቡ ልብ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ጌታቸው ወደ ሮብዓም ይመለሳል፡፡ ከዚያ እኔን ይገሉኛል፤ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓምም ይመለሳሉ፡፡
28ስለዚህ ሮብዓም በጉዳዩ ከመከረበት በኋላ የሁለት ጥጆች ምስል ከወርቅ አሠርቶ ለሕዝቡ ከዚህ በፊት እንደምታደርጉት ለመስገድ እስከ ኢየሩሳሌም መሄድ አድካሚ ነው፡፡ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፡- ከግብጽ ምድር ያወጣችሁ አማልክትህ እነሆ እነዚህ ናቸው! አለ፡፡
29ከዚህ በኋላ ከወርቅ የተሠሩት ሁለት የኮርማ ምስሎች አንዱን በቤቴል ሁለተኛውንም በዳን አቆመ፡፡
30ስለዚህ ይህ ድርጊት ኃጢአት ሆነ፡፡ ሰዎቹም እስከ ዳን ድረስ በጣዖቱ ፊት ተሰልፈው ሄዱ፡፡
31ኢዮርብዓምም በኮረብታዎች ላይ የማምለኪያ ስፍራዎችን አዘጋጅቶ የሌዊ ነገድ ካልሆኑ ቤተ ሰቦች መካከል ማንኛውንም ሰው ካህን አድርጎ ሾመ፡፡
32ኢዮርብዓም በይሁዳ በሚደረገው በዓል ዓይነት ስምንተኛ ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን የባዕድ አምልኮ በዓል እንዲደረግ ወሰነ፤ ከወርቅ ላሠራውም ምስሎች በቤቴል በሚገኘው መሠዊያ ላይ ለጥጃ ምሰሉ መሥዋዕት አቀረበ፤ በዚህም በቤተል ለማምለኪያ ባሠራቸው ስፍራዎች የሚያገለግሉ ካህናትን መደበ፡፡
33ኢዮርብዓምም በዓል እንዲሆን እርሱ ራሱ በወሰነው ስምንተኛ ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን ወደ ቤቴል ሄደ፡፡ በዚያ የእስራኤል ሕዝብ በዓል እንዲያከብር መስዋዕት አዘጋጅቶ ዕጣን ለማጠን ወደ መሠዊያው ሄደ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።