መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

1ኛ ቆሮንቶስ 4

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እንግዲህ ማንም ሰው እኛን የክርስቶስ አገልጋዮችና የእግዚአብሔር የተሰወረው ምሥጢር መጋቢዎች እንደሆነን ሊቆጥረን ይገባል።
2በዚህ መሠረት መጋቢዎች ታማኝ ሆነው መገኘት ይገባቸዋል።
3ነገር ግን በእናንተ ወይም በየትኛውም ፍርድ ቤት መፈረድ ካለብኝ ለእኔ በጣም ትንሽ ነገር ነው።
4እኔ በራሴ እንኳ አልፈርድም። እኔ ምንም ክስ የለብኝም ግን ፍጹም ነኝ ማለቴ አይደለም። በእኔ የሚፈርድ ጌታ ነው።
5ስለዚህ ጊዜ ሳይደርስ፥ ጌታ ከመምጣቱ በፊት ስለምንም ነገር አትፍረዱ።እርሱም በጨለማ የተሰወረውን ወደ ብርሃን ያወጣል፤ የልብንም አሳብ ይገልጣል። በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ምስጋና ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል።
6እንግዲህ ወንድሞችና እህቶች ሆይ፦ "ከተጻፈው አትለፍ" የሚለውን ትርጉሙ ከእኛ መማር እንድትችሉ ስለ እናንተ ስል ለራሴና ለአጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። ይህ ማናችሁም አንዳችሁ በሌላኛችሁ እንዳትታበዩ ነው።
7በእናንተና በሌሎች መካከል ምን ልዩነት አለ? በነጻ ያልተቀበልከውስ ምን አለህ? በነጻ የተቀበልከው ከሆንህ እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድን ነው?
8አሁን የምትፈልጉት ሁሉ አላችሁ! አሁንስ ባለ ጠጎች ሆናችኋል! ከእኛ ተለይታችሁ መንገሥ ጀምራችኋል! በርግጥ እኛ ከእናንተ ጋር መንገሥ እንድንችል እናንተ ብትነግሡ በተመኘሁ ነበር።
9እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች ያደረገን ይመስለኛል። ለዓለም፥ ለመላእክትና ለሰዎች መታያ ሆነናልና።
10እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ጥበበኞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ እናንተ የከበራችሁ ናችሁ፤እኛ ግን የተዋረድን ነን።
11እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፤ እንጥማለን፤ እንራቆታለን፤ ያለርኅራኄ እንደበደባለን፤ ራሳችንን የምናስጠጋበት ስለሌለን እንክራተታለን።
12በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን።
13ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል።
14እነዚህን ነገሮች የጻፍኩላችሁ ላሳፍራችሁ ሳይሆን እንደ ተወደዱ ልጆቼ አድርጌ እንድትታርሙ ልገስጻችሁ ነው።
15በክርስቶስ ብዙ እልፍ አዕላፋት አሳዳጊዎች ቢኖሩአችሁ እንኳ ብዙ አባቶች የሉአችሁም። እኔ ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ልጆቼ ናችሁ።
16እንግዲህ እኔን እንድትመስሉ እለምናችኋለሁ።
17እንግዲህ የተወደደና ታማኝ የሆነውን በጌታ ልጄን ጢሞቲዎስን የላክሁላችሁ ለዚህ ነው ። እኔም በየስፍራውና በየአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደማስተምር፤ በክርስቶስ ያሉትን መንገዶቼ እርሱ ያሳስባችኋል።
18አንዳንዶቻችሁ ግን ወደ እናንተ የማልመጣ መስሎአችሁ በትዕቢት የምትመላለሱ አላችሁ።
19ነገር ግን ጌታ ቢፈቅድ ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ። እነዚህ በትዕቢት የሚመላለሱት የሚናገሩትን ብቻ ሳይሆን ኃይላቸውንም ለማወቅ እሞክራለሁ።
20ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል ብቻ አይደለምና። ምን ትፈልጋላችሁ?
21በበትር ወይስ በፍቅርና በትህትና መንፈስ እንድመጣባችሁ ትፈልጋላችሁ?
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።