1ወንድሞችና እህቶች ሆይ፦ወደ እናንተ ስመጣ ስለ እግዚአብሔር የተሰወረውን የእውነት ምስጢር ሲሰብክላችሁ በሚያባብል የንግግር ችሎታ ወይም በላቅ ጥበብ አልመጣሁም።
2በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀርና፥ እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ እንዳላውቅ ወስኜ ነበርና።
3ወደ እናንተ የመጣሁት በድካምና በፍርሃት፤ እንዲሁም በብዙ መንቀጥቀጥ ነበር።
4መልእክቴና ስብከቴም የመንፈስን ኃይል በመግለጥ እንጂ በሚያባብል የጥበብ ቃል አልነበረም፤
5ይህም እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ ላይ እንዳይመሠረት ነው።
6በእምነታቸው በሰሉት ሰዎች መካከል በጥበብ እንናገራለን፤ ነገር ግን የምንናገረው የዚህን ዓለም ጥበብ ወይም ከጊዜ በኋላ የሚሻሩትን የዚህን ዓለም ገዢዎች ጥበብ አይደለም።
7ይልቁን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን ያዘጃውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን የጥበብ እውነት እንናገራለን።
8የዚህም ዓልም ገዢዎች አንዳቸውም ይህን ጥበብ አላወቁትም፤ በዚያን ጊዜ ይህን አውቀውስ ቢሆን ኖሮ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር።
9ነገር ግን፦ "ዓይን ያላየውን፤ ጆሮም ያልሰማውን፤ በሰውም ልብ ያልታሰበውን፤ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀውን ነገር" ተብሎ ተጽፎአልና።
10እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካይነት የተሰወሩትን ነገሮች ገልጦናን ። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል። በሰው ውስጥ ካለው ከእርሱ መንፈስ በቀር የሰውን አሳብ የሚያውቅ ማን ነው?
11እንዲሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር የሚያውቅ ማንም የለም።
12እኛ ግን ክእግዚአብሔር በነፃ የተሰጠንን እንድናውቅ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበለንም።
13የሰው ጥበብ ሊያስተምር የማይችለውን ነገር ግን የእግዚአብሔር መንፈስ የሚያስተምረውን ስለ እነዚህ ነገሮች በቃላት እንናገራለን። መንፈስ ቅዱስም መንፈሳዊውን ቃላት በመንፈሳዊ ጥበብ ይገልጥልናል።
14የእግዚአብሔር መንፈስ የሌለው ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ስለሚሆንበት አይቀበለውም ። በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም።
15የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት ሰው ሁሉን ይመረምራል፤ እርሱ ግን በማንም አይመረመርም።
16"የጌታን አሳብ ማን አወቀው፤ ማንስ ሊያስተምረው ይችላል?" እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።