1ወንድሞች እና እህቶች፣ ስላወጅሁላችሁ እና እናንተም ጸንታችሁ ስለቆማችሁበት ወንጌል አሳስብባችኋለሁ።
2የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣በዚህ ወንጌል መዳን ይሆንላችኋል፣አለዚያ ግን ማመናችሁ ምንም ጥቅም የለውም።
3ለእናንተ ያስተላለፉሁት በቀዳሚነት አስፈላጊ የሆነውን እና እኔም የተቀበልሁትን ነው፤ መጽሐፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፣
4ተቀበረ፣ በሦስተኛውም ቀን ተነሳ፣መጽሐፍትም ይህን ያረጋግጣሉ።
5ለኬፋ ታየ፣ከዚያም ለእሥራ ሁለቱ።
6እንደገና ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ወንድሞች እና እህቶች በእንድ ጊዜ ታየ። አብዛኛዎቹ እስካሁን ድረስ በሕይወት አሉ፣የተወሰኑት ደግሞ አንቀላፍተዋል።
7ከዚያም ለያዕቆብ፣ደግሞም ለሐዋርያቱ ሁሉ ታየ።
8ከሁሉም በኋላ፣ያለ ጊዜው እንደተወለደ ልጅ ለሆንሁት ለእኔ ታየ።
9ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና። የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን አሳድጃለሁና ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም።
10ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁትን ሆኜአለሁ፣በእኔ ውስጥ የነበረው ጸጋም በከንቱ አልነበረም። ይልቁን ከሁሉም በላይ ጠንክሬ ሠራሁ። ሆኖም ይህ የሆነው ከእኔ ሳይሆን ከእኔ ጋር ካለው የእግዚአብሔር ጸጋ የተነሳ ነው።
11ስለዚህ እኔም ሆንሁ እነርሱ ስንሰብክላችሁ አመናችሁ።
12አሁን ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ ከተሰበከ፣ከእናንተ አንዳንዶች ታዲያ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ?
13ሙታን ትንሣኤ ከሌለ እንግዲያው ክርስቶስም ከሙታን አልተነሳማ።
14ክርስቶስም ካልተነሳ ስብከታችንም፣የእናንተም እምነት ዋጋ የሌለው ሆኗላ።
15እንግዲህ እኛም ስለ እግዚአብሔር የሐሰት ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፣ ምክንያቱም እርሱ ክርስቶስን ሳያስነሳ እኛ አስነስቶታል በማለታችን በእግዚአብሔር ላይ በሐሰት መስክረንበታል።
16ሙታን ካልተነሱ፣ክርስቶስም አልተነሳም ማለት ነው።
17ክርስቶስ ካልተነሳ ደግሞ፣ እምነታችሁ ምንም ዋጋ የለውምናም አሁንም በኃጢአታችሁ አላችሁ።
18ስለዚህ በክርስቶስ ሆነው የሞቱ ደግሞ ጠፍተዋል ማለት ነው።
19ክርስቶስ ተስፋ ያደረግነው ለዚህ ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ከሰዎች ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን።
20አሁን ግን ክርስቶስ ከሙታን ሁሉ በኩር ሆኖ ተነስቷል።
21ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደመጣ፣ የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው በኩል መጥቷል።
22በአዳም ሁሉም እንደሞቱ፣ሁሉም ደግሞ በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ።
23ግን እያንዳንዱ በቅደም ተከተሉ መሠረት፦ ክርስቶስ በኩር፣ ቀጥሎ የክርስቶስ የሆኑት እርሱ ተመልሶ ሲመጣ ሕያዋን ይሆናሉ።
24ከዚያም ክርስቶስ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ ፍጻሜ ይሆናል። ይህም የሚሆነው ግዛትን ሁሉ፣ ሥልጣንን ሁሉ፣ እና ኃይልን ሁሉ ሲደመስስ ነው።
25ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሮቹ ስር እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋል።
26ሊደመሰስ የሚገባው የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው።
27"ሁሉን ከእግሮቹ በታች አደረገ።" ነገር ግን፣"ሁሉን አደረገ፣" ሲል፣ሁሉን እንዲገዛለት ያደረገውን እንደማይጨምር ግልጽ ነው።
28ሁሉም ሲገዛለት፣ ልጁ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል። ይህ የሚሆነው እግዚአብሔር አብ ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ነው።
29አለበዚያ ግን ፤ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ሰዎች ለምን ያደርጉታል? ሙታን ፈጽሞ የማይነሱ ከሆነ፣ስለምን ያጠምቁላቸዋል?
30ስለምንስ በየሰዓቱ አደጋ ውስጥ እንወድቃለን?
31ወንድሞች እና እህቶች፣ ስለ እናንተ በክርስቶስ ባለኝ ትምክህት ይህን እናገራለሁ፦ በየቀኑ እሞታለሁ ።
32በሰው ዓይን ሲታይ፣ በኤፌሶን ከአውሬዎች ጋር መጋደሌ፣ ሙታን የማይነሱ ከሆነ ምን ይጠቅመኛል? "ነገ መሞታችን ስለማይቀር፣እንብላ፣ እንጠጣ።"
33አትታለሁ፦ "መልካም ያልሆነ ግንኙነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።"
34ራሳችሁን ተቆጣጠሩ! የጽድቅ ሕይወት ኑሩ! ኃጢአት ማድረግን አትቅጠጥሉ። አንዳንዶቻችሁ ስለ እግዚአብሔር ዕውቀት የላችሁም። ይህን የምላችሁ ላሳፍራችሁ ነው።
35አንዳንዶች ግን እንዲህ ይላሉ፣"ሙታን የሚነሱት እንዴት ነው? በምን ዓይነት አካል ይመጣሉ?"
36ዕውቀት የጎደላችሁ ናችሁ! የዘራችሁት ዘር ካልሞተ አይበቅልም።
37የዘራችሁት አካል ተምልሶ አይበቅልም፣ይልቁን ዘር ነው እንጂ። ስንዴ ወይም የተዘራውን ሌላ ዓይነት ዘር ሆኖ ይበቅላል።
38እግዚአብሔር እንደወደደ አካልን ይሰጠዋል፣ለእያንዳንዱም ዘር የራሱን አካል ይሰጠዋል።
39ሥጋ ሁሉ አንድ ዓይነት አይደለም። ይልቁን፣ የሰው ሥጋ አለ፣ እንዲሁም የእንሰሳት ሥጋ አለ፣ የአእዋፍት ሥጋም እንዲሁ፣ ዓሣም ደግሞ ሌላ ዓይነት ሥጋ አለው።
40እንዲሁም ደግሞ ሰማያዊ አካልና ምድራዊ አካል አለ። ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር አለ የምድራዊ አካል ክብር ደግሞ ሌላ ነው።
41የፀሐይ ክብር አለ፣ የጨረቃ ክብር ደግሞ ሌላ ነው፣ ከዋክብት ደግሞ ሌላ ክብር አላቸው። የአንዱ ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ይለያል።
42የሙታን ትንሣኤም ልክ እንደዚሁ ነው። የተዘራው የሚጠፋ ነው፣ የሚነሳው ደግሞ የማይጠፋ ነው።
43ሲዘራ በውርደት ሲነሳ ግን በክብር ነው። ሲዘራ በድካም፣ሲነሳ ግን በኃይል ነው።
44የተዘራው ፍጥረታዊ አካል፣የሚነሳው ግን መንፈሳዊ አካል ነው። ፍጥረታዊ አካል እንዳለ ሁሉ መንፈሳዊ አካልም አለ።
45እንዲህም ተብሎ ተጽፎአል፣ "የመጀመሪያው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ።" የመጨረሻው አዳም ግን ሕይወት ሰጭ መንፈስ ሆነ።
46መጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን ፍጥረታዊው ነው፣ከዚያም መንፈሳዊው ተከተለ።
47የመጀመሪያው ሰው ከምድር ሲሆን የተሠራውም ከአፈር ነው። ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው።
48አንዱ ከአፈር እንደተሠራ፣ከአፈር የተሠሩ ሁሉ እንዲሁ ናችው። እንዲሁም ከሰማይ እንደሆነው ሰው፣ ከሰማይ የሆኑትም እንዲሁ ናቸው።
49ልክ እኛ ከአፈር የተሠራውን ሰው እንደምንመስል፣ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩን ሰው መልክ እንይዛለን።
50ወንድሞች እና እህቶች፣ አሁን እንዲህ እላለሁ፣ሥጋ እና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርስ አይችልም። እንዲሁም የሚጠፋው የማይጠፋውን ሊወርስ አይችልም።
51ምስጢር የሆነ እውነት እነግራችኋለሁ፦ ሁላችን አንሞትም፣ግን ሁላችን እንለወጣለን።
52የመጨረሻው መለከት ሲነፋ፣ዐይን ተጨፍኖ እስኪገለጥ ባለ ፍጥነት ድንገት እንለወጣለን። መለከቱ ሲነፋ፣ ሙታን የማይጠፋውን አካል ለብሰው ይነሳሉ፣ እኛም እንለወጣለን።
53ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይለብሳል፣ ሟቹ ደግሞ የማይሞተውን ይለብሳል።
54የሚጠፋው የማይጠፋውን ሲለብስ፣እና ይህ ሟች የሆነው የማይሞተውን ሲለብስ፣ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው ይፈጸማል፣"ሞት በድል ተዋጠ።"
55ሞት ሆይ ድል ማድረግህ የት አለ? ሞት ሆይ መንደፊያህ የት አለ?"
56የሞት መንደፊያ ኃጢአት ነው፣ የኃጢአት ኃይል ደግሞ ሕጉ ነው።
57ነገር ግን በጌታ በክርስቶስ ኢየሱስ ድል የሚሰጠን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!
58ስለዚህ ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ የጸናችሁ እና የማትነቃነቁ ሁኑ። ሁልጊዜም የእግዚአብሔር ሥራ ይብዛላችሁ፣ምክንያቱም በጌታ የምትደክሙት ድካም በከንቱ አይደለም።