1ምነው የእናቴን ጡቶች እንደጠባ እንደ ወንድሜ በሆንክ። ከዚያም በውጭ ባገኘሁህ ጊዜ ሁሉ በሳምኩህና፥ ማንም ባልናቀኝ ነበር።
2በመራሁህና ወደ እናቴ ቤት ባመጣሁህ፥ አንተም ባስተማርከኝ ነበር። የምትጠጣውን ጣፋጭ ወይን ጠጅ በሰጠሁህ፥ ከሮማኖቼም ጭማቂ ጥቂቱን።
3ወጣቷ ለራሷ ስትናገር፥ ግራ እጁ ይዞኛል፤ ቀኝ እጁም አቅፎኛል። ሴቲቱ ለሌሎች ሴቶች ስትናገር፥
4የኢየሩሳሌም ሴቶች ልጆች ሆይ፥ በፍቅር ግንኙነታችን ጊዜ እስክንረካ ድረስ ላታቋርጡን እንድትምሉልኝ እፈልጋለሁ። የኢየሩሳሌም ሴቶች ሲናገሩ፥
5በውዷ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትመጣ ይህቺ ማን ናት? ሴቲቱ ለፍቅረኛዋ ስትናገር፥ ከእንኮዩ ዛፍ ጥላ ሥር አነቃሁህ፤ በዚያ እናትህ ፀነሰችህ፤ በዚያም አንተን ወለደችህ፤ ተገላገለችህ።
6በልብህ ላይ እንደ ማኅተም አስቀምጠኝ፥ እንደ ማኅተም በክንድህ ላይ፥ ፍቅር እንደ ሞት ብርቱ ነውና። የታማኝነቷም ጠንካራ ስሜት እንደ ሲዖል ጨካኝ ነው፤ ነበልባሏ ይነዳል፤ የምትንቦገቦግ ነበልባል ናት፥ ነበልባሏ ከሌላ ከየትኛውም እሳት ይልቅ የጋለ ነው።
7የማዕበል ውሃ ፍቅርን ለማጥፋት አይችልም፥ ጎርፍም ሊያሰጥመው አይችልም። ሰው በቤቱ ያለውን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ብሎ ቢሰጥ ስጦታው ፈጽሞ ይናቃል። የወጣቷ ወንድሞች እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ፥
8ታናሽ እህት አለችን፥ ጡቶቿም ገና አላደጉም። ለጋብቻ በምትሰጥበት በዚያን ቀን ለእህታችን ምን ልናደርግላት እንችላለን?
9እርሷ ቅጥር ብትሆን፥ በላይዋ ላይ የጥበቃ ማማ እንሠራባታለን። በር ብትሆን በዝግባ ሳንቃ እናስውባታለን። ወጣቷ ለራሷ ስትናገር፥
10እኔ ቅጥር ነኝ፥ አሁን ግን ጡቶቼ እንደ ተመሸጉ ግንቦች ናቸው፤ ስለዚህ በዓይኖቹ ፊት በሚገባ አድጌአለሁ። ወጣቷ ለራሷ ስትናገር፥
11ሰለሞን በብኤላሞን የወይን ቦታ ነበረው፤ እርሱም የወይኑን ቦታ ለሚንከባከቡት አከራየው። እያንዳንዱ ስለ ፍሬው አንድ አንድ ሺህ ሰቅል ብር ያመጣለት ነበር።
12የእኔ የወይን ቦታ የእኔው የግሌ ነው፤ ወዳጄ ሰለሞን ሆይ፥ አንድ ሺህ ሰቅሉ ያንተ ይሆናል፥ ሁለት መቶ ሰቅሉ ፍሬውን ለሚንከባከቡት ነው። የሴቲቱ አፍቃሪ ሲናገራት፥
13በአትክልቱ ቦታ የምትኖሪ ሆይ፥ ጓደኞቼ ድምጽሽን እየሰሙት ነው፤ እኔም ከሚሰሙት አንዱ ልሁን። ሴቲቱ ለፍቅረኛዋ ስትናገር፥
14ውዴ ሆይ፥ ፍጠን፤ በቅመማ ቅመም ተራራዎች ላይ የአጋዘንን ወይም የሜዳ ፍየል ግልገልን ምሰል።