መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሮሜ 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የእግዚአብሔርን ወንጌል በሐዋርያነት እንዲያገለግል ተለይቶ ከተጠራው ከኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከጳውሎስ።
2ወንጌሉም በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በነቢያቱ አስቀድሞ ተስፋ የሰጠው ነው።
3ይህም ወንጌል በስጋ ከዳዊት ዘር ስለተወለደው ስለ ልጁ ነው።
4እርሱም በቅድስና መንፈስ ኃይል ከሙታን በመነሳት የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ የተነገረለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር።
5በስሙ ምክንያት ከእምነት የሚገኝ መታዘዝ በሕዝቦች ሁሉ መካከል እንዲሆን በእርሱ በኩል ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን።
6እናንተም በእነዚህ ሕዝቦች መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ ለመሆን ተጠራችሁ።
7ይህ መልዕክት የተጻፈው በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱስ ሕዝብ ለመሆን ለተጠራችሁ በሮም ላላችሁት ሁሉ ነው። ከእግዚአብሔር ከአባታችንና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
8ስለ እምነታችሁ በመላው ዓለም በመነገሩ ምክንያት አስቀድሜ ስለሁላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አምላኬን አመሰግናለሁ።
9ባለማቋረጥ እንደማስባችሁ የልጁን ወንጌል በመንፈሴ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው።
10አሁን በተቻለኝ መጠን በእግዚአብሔር ፈቃድ ተሳክቶልኝ ወደ እናንተ እንድመጣ ሁልጊዜ በጸሎቴ እለምናለሁ።
11የሚያበረታችሁን ጥቂት መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁ፥
12ይኸውም የእኔና የእናንተ በሆነ የእርስ በርሳችን እምነት አማካይነት እንድንበረታታ ስለምጓጓ ነው።
13ወንድሞች ሆይ፥ ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ለመምጣት እንደ ሞከርኩኝና እስካሁን እንደተስተጓጎልኩኝ ሳታውቁ እንድትቀሩ አልፈልግም። ወደ እናንተ መምጣት የፈለግሁበት ምክንያት ከተቀሩት አሕዛብ እንዳገኘሁት ሁሉ ከእናንተ ደግሞ ጥቂት ፍሬ እንዳገኝ ነው።
14ለግሪኮችና ግሪኮች ላልሆኑት፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ ዕዳ አለብኝ።
15ስለዚህ፥ በበኩሌ በሮም ለምትገኙት ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ለመስበክ ተዘጋጅቻለሁ።
16በወንጌል አላፍርም! ምክንያቱም እርሱ አስቀድሞ ለአይሁድ ደግሞም ለግሪኮች የሚያምኑትን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ኃይል ስለሆነ ነው።
17"ጻድቅ በእምነት ይኖራል" ተብሎ እንደተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ በወንጌል ከእምነት ወደ እምነት ተገልጧልና።
18በአመጻቸው እውነትን በሚያፍኑ አመጸኞችና ክፉዎች ሰዎች ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ከሰማይ ተገልጧል።
19ይኽውም እግዚአብሔር ስላስታወቃቸው ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚገባው ነገር ለእነርሱ ግልጥ ነው።
20የማይታዩት ገጽታዎቹ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ግልጥ ሆነው ይታያሉ። እነዚህም በተፈጠሩት ነገሮች አማካይነት ይታወቃሉ። ገጽታዎቹም የዘላለም ኃይሉና የመለኮት ባህርዩ ናቸው። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች የሚያመካኙት አይኖራቸውም።
21ምክንያቱም ስለ እግዚአብሔር ቢያውቁም እንደ እግዚአብሔርነቱ ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት ነው። ይልቁንም በሀሳባቸው ሞኞች ሆኑ፥ የማያስተውለው ልባቸውም ጨለመ።
22ጥበበኞች ነን ቢሉም የማያስተውሉ ሆኑ።
23የማይጠፋውን የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰው አምሳል፥በወፎች፥ አራት እግር ባላቸው አራዊትና በደረታቸው በሚሳቡ ፍጥረታት መልክ ለወጡ።
24ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሰውነታቸውን እንዲያዋርዱ እግዚአብሔር ለልባቸው የክፋት ምኞት ለእርኩሰት አሳልፎ ሰጣቸው።
25እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት የለወጡና በፈጣሪ ፈንታ ፍጥረትን ያመለኩና ያገለገሉ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የተመሰገነ ነው።አሜን።
26ከዚህም የተነሳ እግዚአብሔር ለአስነዋሪ ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፥ ሴቶቻቸውም ለተፈጥሮአቸው የሚገባውን ተግባር ተገቢ ባልሆነው ለወጡ።
27እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለተፈጥሮአቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወተ-ሥጋ ምኞት ተቃጠሉ። እነዚህ ወንዶች የማይገባውን ነገር ከወንድ ጋር በማድረጋቸው ስለ ነውራቸው ቅጣትን የተቀበሉ ናቸው።
28እግዚአብሔርን ለማወቅ ስላልፈቀዱ እነዚያን ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች እንዲያደርጉ ለማይረባ አዕምሮ አሳልፎ ሰጣቸው።
29እነርሱ በአመጻ ሁሉ፥ በጨካኝነት፥ በክፉ ምኞትና በምቀኝነት፥ በቅናት፥ በነፍስ መግደል፥ በጸብ፥ በማታለልና በክፉ ሃሳብ የተሞሉ ናቸው።
30ሐሜተኞች፥ የሰው ስም አጥፊዎችና እግዚአብሔርን የሚጠሉ፥ ቁጡዎች፥ ዕብሪተኞችና ትዕቢተኞች ናቸው። ክፉ ነገሮችን የሚያመነጩና ለወላጆቻችው የማይታዘዙ፥
31ማስተዋል የሌላቸው፤ እምነት የማይጣልባቸው፥ ፍቅር የሌላቸውና የማይምሩ ናቸው።
32እንደዚህ ያሉትን ነገሮች የሚያደርጉ ሞት እንደሚገባቸው የሚናገረውን የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ያውቃሉ፥እነርሱ ግን እነዚህኑ ነገሮች ራሳቸው የሚያደርጉ ብቻ ሳይሆኑ የሚያደርጉትን ሌሎችን የሚያበረታቱ ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።