መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መጽሐፈ መዝሙር 94

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የበቀል አምላክ አንተ ያህዌ ሆይ፣ የበቀል አምላክ ሆይ፣ ብርሃንህ ይብራልን፡፡
2የምድር ዳኛ ሆይ፣ ተነሥ ለትዕቢተኞች የእጃቸውን ስጣቸው፡፡
3ያህዌ ሆይ፣ ክፉዎች እስከ መቼ፣ ክፉዎች እስከ መቼ ነው የሚፈነጩት?
4የእብሪት ቃሎች ያዥጐደጉዳሉ ክፉ አድራጊዎችም ሁሉ ጉራ ይነዛሉ፡፡
5ያህዌ ሆይ፣ ሕዝብህን ያደቅቃሉ የአንተን ወገኖች ይጨቁናሉ፡፡
6በአገራቸው የሚኖሩ መበለቶችንና መጻተኞችን ይገድላሉ፤
7«ያህዌ አያይም፤ የያዕቆብ አምላክም አያስተውልም» ይላሉ፡፡
8እናንት አላዋቂዎች ይህን አስተውሉ፤ እናንት ሞኞች ለመሆኑ፣ ጥበበኞች የምትሆኑት መቼ ነው?
9ጆሮን የተከለ እርሱ አይሰማምን? ዐይንን የሠራ እርሱ አያይምን?
10ሕዝቦችን የሚገሥጸው አይቀጣምን? ለሰው ዕውቀት የሚሰጥ እርሱ ነው፡፡
11ያህዌ የሰው ሐሳብ ከንቱ እንደ ሆነ ያውቃል፡፡
12ያህዌ ሆይ፣ አንተ የምትገሥጸው ሕግህንም የምታስተምረው ሰው ቡሩክ ነው፡፡
13ለክፉዎች ጉድጓድ እስኪቆፈር ድረስ አንተ እርሱን ከመከራ ታሳርፈዋለህ፡፡
14ያህዌ ሕዝቡን አይጥልምና ርስቱንም አይተውም፡፡
15ፍርድ ተመልሶ በጽድቅ አሠራር ላይ ይመሠረታል ልበ ቀናዎችም ሁሉ ይከተሉታል፡፡
16ክፉዎችን የሚቋቋምልኝ ማን ነው? ከክፉ አድራጊዎች የሚሟገትልንስ ማን ነው?
17ያህዌ ረዳቴ ባይሆን ኖሮ ፈጥኜ ወደ ዝምታው ዓለም በወረድሁ ነበር፡፡
18እኔ፣ «እግሬን አዳለጠኝ» ባልሁ ጊዜ ያህዌ ሆይ፣ ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ፡፡
19ሐዘኔ በበዛ ጊዜ፣ ማጽናናትህ ደስ አሰኘኝ፡፡
20ዓመፅን ሕጋዊ የሚያደርግ የጥፋት ዙፋን ከአንተ ጋር ሊያብር ይችላልን?
21ጻድቃንን ለማጥፋት ያሤራሉ በንጹሐን ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ይበይናሉ፡፡
22ለእኔ ግን ያህዌ ጠንካራ ምሽግ አምላኬም መጠጊያ ዐለት ሆኖኛል፡፡
23ኃጢአታቸውን ወደ ራሳቸው ይመልሳል በገዛ ክፋታቸውም ያጠፋቸዋል፡፡ ያህዌ አምላካችን ይደመስሳቸዋል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።