1እግዚአብሔር ሆይ፣ ጸሎቴን ስማ ልመናዬንም ቸል አትበል፡፡
2ችግሬ ዕረፍት ነስቶኛልና ወደ እኔ ተመልከት መልስልኝም፡፡
3ከጠላቶቼ ዛቻ የተነሣ፣ ፈርቼአለሁ፤ በክፉዎችም ጭቈና ደቅቄአለሁ፡፡ መከራ አምጥተውብኛል፤ በቁጣም ያሳድዱኛል፡፡
4ልቤ በውስጤ ተሸበረብኝ የሞት ድንጋጤም መጣብኝ፡፡
5ፍርሃትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ ሽብርም በረታብኝ፡፡
6እኔም እንዲህ አልሁ፣ «ምነው የርግብ ክንፍ በኖረኝ! በርሬ ሄጄ ዐርፍ ነበር፡፡
7እነሆ፣ ኮብልዬ በራቅሁ ነበር በምድረ በዳ በሰነበትሁ ነበር፡፡ ሴላ
8ከዐውሎ ነፋስና ከውሽንፍር ሸሽቼ ወደ መሸሽጊያ ፈጥኜ በደረስሁ ነበር፡፡»
9ግፍና ሁከት በከተማዪቱ ዐይቻለሁና ጌታ ሆይ ግራ አጋባቸው፤ ቋንቋቸውንም ደበላልቅ!
10ቀንና ሌሊት ቅጥሮቿን ይዞራሉ ተንኰልና መከራ በውስጧ አሉ፡፡
11ዐመፃ በመካከልዋ ነው፤ ግፍና አታላይነት ከጐዳናዋ አይጠፋም፡፡
12የሰደበኝ ጠላት አይደለም ያማ ቢሆን በታገሥኩ ነበር፤ የሚታበይብኝ፣ ራሱንም ቀና ቀና ያደረገብኝ ባላንጣ አይደለም፤ ያማ ቢሆን፣ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር፡፡
13ነገር ግን ያን ያደረግህ አንተ እኩያየ፣ ባልንጀራዬና የቅርብ ወዳጄ ነህ፡፡
14ደስ የሚል ኅብረት በአንድነት ነበረን በሕዝቡ መካከል በእግዚአብሔር ቤት አብረን ተመላልሰን ነበር፡፡
15በድንገት ሞት ይምጣባቸው ክፋት በመካከላቸው ናትና በሕይወታቸው እያሉ ወደ ሲኦል ይወረዱ፡፡
16እኔ ግን እግዚአብሔርን እጣራለሁ ያህዌም ያድነኛል፡፡
17በማታ፣ በጧትና በቀትር አቃሥታለሁ እቃትታለሁም እርሱም ድምፄን ይሰማል፡፡
18ከእኔ ጋር የሚዋጉት ብዙ ናቸውና እርሱ፣ ከተከፈተብኝ ጦርነት በሰላም ይታደገኛል፡፡
19ስለማይለወጡና አምኬንም ስለማይፈሩ ከዘላለም እስከ ዘላለም ዙፋኑ ላይ ያለው እግዚአብሔር ሰምቶ ያዋርዳቸዋል፡፡ ሴላ
20ጓደኛዬ የምለው ሰው እጁን በወዳጆቹ ላይ ሰነዘረ፤ ቃል ኪዳኑንም አፈረሰ፡፡
21አፉ ከቅቤ ይልቅ የለዘበ ነው በልቡ ግን ጦርነት አለ፤ ቃሉ ከዘይት ይልቅ የለሰለሰ ነው ሆኖም የተመዘዘ ሰይፍ ነው፡፡
22የከበድህን ነገር በያህዌ ላይ ጣል እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁን መናወጥ ከቶ አይፈቅድም፡፡
23አንተ ግን እግዚአብሔር ሆይ፣ ዐመፀኞችን ወደ ጥፋት ጉድጓድ ታወርዳቸዋለህ ደም የተጠሙና አታላዮች የዕድሜያቸውን ግማሽ እንኳ አይኖሩም፡፡ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ፡፡