1የእስራኤል ንጉስ፣ የዳዊት ልጅ የሰለሞን ምሳሌዎች፡፡
2እነዚህ ምሳሌዎች የተጻፉት ጥበብንና ተግሳጽን፣ አርቆ ለማስተዋል የሚያስችሉ ቃላትን፣
3እርማትን በመቀበል ጽድቅ፣ ፍትሕና ሚዛናዊ የሆነ ብያኔን በማድረግ እንድትኖር ለማስተማር ነው፡፡
4ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ምሳሌዎች የተጻፉት ላልተማሩ ጥበብን፣ ለወጣቶች ደግሞ እውቀትንና ልባምነትን ለመስጠት ነው፡፡
5ጥበበኞች ያድምጡና ትምህርታቸውን ያዳብሩ፣ አስተዋዮች ደግሞ ምሪትን ያግኙበት፣
6ይህ ደግሞ የጠቢባንን ምሳሌዎች፣ አባባሎችና ቃላቶች እንደዚሁም እንቆቅልሾቻቸውን እንዲረዱ ነው፡፡
7እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመርያ ነው፣ ሞኞች ግን ጥበብንና ተግሳጽን ይንቃሉ፡፡
8ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው፤
9ለራስህ የሞገስ አክሊል፣ ለአንገትህ ደግሞ ውበት የሚሰጥ ጌጥ ይሆኑልሃል፡፡
10ልጄ ሆይ፣ ኃጢአተኞች በኃጢአታቸው እንድትሳተፍ ሊያባብሉህ ቢሞክሩ፣ እሺ አትበላቸው፡፡
11“ከእኛ ጋር ና፣ ነፍስ ለመግደል ተደብቀን እንጠብቅ፣ ንጹሐን ሰዎችን ያለ ምንም ምክንያት ለማትፋት እንሸምቅበት፡፡
12ሲኦል ጤናማ ሰዎችን እንደሚውጣቸው፣ ወደ ጉድጓድ እንደሚወርዱ፣ እንዲሁ በሕይወት እያሉ እንዋጣቸው፡፡
13ሁሉም አይነት ውድ የሆኑ ነገሮች እናገኛለን፤ ከሌሎች ሰዎች በሰረቅናቸው ነገሮች ቤቶቻችንን እንሞላለን፡፡
14ከእኛ ጋር ዕጣህን ጣል፤ ሁላችንም አንድ የጋራ ቦርሳ ይኖረናል፡፡” ቢሉህ፣
15ልጄ ሆይ፣ ከእነርሱ ጋር በዚያ መንገድ አትሂድ፤ እነርሱ በሚሄዱበት መንገድ እግርህ አይርገጥ፤
16እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉ፣ ደም ለማፍሰስም ይቸኩላሉ፡፡
17ወፍ ፊት ለፊት እያየች ወፍን ለመያዝ ወጥመድ መዘርጋት ጥቅም የለውም፡፡
18እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ለመግደል ተደብቀው ይጠብቃሉ፣ በራሳቸው ላይ ወጥመድን ይዘረጋሉ፡፡
19ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ሀብትን ያከማቹ ሰዎች መንገዳቸው እንደዚህ ነው፣ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የተከማቸ ሃብት የባለቤቱን ሕይወት ያጠፋል፡፡
20ጥበብ በጎዳና ላይ ጮኻ ትጣራለች፣ በአደባባይም ድምጿን ከፍ ታደርጋለች፤
21ጩኸት በበዛባቸው ጎዳናዎች ላይ ትጣራለች፣ በከተማ መግቢያ በሮች ላይ እንዲህ በማለት ትናገራለች፣
22እናንተ ጥበብ የሌላችሁ አላዋቂነትን የምትወዱት እስከ መቼ ነው? እናንተ ፌዘኞች በፌዝ የምትደሰቱት እስከ መቼ ነው? እናንተ ሞኞች እውቀትን የምትጠሉት እስከ መቼ ነው?
23ለዘለፋየ ትኩረት ስጡ፤ ሃሳቤን ሁሉ ለእናንተ አፈስሳለሁ፤ ቃሎቼን አሳውቃችኋለሁ፡፡
24ጠራኋችሁ፣ እናንተ ግን ለመስማት እምቢ አላችሁ፤ እጄን ለእናንተ ዘረጋሁ፣ ነገር ግን አንድም ሰው ትኩረት አልሰጠውም፡፡
25ነገር ግን እናንተ ተግሳጼን በሙሉ ችላ አላችሁ፣ ለዘለፋየ ደግሞ ትኩረት አልሰጣችሁም፡፡
26እኔ ደግሞ በመከራችሁ እስቃለሁ፣ ሽብር በመጣባችሁ ጊዜ አላግጥባችኋለሁ፣
27አስፈሪ ድንጋጤ እንደ ማዕበል በእናንተ ላይ ሲመጣባችሁ፣ ጥፋት እንደ አውሎ ነፋስ እናንተን ሲጠራርጋችሁ፣ ጭንቅና ችግር በእናንተ ላይ በመጣ ጊዜ፡፡
28በዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፣ እኔም አልመልስላቸውም፤ አጥብቀው ይፈልጉኛል፣ ነገር ግን አያገኙኝም፡፡
29እውቀትን ስለ ጠሉ፣ እግዚአብሔርን መፍራት ስላልመረጡ፣
30ምክሬን አልተከተሉምና፣ ዘለፋየንም ሁሉ ናቁ፡፡
31የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፣ በእቅዳቸው ፍሬ ይጠግባሉ፡፡
32እነዚህ ያልተማሩ ሰዎች ከእውቀት መራቃቸው ይገድላቸዋል፣ ሞኞችንም ቸልተኝነታቸው ያጠፋቸዋል፡፡
33ነገር ግን የሚያደምጠኝ ሁሉ በሰላም ይኖራል፣ ከመከራም ስጋት ያርፋል፡፡