መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ነህምያ 13

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በዚያን ቀን እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን አሞናዊያን ወይም ሞአባዊያን የእግዚአብሔር ህዝቦች ወደሚያመልኩበት ስፍራ አይግቡ የሚለውን የህጉን ክፍል ካህናቱ ለህዝቡ አነበቡ፤ ህዝቡም አደመጠ፡፡
2ይህ የሆነው የአሞንና የሞአብ ሰዎች እስራኤላዊያን ከግብጽ ወጥተው ወደሚገቡበት አገር ሲጓዙ ምንም ምግብ ወይም ውሃ ስላልሰጧቸው ነበር፡፡ ይልቁንም፣ የአሞንና የሞብ ሰዎች በለዓም እስራኤላዊያንን እንዲረግም ገንዘብ ከፈሉት፡፡ እግዚአብሔር ግን እስራኤልን ለመርገም የተደረገውን ያን ጥረት ወደ በረከት ለወጠው፡፡
3ስለዚህም ህዝቡ እነዚያ ህጎች ሲነበቡላቸው በሰሙ ጊዜ፣ አባቶቻቸው ከሌሎች አገሮች የሆኑትን ሰዎች ሁሉ አስወጡ፡፡
4አስቀድሞ፣ ካህኑ ኤልያሴብ በቤተ መቅደሱ የግምጃ ቤቱ ኃላፊ ሆኖ ተሹሞ ነበር፡፡ እርሱም የጦቢያ ቤተዘመድ ነበር፡፡ እነርሱም የእህል ቁርባኖቹንና እጣኑን በዚያ ስፍራ አከማቹ፡፡
5ለቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ዕቃዎችን በዚያ አስቀመጡ፡፡ ህዝቡ ለሌዋውያን የሰጠውን ስጦታዎች በግምጃ ቤት አስቀመጡ፡፡ እግዚአብሔር ለሌዋውያኑ፣ ለዘማሪዎቹና ለበር ጠባቂዎች እንዲሰጡ ያዘዘውን የእህል፣ የወይንና የወይራ ዘይት አስራት አመጡ፡፡ ሌሎች ካህናትን ለመደገፍም ስጦታዎቹን አመጡ፡፡
6በዚያን ጊዜ እኔ ኢየሩሳሌም ውስጥ አልነበርኩም፡፡ አርጤክስስ የባቢሎን ንጉስ በነበረበት በሰላሳ ሁለተኛው አመት ያከናወንኩትን ለንጉሱ ለመናገር ተመለስኩ፡፡ ለጥቂት ጊዜ በዚያ ከቆየሁ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም እንድመለስ እንዲፈቅደልኝ ንጉሱን ጠየቅሁት፡፡
7ስመለስ፣ ኤልያሴብ ያደረገውን ክፉ ነገር አወቅሁ፡፡ ጦቢያ ለእግዚአብሔር የተለየውን አንድ ክፍል ቤት ለገዛ ጥቅሙ እንዲያውለው ትቶለት ነበር፡፡
8እኔም በጣም ተቆጣሁ፡፡ ወደዚያ ክፍል ገብቼ የጦቢያ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ አውጥቼ ጣልኩ፡፡
9ከዚያ ያንን ክፍል እንደገና ለማንጻት የማንጻት ሥርኣት እንዲደረግ አዘዝኩ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የሚውሉ ማናቸውም ዕቃዎችና የእህል ቁርባኖችን እንዲሁም እጣኑ ወደነበሩበት ወደዚያ ክፍል እንዲመለሱ አዘዝኩ፡፡
10የእስራኤል ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ቀለብ ወደ ግምጃ ቤት ስላላመጡአቸው፣ የቤተ መቅደሱ ዘማሪዎችና ሌሎች ሌዋውያን ኢየሩሳሌምን ለቀው ወደ እርሻዎቻቸው መመለሳቸውን ተረዳሁ፡፡
11ስለዚህ ሹማምንቱን እንዲህ ስል ገሰጽኳቸው፣ “በቤተ መቅደስ ለሚካሄደው አገልግሎት ጥንቃቄ ያላደረጋችሁት ለምንድን ነው?” ስለዚህም እነርሱን በአንድነት ሰብስቤ ወደ መጀመሪያ ስፍራቸው መለስኳቸው፡፡
12ከዚያ የይሁዳ ሰዎች በሙሉ የእህል፣ የወይንና የወይራ ዘይት አስራታቸውን ወደ ቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት ዳግም ማምጣት ጀመሩ፡፡
13እኔም እነዚህን ሰዎች የግምጃ ቤቶቹ ሀላፊዎች አድርጌ ሾምኳቸው፡፡ እነርሱም ካህኑ ሰሌምያ፣ የአይሁድ ህግ አዋቂው ሳዶቅ፣ እና ከሌዊ ወገን የሆነው ፈዳያ ናቸው፡፡ እነርሱን እንዲረዳ የመታንያን የልጅ ልጅ የዘኩርን ልጅ ሐናን ሾምኩት፡፡ እነዚያ ሰዎች ለሠራተኞቹ ወገኖቸው ስጦታዎችን በትክክል እንደሚያከፋፍሉ ልተማመንባቸው እንደምችል አውቅ ነበር፡፡
14አምላኬ ሆይ፣ ለአንተ ቤተ መቅደስ የሰራኋቸውን እነዚህን መልካም ሥራዎችና እዚህ ለተሰራው ሰራ ሁሉ ያደረኩትን አትርሳ!
15በእነዚያ ጊዜያት፣ ይሁዳ ውስጥ አንዳንዶች በሰንበት ቀን ሲሰሩ አየሁ፡፡ አንዳንዶች ወይን ለመጥመቅ የወይን ፍሬ ይረግጡ ነበር፡፡ ሌሎች እህል፣ የወይን አቁማዳዎች፣ የወይን ፍሬ የሞሉ ቅርንጫቶች፣ በለስ፣ እና ሌሎች ብዙ ነገሮች በአህዮቻቸው ጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ይወስዱ ነበር፡፡ በሰንበት ለይሁዳ ሰዎች ምንም ነገር እንዳይሸጡ አስጠነቀቅኳቸው፡፡
16ደግሞም በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አንዳንድ የጢሮስ ሰዎች በሰንበት ቀን አሳና ሌሎች ነገሮችን ለአይሁድ ሰዎች ለመሸጥ ወደ ኢየረሳሌም ሲያመጡ አይሁ፡፡
17ስለዚህ የአይሁድን መሪዎች በመገሰጽ እንዲህ አልኳቸው፣ “ይህ የምታደርጉት በጣም ክፉ ነገር ነው! በሰንበት ቀን እግዚአብሔር በፍጹም እንዲሆን የማይወደውን ነገር እያደረጋችሁት ነው፡፡
18አባቶችሁ እንደዚህ ያለ ነገሮችን አደረጉ፣ ስለዚህም እግዚአብሔር ቀጣቸው፡፡ በእነርሱ ኃጢአት ምክንያት ይህች ከተማ እንድትጠፋ ፈቅዶ ነበር! እና አሁን የሰንበት ቀን ህግጋትን በመተላፍ እግዚአብሔር በእኛ ላይ እንዲቆጣ ምክንያት እየሆናችሁ ነው፣ እናም የከፋ ቅጣት ይቀጣናል!”
19ቀኑ ሲመሽ በኢየሩሳሌም መግቢያ ላይ አንዳንድ የራሴን ሰዎች አቆምኩ፣ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በዚያን ቀን ምንም አይነት የሚሸጥ ዕቃ ማንም ሰው ወደ ከተማይቱ እንዳያስገባ ያደርጋሉ፡፡
20ነጋዴዎችና ሻጮች የተለያዩ አይነት ዕቃዎችና ሸቀጦች እንዲሁም አንዳንድ ነገሮችን በማግስቱ ለመሸጥ ተስፋ አድርገው ሰንበት ከሚጀምርበት ከአርብ ምሽት አንስቶ ከኢየሩሳሌም ውጭ ለጥቂት ጊዜ ይሰፍራሉ፡፡
21እኔም እንዲህ ስል አስጠነቀቅኳቸው፣ “ዓርብ ምሽት ከቅጥሩ ውጭ በዚህ ማደራችሁ አይጠቅማችሁም! ይህን ደግማችሁ ብታደርጉ፣ እኔ ራሴ አስወጣችሁና አባርራችኋለሁ!” ስለዚህ ከዚያ በኋላ፣ ዳግመኛ በሰንበት ቀናት ተመልሰው አልመጡም፡፡
22እንደዚሁም ደግሞ የሌዊ ትውልዶች፤ ራሳቸውን ለማንጻት የማንጻት ሥርዓቱን እንዲፈጽሙና የከተማዋን በሮች ለመጠበቅ ስፍራቸውን እንዲይዙ፣ በዚያ የተቀደሰ ቀን ነጋዴዎች እንዳይገቡ በመከልከል ሰንበት ቅዱስ ሆኖ መጠበቁን እንዲያረጋግጡ አዘዝኳቸው፡፡ አምላኬ ሆይ፣ ስለዚህም ደግሞ አሰበኝ! እንደ ታላቅ ፍቅርህ መጠን ምህረትህን አድርግልኝ፡፡
23በዚያን ጊዜ ብዙዎቹ የአይሁድ ወንዶች ከአሽዶድ፣ አሞንና ሞዓብ ሴቶች ጋር መጋባታቸውን አወቅሁ፡፡
24ከልጆቻቸው እኩሌቶቹ የኖሩበትን ህዝብ የአሽዶድ ሰዎችን ቋንቋ ወይም ሌላ ቋንቋ ይናገሩ እንጂ የአይድን ቋንቋ መናገር አይችሉም ነበር፡፡
25ስለዚህም እነዚያን ሰዎች ገስጽኳቸው፣ እግዚአብሔር የተረገሙ እንዲያደርጋቸው ጠየቅኩት፤ አንዳንዶቹን በቡጢ መታኋቸው፤ የአንዳንዶቹንም ጸጉር ነጨሁ! ከዚያ እግዚአብሔር እንደሚሰማ በማወቅ ዳግመኛ ባዕዳንን እንዳያገቡና ልጆቻቸውም ከባዕዳን ጋር እንዲጋቡ እንዳይፈቅዱ ጥብቅ ቃል ኪዳን እንዲገቡ አስገደድኳቸው፡፡
26እንዲህ አልኳቸው፣ “የእስራኤል ንጉስ፣ ሰለሞን፣ ከባዕድ ሴቶች ጋር በመጋባቱ ምክንያት ኃጢአት ሰራ፡፡ እርሱ ከሌሎች መንግስታት ነገስታት ሁሉ ታላቅ ነበር፡፡ እግዘአብሔር ወዶት በመላው የእስራኤል ህዝብ ላይ ንጉስ አደረገው፡፡ ነገር ግን ባዕዳን የሆኑት ሚስቶቹ ኃጢአት እንዲሰራ ምክንያት ሆኑ፡፡
27እናንተ ስህተት መሆኑን እያወቃችሁ ባዕድ ሚስቶችን እንዳገባችሁና ጣኦት አምላኪ የሆኑ ባዕድ ሴቶችን በማግባት በአምላካችሁ ላይ ታላቅ ኃጢአት እንደፈፀማችሁ እኛም ያንን ማድረግ ያለብን ይመስላችኋልን?”
28ከዮአዳ ልጆች አንዱ፣ የሊቀ ካህኑ የአልያሴብ ልጅ የሰንበላጥን ልጅ አገባ፡፡ ስለዚህ የዮአዳን ልጅ ከኢየሩሳሌም አባረርኩት፡፡
29አምላኬ ሆይ በክህነት ማዕረግ ላይ ዕፍረት ያስተሉትን አስብ፣ እናም በስራቸው የክህነትንና የሌዋዊነትን ቃል ኪዳን ተላልፈዋል!
30ከሌሎች አገሮችና ሀይማኖቶች ካመጧቸው ማናቸውም ነገር አነፃኋቸው፣ እንደዚሁም ለካህናቱና ለሌዊ ወገኖች ደንቦችን ሰጠሁ፣ ስለዚህም እያንዳንዳቸው ማድረግ የለባቸውን ያውቃሉ፡፡
31በተወሰነው ጊዜና ቀናት በመሰዊያው ላይ የሚነድ ማገዶ ስለመኖሩ አረጋገጥሁ፡፡ ህዝቡ ከምርቱ በኩራቱን ወደ ግምጃ ቤት እንዲያመጣ መመሪያ ሰጠሁ፡፡ አምላኬ ሆይ፣ እዚህን ሁሉ ነገሮች ማድረጌን አትርሳ፣ እነዚህን በማድረጌም ባርከኝ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።