1ደም ለሞላባት ከተማ ወዮላት! ሐሰትና የተዘረፈ ንብረት ሞልቶበታል፡፡
2አሁን ግን የአላንጋ ድምፅና የመንኰራኩር ኳኳታ ድምፅ፣ የፈጣን ፈረስ ኮቴ፣ የሰረገሎች መንጓጓት ይሰማል፡፡
3የሚያብረቀርቅ ሰይፍና የሚያንጸባርቅ ጦር የያዙ ፈረሰኞች ጥቃት ያደርሳሉ፤ የሞተው ብዙ ነው፤ ሬሳ በሬሳ ተከምሮአል እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ አጥቂዎቹ በሞቱት ሰዎች ሬሳ ይሰናከላሉ፡፡
4ይህ ሁሉ የሆነው ገደብ በሌለው የአመንዝራዋ ፍትወት ምክንያት ነው፤ እርሷ በዝሙቷ መንግሥታን፣ በጥንቆላዋም ሕዝቦችን ባሪያ አድርጋለች፡፡
5የሰራዊት ጌታ ያህዌ እንዲህ ይላል፣ «እኔ በጠላትነት ተነሥቼብሻለሁ ዕርቃንሽን ለሕዝቦች፣ ኅፍረተ ሥጋሽን ለመንግሥታት አሳያለሁ፡፡
6በጣም የሚያስጸይፍ ቆሻሻ እደፋብሻለሁ፤ እንቅሻለሁ፤ ሰው ሁሉ እንዲሳለቅብሽ አደርጋለሁ፡፡
7የሚያይሽ ሁሉ ከአንቺ እየሸሸ፣ «ነነዌ ፈራርሳለች፤ ማን ያለቅስላታል? የሚያጽናናትንስ ከወዴት አገኛለሁ?» ይላል፡፡
8ነነዌ ሆይ፣ ለመሆኑ አንቺ ዐባይ ወንዝ አጠገብ ከተሠራችውና በውሃ ከተከበበችው፣ ወንዙ መከላከያ፣ ባሕሩ ራሱ ቅጥራ ከሆነለት ከቴብስ ትበልጫለሽን?
9ኢትዮጵያና ግብፅ ወሰን የለሽ ኃይሏ ነበሩ ፉጥና ሊቢያም ረዳቶቿ ነበሩ፡፡
10ያም ሆኖ፣ ቴብስ ተጋዘች፤ በምርኮም ተወሰደች ሕፃናቷ በየመንገዱ ማእዘን ላይ ተፈጠፈጡ፤ በመኳንንቷ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ ታላላቅ ሰዎቿ ሁሉ በሰንሰለት ታሰሩ፡፡
11አንቺ ደግሞ ትሰክሪያለሽ መደበቅ ትሞክሪያለሽ ከጠላቶችሽ መሸሸጊያም ትፈልጊያለሽ፡፡
12ምሽጐችሽ ሁሉ ቀድሞ እንደ ደረሰ፣ ሲነቀነቅ በላተኛው አፍ ውስጥ እንደሚወድቅ የበለስ ፍሬ ሆነዋል፡፡
13ወታደሮችሽ እንደ ሴት ፈሪዎች ሆነዋል የምድርሽ በሮች ወለል ብለው ለጠላቶችሽ ተከፍተዋል፡፡ መዝጊያዎቻቸውን እሳት በልቷቸዋል፡፡
14ለከበባው ውሃ ቅጂ፣ ምሽጐችሽን አጠናክሪ፤ ጭቃ ረግጠሸ የሸክላ መሥሪያ አዘጋጂ፤ ጡብም ሥሪ፡፡
15በዚያ እሳት ይበላሻል፤ ሰይፍ ያጠፋሻል፤ አንበጣ ማንኛውንም ነገር እንደሚጠፉ ያጠፋሻል፡፡ ስለዚህ እንደ አንበጣ እርቢ እንደ ኩብኩባም ተባዢ፡፡
16ነጋዴዎችሽን ከሰማይ ከዋክብት ይበልጥ አብዝተሻል፤ ይሁን እንጂ፣ ምድሪቱን እንደ አንበጣ ጋጡ፤ ከዚያም በርረው ሄዱ፡፡
17መኳንንቶችሽ የአንበጦችን ያህል ብዙ ናቸው፣ የጦር መሪዎችሽ በብርድ ቀን ቅጥር ሥር እንደሚቀመጥ የኩብኩባ መንጋ ናቸው፡፡ ፀሐይ ሲወጣ ግን በርረው ይሄዳሉ፤ የት እንደሚሄዱም አይታወቅም፡፡
18የአሦር ንጉሥ ሆይ፣ እረኞችህ አንቀላፉ መኳንንትህ ዐርፈው ተኙ፡፡ ሕዝብህ ሰብሳቢ አጥተው በየተራሮች ተበትነዋል፡፡
19ቁስልህን መፈወስ የሚችል የለም፤ ቁስልህ እጅግ ጽኑ ነው፡፡ ስለ አንተ የሚሰማ ሁሉ በውድቀትህ ደስ ብሎት ያጨበጭባል፡፡ ወሰን ከሌለው ጭካኔህ ማን ያመለጠ አለ?