1ከዚያም በኋላ በዲያብሎስ ሊፈተን መንፈስ ኢየሱስን ወደ ምድረ በዳ መራው፡፡
2ኢየሱስ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ፡፡
3ፈታኙ ወደ እርሱ መጣና፣ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ እንጀራ እንዲሆኑ እነዚህን ድንጋዮች እዘዛቸው›› አለው፡፡
4ኢየሱስ ግን መለሰና፣ ‹‹ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል" አለው፡፡
5ከዚያም ዲያብሎስ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ወሰደው፤ በቤተ መቅደስ ሕንጻ ዐናት ላይም አቁሞ፣
6የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ ራስህን ወደ ታች ወርውር፤ ‹እንዲጠብቁህ መላእክቱን ይልካል፣› እና ‹‹እግርህ ድንጋይ እንዳይመታው፣ በእጆቻቸው ያነሡሃል›› ተብሎ ተጽፎአል አለው፡፡
7ኢየሱስም፣ ‹‹‹ጌታ አምላክህን አትፈታተን› ተብሎም ተጽፎአል›› አለው፡፡
8እንደ ገናም ዲያብሎስ ወደ አንድ ተራራ ወሰደውና የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ከሙሉ ክብራቸው ጋር አሳየው፡፡
9‹‹ብትወድቅና ብትሰግድልኝ፣ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ›› አለው፡፡
10ከዚያም ኢየሱስ፣ አንተ ሰይጣን ከዚህ ሂድ! ‹ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፣ እርሱንም ብቻ አምልክ››› ተብሎ ተጽፎአልና አለው፡፡
11ከዚያ በኋላ ዲያብሎስ ተወው፤ እነሆም፣ መላእክት መጡና ኢየሱስን አገለገሉት፡፡
12ኢየሱስ የዮሐንስን መያዝ ሲሰማ፣ ወደ ገሊላ ሄደ፡፡
13ናዝሬትን ትቶ በመሄድ በዛብሎንና በንፍታሌም አገር በገሊላ ባሕር አጠገብ ባለው በቅፍርናሆም ኖረ፡፡
14ይህ የሆነው፣ በነቢዩ ኢሳይያስ ተነግሮ የነበረው እንዲፈጸም ነው፤ ይኸውም፡-
15‹‹የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፣ በባሕሩ አቅጣጫ፣ ከዮርዳኖስ ማዶ፣ የአሕዛብ ገሊላ!
16በጨለማ ውስጥ የኖረ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፣ በሞት ጥላና ምድር ውስጥ ለሚኖሩትም፣ ብርሃን ወጣላቸው›› የሚለው ነው፡፡
17ኢየሱስ ከዚያ ጊዜ አንሥቶ፣ ‹‹መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ›› እያለ መስበክ ጀመረ፡፡
18ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ እየሄደ ሳለ፣ ሁለት ወንድማማቾችን አየ፤ ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ፣ ወደ ባሕሩ መረብ እየጣሉ ነበር፡፡
19ኢየሱስ፣ ‹‹ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን የምታጠምዱ አደርጋችኋለሁ›› አላቸው፡፡
20እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት፡፡
21ኢየሱስ ከዚያ ዐለፍ እንዳለም ሁለት ሌሎች ወንድማማቾችን፣ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን አየ፤ ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በጀልባ ውስጥ መረቦቻቸውን ያበጃጁ ነበር፡፡ ኢየሱስም ጠራቸው፡፡
22ወዲያውኑ ጀልባዋንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት፡፡
23ኢየሱስ በምኵራቦቻቸው ውስጥ እያስተማረ፣ የመንግሥትን ወንጌልም እየሰበከና በሕዝቡ መካከል ያሉ በሁሉም የደዌና የበሽታ ዐይነት የሚሠቃዩትን እየፈወሰ በመላው ገሊላ ተዘዋወረ፡፡
24ስለ እርሱ በሶርያ ምድር ሁሉ ተወራ፤ ሕዝቡም የታመሙትን ሁሉ፣ በልዩ ልዩ ደዌና ሕመም የሚሠቃዩትን፣ በአጋንንት የተያዙትንና የሚጥል በሽታ ያለባቸውን፣ ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው፡፡
25ከገሊላ፣ ከዐሥሩ ከተሞች፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት፡፡