1በሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ሴቶች ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው በጣም ማልደው ወደ መቃብሩ መጡ።
2ድንጋዩ ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት።
3ወደ ውስጥ ገቡ፣ ነገር ግን የጌታ ኢየሱስን ሥጋ አላገኙም።
4ስለዚህ ነገር ግራ ተጋብተው ሳሉ፣ የሚያብረቀርቅ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በድንገት ከአጠገባቸው ቆመው አገኙ።
5ሴቶቹ በፍርሃት ተሞልተውና ወደ መሬት አቀርቅረው ሳሉ፣ ሰዎቹ ፣“ስለምን ሕያውን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ?
6እርሱ በዚህ የለም፣ ተነሥቷል! ገና በገሊላ ሳለ፣
7እንዴት በኃጢአተኞች ሰዎች እጅ ተላልፎ እንደሚሰጥ፣ እንደሚሰቀልና በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ የነገራችሁን አስታውሱ" አሏቸው።
8ሴቶቹ ቃሎቹን አስታወሱ፣
9ከመቃብሩም ተመለሱና እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለዐሥራ አንዱና ለተቀሩትም ነገሩ።
10መግደላዊት ማርያም፣ ዮሐናና የያዕቆብ እናት ማርያም እንዲሁም ሌሎች ሴቶች ሁኔታውን ለሐዋርያት ነገሯቸው።
11ነገር ግን ይህ ንግግር ለሐዋርያቱ ቀልድ ስለ መሰላቸው፣ ሴቶቹን አላመኗቸውም፣
12ሆኖም ግን ጴጥሮስ ተነሣና እየሮጠ ወደ መቃብሩ ሄደ፣ ከዚያም አጎንብሶ ወደ ውስጥ ሲመለከት፣ የተልባው እግር ጨርቅ ለብቻው ተቀምጦ አየ። ከዚያ በኋላ ጴጥሮስ ምን ተፈጥሮ ይሆን ብሎ እያሰበ ወደ ቤቱ ተመለሰ።
13እነሆ፣ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያው ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ርቆ ወደሚገኝ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር እየተጓዙ ነበር።
14ስለሆኑት ነገሮች ሁሉ በመንገዳቸው ላይ እርስ በርስ ይነጋገሩ ነበር።
15እየተነጋገሩና እየተጠያየቁ በመሄድ ላይ ሳሉ፣ ኢየሱስ ወደ እነርሱ ተጠግቶ ይሄድ ነበር።
16ነገር ግን እርሱን እንዳያውቁት ዐይኖቻቸው ተይዘው ነበር።
17ኢየሱስ፣ “እናንተ ሁለታችሁ እየተጓዛችሁ የምትነጋገሩት ስለምንድን ነው?” አላቸው። ያዘኑ መስለው ቆም አሉ።
18ስሙ ቀለዮጳ የተባለ ከሁለቱ አንዱ፣ “በኢየሩሳሌም ሰሞኑን የተደረጉትን ነገሮች የማታውቅ አንተ ብቻ ነህን?" ብሎ መለሰለት።
19ኢየሱስም፣ “ነገሮቹ ምንድን ናቸው?” አላቸው።
20እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱለት፣ “የካህናት አለቆችና ገዢዎቻችን ኢየሱስ የተባለውን ናዝራዊና ነቢይ እንዴት አድርገው እንደ ፈረዱበትና ለሞትና ለስቅላት አሳልፈው እንደ ሰጡት ነዋ።
21እስራኤልን ነጻ ያወጣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን ነበር። አዎን፣ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ይህ ነገር ከሆነ አሁን ሦስተኛ ቀኑ ነው”
22ነገር ግን ጠዋት ወደ መቃብሩ የሄዱ ከእኛ ጋር የሆኑ አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን።
23ሥጋውን ባላገኙ ጊዜ፣ በመቃብሩ ውስጥ ሥጋውን እንዳላገኙና እርሱ ሕያው ሆኗል ብለው የነገሯቸውን የመላእክት ራእይ አይተናል አሉ።
24ከእኛ ጋር ካሉት ወንዶችም አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት። ነገር ግን እርሱን አላዩትም”።
25ኢየሱስም፣ “ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ለማመን የዘገያችሁ እናንተ ሞኞች!
26ክርስቶስ በእነዚህ ነገሮች መሠቃየቱና ወደ ክብሩ መግባቱ ግድ መሆኑን አታውቁምን?" አላቸው።
27ከዚያም ከሙሴ ጀምሮ እስከ ነቢያት መጻሕፍት፣ በመጻሕፍት ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን ተረጐመላቸው።
28ወደሚሄዱበት መንደር በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ ቀደም ቀደም እያለ መሄድ ጀመረ።
29ነገር ግን እነርሱ፣ “ቀኑ እየመሸ ጊዜውም እያለፈ ስለ ሆነ ከእኛ ጋር እደር” ብለው ጎተጎቱት። ስለዚህ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ሊያድር ሄደ።
30ለመብላት ከእነርሱ ጋር በማዕድ በተቀመጠ ጊዜ፣ እንጀራውን ወሰደና ከባረከው በኋላ ቈርሶ ሰጣቸው።
31በዚህ ጊዜ ዐይኖቻቸው ተከፈቱና አወቁት። እርሱ ግን ከዐይናቸው ተሰወረባቸው።
32እርስ በርሳቸው፣ “በመንገድ ላይ አብረን ሳለን ሲያናግረንና መጻሕፍትን ሲከፍት ልባችን በውስጣችን ይቃጠልብን አልነበርምን?” ተባባሉ።
33በዚያው ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም ተሰብስበው እንዲህ እያሉ አገኟቸው፤
34“ጌታ በእርግጥ ተነሥቷል፣ ለስምዖንም ታይቷል።”
35ከዚያም በመንገድ ላይ የሆነውን ነገርና ኢየሱስ በማዕድ እንጀራን በሚቈርስበት ጊዜ እንዴት እንደ ታያቸው ተናገሩ።
36እነዚህን ነገሮች እየተናገሩ እያሉ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን" አላቸው።
37እነርሱም ስለ ተሸበሩና በፍርሃት ስለ ተዋጡ መንፈስ ያዩ መሰላቸው።
38ኢየሱስ፣ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ በልባችሁ ጥያቄዎች ይነሣሉ?
39እኔው ራሴ ስለ መሆኔ እጆቼንና እግሮቼን እዩ። ዳሳችሁም እዩኝ። በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም" አላቸው።
40ይህን ተናግሮ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው።
41ከደስታ የተነሣ ማመን ተስኗቸው ግራ ተጋብተው ሳሉ፣ ኢየሱስ፣ “የሚበላ ጥቂት ነገር ይኖራችኋል?” አላቸው።
42የተጠበሰ ዐሣ ሰጡት።
43ኢየሱስም ወስዶ በፊታቸው በላው።
44እንዲህም አላቸው፤ “ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙራት የተጻፈው ሁሉ መፈጸም እንደሚገባው ነግሬአችሁ ነበር።”
45ከዚያም መጻሕፍትን ይረዱ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው።
46እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ ክርስቶስ መሠቃየት፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን መካከል መነሣት እንደሚገባው በመጻሕፍት ተጽፏል።
47ደግሞም ንስሐና የኃጢአት ይቅርታ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለአሕዛብ ሁሉ በስሙ መሰበክ አለበት።
48እናንተ የእነዚህ ነገሮች ምስክሮች ናችሁ።
49እነሆ፣ የአባቴን ተስፋ በእናንተ ላይ እልካለሁ። ኅይልን ከላይ እስከምትቀበሉ ድረስ በዚህ ከተማ ሆናችሁ ተጠባበቁ።"
50ከዚያም ኢየሱስ ወደ ቢታንያ እስከሚቃረቡ ድረስ ይዟቸው ሄደ። እጆቹንም አነሣና ባረካቸው፤
51እየባረካቸውም ሳለ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አለ።
52ስለዚህ እነርሱ ሰገዱለት፣ እጅግ ደስ እያላቸውም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
53በቤተ መቅደስም ያለ ማቋረጥ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።