1ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለ፦
2"ከሕዝቡ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ አሥራ ሁለት ሰዎች ምረጥ።
3እንዲህ ብለህ ትእዛዝ ስጣቸው፦"በዮርዳኖስ መካከል የካህናት እግር ከቆመበት ስፍራ አሥራ ሁለት ድንጋዮችን አንሡ፤ ተሸክማችሁም በዚህ ሌሊት በምታድሩበት ስፍራ አኑሩአቸው።"
4ከዚያም ኢያሱ ከእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንድ አንድ ሰው የመረጣቸውን አሥራ ሁለት ሰዎች ጠራቸው።
5ኢያሱም አላቸው፦"በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በዮርዳኖስ መካከል፤ እያንዳንዱም ሰው በጫንቃው ከአንዳንድ ድንጋይ ጋር በእስራኤል ልጆች ሁሉ ነገድ ቁጥር አሥራ ሁለት ድንጋዮችን ተሸክመው ይለፉ።
6፤ልጆቻችሁም በሚመጣው ዘመን፦ እነዚህ ድንጋዮች ለእናንተ ምን ትርጉም አላቸው? ብለው በሚጠይቁበት ጊዜ ይህ በመካከላችሁ ምልክት ይሆናል።
7በዚያን ጊዜ እናንተም እንዲህ ብላችሁ ትመልሳላችሁ፦ "በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለተቋረጠ ነው። በተሻገሩም ጊዜ የዮርዳኖስ ውኃ ቆመ፤ እነዚህም ድንጋዮች ለእስራኤል ልጆች ለዘላለም መታሰቢያ ይሆናሉ።"
8የእስራኤልም ልጆች ኢያሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔርም ኢያሱን እንደ ተናገረው በእስራኤል ነገድ ቁጥር ከዮርዳኖስ መካከል እንደ እስራኤል ነገድ ቁጥር አሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሥተው ወደሚያድሩበት ስፍራ ወሰዱ። በዚያም በሚያድሩበት ስፍራ አኖሩአቸው።
9ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮች በቆሙበት ስፍራ በዮርዳኖስ መካከል ሌሎችን አሥራ ሁለት ድንጋዮች ተከለ። እስከ ዛሬም ድረስ መታሰቢያ ሆነው በዚያ አሉ።
10ሙሴም ኢያሱን እንዳዘዘው ሁሉ እግዚአብሔር ኢያሱን ለሕዝቡ እንዲነገር ያዘዘው ነገር ሁሉ እስክፈጸም ድረስ ታቦቱን የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል ቆመው ነበር። ሕዝቡም ፈጥነው ተሻገሩ።
11ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው መሻገራቸውን በጨረሱ ጊዜ የእግዚአብሔር ታቦትና ካህናቱ በሕዝቡ ፊት ተሻገሩ።
12ሙሴም እንዳዘዘቸው የሮቤል ልጆች፥ የጋድም ልጆች፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ተሰልፈው በእስራኤል ልጆች ፊት ተሻገሩ።
13አርባ ሺህ ያህል ሰዎች ጋሻና ጦራቸውን ይዘው ለጦርነት በእግዚእብሔር ፊት ወደ ኢያሪኮ ሜዳ ተሻገሩ።
14በዚያም ቀን እግዚአብሔር ኢያሱን በእስራኤል ሁሉ ፊት ከፍ አደረገው። ሕዝቡም ሙሴን እንዳከበሩት በዕድሜው ሁሉ አከበሩት።
15እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦
16"የምስክርን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት ከዮርዳኖስ እንዲወጡ እዘዝ።"
17ኢያሱም ካህናቱን፦ ከዮርዳኖስ ውጡ ብሎ አዘዛቸው።
18የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት ከዮርዳኖስ መካከል በወጡ ጊዜና የካህናቱም እግር ጫማ ደረቅ መሬት መርገጥ በጀመረ ጊዜ የዮርዳኖስ ውኃ ወደ ስፍራው ተመለሰ፤ ቀድሞም ከአራት ቀናት በፊት እንደ ነበረ በዳሩርቻው ሁሉ መፍሰስ ጀመረ።
19ሕዝቡም በመጀመሪያው ወር በአሥረኛው ቀን ከዮርዳኖስ ወጡ። ከኢያሪኮ በስተ ምሥራቅ በኩል በጌልገላ ሰፈሩ።
20ከዮርዳኖስም ውስጥ የወሰዱአቸውን አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ኢያሱ በጌልገላ አቆማቸው።
21ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ "በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ አባቶቻቸውን፦ እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው? ብለው ሲጠይቁ፥
22ለልጆቻችሁ እንዲህ ብላችሁ ታስታውቃላችሁ፦ እስራኤል ይህን ዮርዳኖስን በደረቅ ተሻገረ።
23እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ የኤርትራን ባሕር ከፊታችን እንዳደረቀ እንዲሁ እስክትሻገሩ ድረስ አምላካችሁ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ውኃ ከፊታችሁ አደረቀ።
24የእግዚአብሔርም እጅ ጠንካራ እንደ ሆነች የምድር አሕዛብ ሁሉ እንዲያውቁ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ለዘላለሙ እንድታከብሩ ነው።