1ኢዮብም ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰ፥
2"ሁሉን ለማድረግ እንደምትችል፥ ዓላማህ ሊደናቀፍ እንደማይችል አውቃለሁ።
3'ያለዕውቀት ዕቅዴን የሚያጨልም ይህ ማነው?' ብለህ ጠይቀኸኛል። ስለዚህ የማላውቀውን፥ ያልተረዳሁትን፥ ለማወቅም እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን ነገር ተናግሬአለሁ።
4አንተም፥ 'አሁንም፥ አድምጥ፥ እኔ እናገራለሁ፤ አንዳንድ ነገሮችን እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ትነግረኛለህ' አልከኝ።
5ስለአንተ መስማትን በጆሮዬ ሰምቼ ነበር፥ አሁን ግን ዓይኖቼ አዩህ።
6ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ በአመድና በትቢያ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ"።
7እግዚአብሔር ኢዮብን ይህን ቃል ከተናገረው በኋላ ቴማናዊውን ኤልፋዝን እንዲህ አለው፥ "አንተና ሁለቱ ጓደኞችህ አገልጋዬ ኢዮብ እንዳደረገው ስለ እኔ ትክክለኛውን ነገር አለተናገራችሁምና ቁጣዬ በእናንተ ላይ ነዶባችኋል።
8አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችንና ሰባት አውራ በጎችን ለራሳችሁ ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ኢዮብ ሂዱ፤ ለራሳችሁም የሚቃጠል ምስዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ። እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ አገልጋዬ ኢዮብ ይጸልይላችኋል፤ እኔም ጸሎቱን እቀበላለሁ። አገልጋዬ ኢዮብ እንዳደረገው ስለ እኔ ትክክለኛውን ነገር አልተናገራችሁምና።"
9ስለዚህ ቴማናዊው ኤልፋዝ፥ ሹሐዊው በልዳዶስና ናዕማታዊው ሶፋር እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው ሄደው አደረጉ፤ እግዚአብሔርም ኢዮብን ተቀበለው።
10ኢዮብ ስለ ጓደኞቹ በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔር እንደገና አበለጸገው። ቀድሞ ከነበረው በላይ እግዚአብሔር ዕጥፍ አድርጎ ሰጠው።
11ከዚያም የኢዮብ ወንድሞቹና እህቶቹ ሁሉ፥ ቀድሞ ያውቁት የነበሩትም ሁሉ እርሱ ወደነበረበት መጡ፤ ከእርሱም ጋር ምግብ በሉ። እነርሱም ሐዘኑን ተጋሩት፤ እግዚአብሔር አምጥቶበት ስለነበረው መከራ ሁሉ አጽናኑት። እያንዳንዳቸውም ለኢዮብ ጥሬ ብርና የወርቅ ቀለበት ሰጡት።
12እግዚአብሔር ከመጀመሪያው ይልቅ የኢዮብን የኋለኛውን ዘመን ባረከለት፤ እርሱም ዐሥራ አራት ሺህ በጎች፥ ስድስት ሺህ ግመሎች፥ አንድ ሺህ ጥማድ በሬዎች፥ አንድ ሺህም ሴት አህዮች ነበሩት።
13ደግሞም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ነበሩት።
14የመጀመሪያ ሴት ልጁን ይሚማ፥ ሁለተኛዋን ቃሥያ፥ ሦስተኛዋን አማልቶያስ ቂራስ ብሎ ሰየማቸው።
15በሀገሩ ሁሉ እንደ ኢዮብ ሴቶች ልጆች የተዋቡ ሴቶች አልተገኙም። አባታቸውም ከወንድሞቻቸው እኩል ርስትን ሰጣቸው።
16ከዚህ በኋላ ኢዮብ 140 አመት ኖረ፤ እርሱም ወንዶች ልጆችን፥ የወንዶች ልጆቹን ወንዶች ልጆች እስከ አራት ትውልድ ድረስ አየ።
17ከዚያም ኢዮብ አርጅቶ፥ ዕድሜንም ጠግቦ ሞተ።