1ሌዋታንን በዓሳ መንጠቆ ልትይዘው ትችላለህ? ወይስ መንጋጋዎቹን በገመድ ታስራለህ?
2በአፍንጫው ገመድ ልታስገባ ወይም አገጩን በችካል ልትበሳው ትችላለህ?
3አብዝቶስ ይለምንሃል? በለሰለሱ ቃላትስ ያናግርሃል?
4የሁልጊዜ አገልጋይህ ለመሆን እንድትወስደው ከአንተ ጋር ስምምነት ያደርጋል?
5ከወፍ ጋር እንደምትጫወት ከእርሱ ጋር ትጫወታለህ? ሴት አገልጋዮችህ እንዲጫወቱበት ታስርላቸዋለህ?
6ዓሳ አጥማጆችስ በእርሱ ላይ ይደራደራሉ? ለነጋዴዎችስ ያከፋፍሉታል?
7ቆዳውን በአንካሴ ወይም ራሱን በዓሳ መውጊያ ጦር ልትበሳው ትችላለህ? አንድ ጊዜ ብቻ
8እጅህን በላዩ ላይ አድርግ፥ ያን ጊዜ ግብግቡን አትረሳውም፥ እንዲህ ያለውን ተግባርም አትደግመውም።
9ተመልከት፥ ማንም ይህንን ለማድረግ ተስፋ ቢያደርግ ሐሰተኛ ነው፤ እርሱን በማየቱ ብቻ በድንጋጤ የማይወድቅ ማነው?
10ሌዋታንን ለመቀስቀስ የሚደፍር የለም፤ ማንስ በፊቱ ሊቆም ይችላል?
11እንድመልስለት ማንኛውንም ነገር አስቀድሞ ለእኔ የሰጠኝ ማነው? ከሰማይ በታች ያለው ሁሉ የእኔ ነው።
12ስለ ሌዋታን እግሮች፥ ስለ ብርታቱና ስለተዋበው ቅርጹ ከመናገር ዝም አልልም።
13ቆዳውን ማን ሊገፈው ይችላል? ድርብ መከላከያውንስ ማን ሊበሳው ይችላል?
14አስፈሪ ጥርሶቹ የተገጠገጡበትን የፊቱን ደጆች ማን ሊከፍት ይችላል?
15ጀርባው ተቀራርበው ከተጣበቁ ንብርብር ጋሻዎች የተሠራ ነው።
16አንደኛው ከሌላኛው ጋር እጅግ ከመቀራረቡ የተነሣ በመካከላቸው ነፋስ አያስገባም።
17እርስ በእርስ ተገናኝተዋል፥ ሊነቅሏቸው እስከማይቻልም ድረስ በአንድነት ተጣብቀዋል።
18ከእንጥሽታው የብርሃን ብልጭታ ይወጣል፤ ዓይኖቹ እንደ ንጋት ጮራ ያበራሉ።
19የሚነድ ፍም፥ የእሳትም ትንታግ ከአፉ ይወጣል።
20በእሳት ላይ ተጥዶ በኃይል እንደሚንተከተክ ድስት ከአፍንጫው ጢስ ይወጣል።
21እስትንፋሱ ከሰሉን እንዲቀጣጠል ያደርገዋል፤ ከአፉም እሳት ይወጣል።
22ብርታት በአንገቱ ውስጥ አለ፥ ሽብርም በፊት ለፊቱ ይጨፍራል።
23የሥጋው እጥፋቶች እርስ በእርሳቸው የተገጠገጡ ናቸው፤ በእርሱ ላይ ጸንተዋል፤ ሊያነቃንቋቸውም አይቻልም።
24ልቡ እንደ ድንጋይ የጠነከረ ነው፤ በእርግጥም እንደ ወፍጮ መጅ ጠንካራ ነው።
25ቀና በሚልበት ጊዜ አማልክት እንኳ ይፈራሉ፤ ከፍርሃታቸውም የተነሣ ወደኋላቸው ይመለሳሉ።
26ሰይፍ ቢቆርጠው አንዳች አይሰማውም፤ ጦር፥ ቀስት፥ ወይም የትኛውም የጦር መሣሪያ ቢነጣጠርበት አይሰጋም።
27ብረትን እንደ አገዳ፥ ናስንም እንደ ነቀዘ እንጨት ይቆጥረዋል።
28ቀስት እንዲሸሽ አያደርገውም፥ የወንጭፍ ድንጋይም ለእርሱ እንደ ገለባ ነው።
29ዱላ እንደ አገዳ ተቆጥሯል፤ በሚወረወርበት ጦር ላይም ይስቃል።
30የሆዱ ስር እንደ ገል ስብርባሪ የሾለ ነው፤ የእህል መውቂያ መሣሪያ ይመስል በጭቃው ላይ ምልክት ትቶ ያልፋል።
31በድስጥ ውስጥ ያለ ውሃ እንደሚፈላ የጥልቁን ውሃ ያናውጠዋል፤ ባህሩንም እንደ ሽቶ ቢልቃጥ ያደርገዋል።
32የሄደበት መንገድ ከበስተኋላው እንዲያበራ ያደርጋል፤ ይህንን ያየም ጥልቁን ነጭ ነው ብሎ ያስባል።
33ያለ ፍርሃት እንዲኖር የተፈጠረ በምድር ላይ እርሱን የሚያክል የለም።
34ኩሩ የሆነውን ሁሉ ያያል፤ እርሱ በትዕቢት ልጆች ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው።"