መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 63

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ይህ ከኤዶምያስ፣ ልብሱም የቀላ ከባሶራ የሚመጣ፣ አለባበሱ ያማረ፣ በጕልበቱ ጽናት በራስ መተማመን የሚራመድ ማን ነው? በጽድቅ የምናገር ለማዳንም የምበረታ እኔ ነኝ።
2ቀሚስህ ስለ ምን ቀላ፣ ልብስህስ በወይን መጥመቂያ እንደሚረግጥ ሰው ልብስ ስለ ምን መሰለ?
3መጥመቂያውን ብቻዬን ረግጫለሁ፣ ከአሕዛብም አንድ ሰው ከእኔ ጋር አልነበረም፤ በቍጣዬ ረገጥኋቸው በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፤ ደማቸውም በልብሴ ላይ ተረጭቶአል፣ ልብሴንም ሁሉ አስድፌአለሁ።
4የምበቀልበት ቀን በልቤ ነውና፣ የምቤዥበትም ዓመት ደርሶአልና።
5ተመለከትሁ፣ የሚረዳም አልተገኘም፤ የሚያግዝም አልነበረምና ተደነቅሁ፤ ስለዚህ የገዛ ክንዴ መድኃኒት አመጣልኝ፣ ቍጣዬም እርሱ አገዘኝ።
6በቍጣዬም አሕዛብን ረገጥሁ በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፣ ደማቸውንም ወደ ምድር አፈሰስሁት።
7እግዚአብሔር እንደ ሰጠን ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የእግዚአብሔርን ምስጋና፣ እንደ ምሕረቱና እንደ ቸርነቱም ብዛት ለእስራኤል ቤት የሰጠውን ትልቅ በጎነት አሳስባለሁ።
8እርሱም፣ "በእውነት ሕዝቤ፣ ሐሰትን የማያደርጉ ልጆች ናቸው" አለ፤ መድኃኒትም ሆነላቸው።
9በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፣ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፣ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው።
10እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ። ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆነባቸው፣ እርሱም ተዋጋቸው።
11እርሱም እንዲህ ብሎ የቀደመውን ዘመን አሰበ። "የበጎቹን እረኛ ከባሕሩ ያወጣው ወዴት ነው ያለ? ቅዱስ መንፈሱንም በመካከላቸው ያኖረ ወዴት ነው ያለ?
12የከበረውንም ክንድ በሙሴ ቀኝ ያስሄደ፣ ለራሱም የዘላለምን ስም ያደርግ ዘንድ ውኃውን በፊታቸው የከፈለ፣
13በምድረ በዳም እንደሚያልፍ ፈረስ፣ በቀላይ ውስጥ ያለ ዕንቅፋት ያሳለፋቸው ወዴት ነው ያለ?
14ወደ ሸለቆ እንደሚወርዱ ከብቶች፣ እንዲሁ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ዕረፍት አመጣቸው። እንዲሁም ለራስህ የከበረ ስም ታደርግ ዘንድ ሕዝብን መራህ።
15ከሰማይ ቁልቊል ተመልከት፣ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ፤ ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ተከለከለ።
16አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን፣ አንተ አባታችን ነህ፤ 'አቤቱ፣ አንተ አባታችን ነህ፣' ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው።
17አቤቱ፣ ከመንገድህ ለምን አሳትኸን? እንዳንፈራህም ልባችንን ለምን አጸናህብን? ስለ ባሪያዎችህ ስለ ርስትህ ነገዶች ተመለስ።
18የተቀደሰው ሕዝብህ መቅደስህን ጥቂት ጊዜ ወረሱት፤ ጠላቶቻችንም ረግጠውታል።
19ከዘላለም እንዳልገዛኸን በስምህም እንዳልተጠራን ሆነናል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።