መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 58

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1"በኃይልህ ጩኽ፣ አትቈጥብ፣ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፣ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር።
2ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ፤ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል። ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ።
3'ስለ ምን ጾምን፣' አንተም 'አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፣ አንተም አላወቅህም?' ይላሉ። ተመልከቱ፣ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፣ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ።
4ተመልከቱ፣ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም።
5እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፣ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን?
6እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የክፋት በደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፣ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፣ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን?
7እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፣ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፣ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፣ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?
8የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፣ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፣ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፣ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል።
9የዚያን ጊዜ ትጠራለህ፣ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም፣ "እነሆኝ" ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፣ ጣትህንም መጥቀስ ብትተው፣
10ባታንጐራጕርም፣ ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፣ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፣ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል።
11እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል አጥንትህንም ያጠናል። አንተም እንደሚጠጣ ገነት፣ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ።
12ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ፣ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል፤ አንተም፣ "ቅጥሩን ጠጋኝ፣" "የመኖሪያ መንገድን አዳሽ" ትባላለህ።
13ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፣ ሰንበትንም ደስታ፣ እግዚአብሔርም የቀደሰውን ክቡር ብትለው፣ የገዛ መንገድህንም ከማድረግ ፈቃድህንም ከማግኘት ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው።
14"በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በምድርም ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፤ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ፤ የእግዚአብሔር አፍ ተናግሮአልና።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።