መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 57

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ጻድቅ ይጠፋል፣ በልቡም ነገሩን የሚያኖር የለም፤ ምሕረተኞችም ይወገዳሉ፣ ጽድቅም ከክፋት ፊት እንደ ተወገደ ማንም አያስተውልም።
2ወደ ሰላም ይገባል፤ በቅንነት የሄደ በአልጋው ላይ ያርፋል።
3እናንተ የአስማተኛይቱ ልጆች፣ የአመንዝራውና የጋለሞታይቱ ዘር፣ ወደዚህ ቅረቡ።
4በማን ታላግጣላችሁ? በማንስ ላይ አፋችሁን ታላቅቃላችሁ? ምላሳችሁንስ በማን ላይ ታስረዝማላችሁ?
5እናንተ በአድባር ዛፎች መካከል በለመለመም ዛፍ ሁሉ በታች በፍትወት የምትቃጠሉ፣ እናንተም በሸለቆች ውስጥ በዓለትም ስንጣቂዎች በታች ሕፃናትን የምታርዱ፣ የዓመፅ ልጆችና የሐሰት ዘር አይደላችሁምን?
6በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች እድል ፈንታሽ ናቸው፣ እነርሱም ዕጣሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፣ የእህልንም ቍርባን አቅርበሻል። እንግዲህ በዚህ ነገር አልቈጣምን?
7ከፍ ባለውም በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፣ መሥዋዕትንም ትሠዊ ዘንድ ወደዚያ ወጣሽ።
8ከመዝጊያውና ከመቃኑ በኋላ መታሰቢያሽን አደረግሽ፤ እኔን ትተሽ ለሌላ ተገልጠሻል፣ ወጥተሽ መኝታሽን አስፍተሻል፤ ቃል ኪዳንም ተጋባሻቸው፣ ባየሽበትም ስፍራ ሁሉ መኝታቸውን ወደድሽ።
9ዘይትም ይዘሽ ወደ ንጉሡ ሄድሽ፣ ሽቱሽንም አበዛሽ፣ መልእክተኞችሽንም ወደ ሩቅ ላክሽ፣ እስከ ሲኦልም ድረስ ተዋረድሽ።
10በመንገድሽም ብዛት ደከምሽ፣ ነገር ግን፣ "ተስፋ የለም" አላልሽም፤ የጕልበትን መታደስ አገኘሽ፣ ስለዚህም አልዛልሽም።
11"ሐሰትን የተናገርሺው እኔንም ያላሰብሺው በልብሽም ነገሩን ያላኖርሺው ማንን ሰግተሽ ነው? ማንንስ ፈርተሽ ነው? እኔ ብዙ ጊዜ ዝም አልሁ፣ አንቺም አልፈራሽም።
12እኔ ጽድቅሽን እናገራለሁ፣ ሥራሽም አይረባሽም።
13ወደ አንቺ የሰበሰብሻቸው በጮኽሽ ጊዜ ይታደጉሽ፤ ንፋስ ግን ይወስዳቸዋል ሽውሽውታም ሁሉን ያስወግዳቸዋል። በእኔ የታመነ ግን ምድሪቱን ይገዛል፣ የተቀደሰውንም ተራራዬን ይወርሳል።
14እርሱም፣ 'ጥረጉ፣ መንገድን አዘጋጁ! ከሕዝቤም መንገድ ዕንቅፋትን አውጡ!" ይላል።
15ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፣ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል፣ "የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፣ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፣ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ።
16መንፈስም የፈጠርሁትም ነፍስ ከፊቴ እንዳይዝል ለዘላለም አልጣላም፣ ሁልጊዜም አልቈጣም።
17ስለ ኃጢአቱ ጥቂት ጊዜ ተቈጥቼ ቀሠፍሁት፣ ፊቴን ሰውሬ ተቈጣሁ፤ እርሱም በልቡ መንገድ እያፈገፈገ ሄደ።
18መንገዱን አይቻለሁ እፈውሰውማለሁ፣ እመራውማለሁ፣ ለእርሱና ስለ እርሱም ለሚያለቅሱ መጽናናትን እመልሳለሁ።
19የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ። በሩቅም በቅርብም ላለው ሰላም ሰላም ይሁን፣ እፈውሰውማለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።
20ክፉዎች ግን እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው፤ ጸጥ ይል ዘንድ አይችልምና፣ ውኆቹም ጭቃና ጕድፍ ያወጣሉና።
21ለክፉዎች ሰላም የላቸውም" ይላል አምላኬ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።